የመለስ ዜናዊ እና የስሎቦዳን ሚሎሶቪች መመሳሰል

Source: http://welkait.com/?p=12107
Print Friendly, PDF & Email

የመለስ ዜናዊ እና የስሎቦዳን ሚሎሶቪች መመሳሰል

(ልሣነ ዐማራ- Amhara Press)

Melez Zenawi and Slobodan Milošević

ይህንን የሁለት አምባገነኖች ማነጻጸሪያ ለመከተብ የተገደድነው ባለፈው ጊዜ የህዋሃቱ አባይ ጸሃየ በፌድራሊዝም ዙሪያ በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ላይ እንዲህ የሚል አስቂኝ ቀልድ ስለተናገረ ነው “ዩጎዝላቪያ የፈራረሰችው በአንድ ብሄር የበላይነት ቁጥጥር ስር ስለነበረች ነው፤ ሰርቦች ሁሉንም ነገር ስለተቆጣጠሩት ሃገሪቱ ልትፈራርስ ችላለች ፤ በኢትዮጵያ ግን ያ እድል የለም” የሚል የደንቆሮ ንግግር። የትግራይ የበላይነት የለም እና ኢትዮጵያ አትፈርስም ማለቱ ነው በእርሱ ቤት። እስኪ ለመሆኑ የኢትዮጵያ አፍራሽ መሃንዲስ የሆነው መለስ ዜናዊ እና አቻው የዩጎዝላቪያው ስሎቦዳን ሚሎሶቪችን ባህሪ እንገምግም እና የኢትዮጵያን እጣፈንታም በዚያው ገረፍ አድርገን እንይ
———————————————————————————-

★ መለስ ዜናዊ ትግሬ ነው። ሚሎሶቪች ደግሞ ሰርብ ነው።

★ መለስ ዜናዊ የህዋሃት ሊቀመንበር ነበር። ሚሎሶቪችም የሰርቢያ ሶሻሊስት ፓርቲ መሪ ነበር።

★ መለስ ዜናዊ ወደ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተርነት የመጣው ‘ትግራይ በአማራ ተጨቁናለች’ በሚል እሳቤ በተደረገ ትግል ነው። ሚሎሶቪች የዩጎዝላቪያ መሪ የሆነው ደግሞ የእርሱ ዘር የሆነው ሰርብ በአልባኒያዎች እና ኮሶቮዎች በደል ደርሶበታል እና ማሻሻያ ያስፈልጋል በሚል ነበር። (ትግራይ የኢትዮጵያ አንዷ አካል እንደሆነች ሁሉ ሰርቢያ ደግሞ የዩጎዝላቪያ አንዷ ክልል ነበረች)

★ መለስ ስልጣን ላይ እንደወጣ የደርግን ኮሚኒስታዊ ስርአት በማስወገድ የውሸት ‘ህብረ ብሄራዊ’ ፌድራላዊ የፖለቲካ ስርአት በኢትዮጵያ መሰረተ። ሚሎሶቪች የዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት እንደሆነ ወዲያውኑ የማርክሲስታዊ እና ሌኒናዊ የአንድ ፓርቲ ስርአትን በማስወገድ ፌክ ህብረ ብሄራዊ ስርአትን (multi party system) መሰረተ።

★ መለስ ዜናዊ ስልጣን በወጣ በጥቂት ጊዚያት ውስጥ የመቀሌን ህዝብ ሰብስቦ እንዲህ የሚል የእብሪት ንግግር ተናገረ ““እንኳንም የእናንተ ሆኜ ተፈጠርኩ! እንኳንም ከእናንተ ወርቅ አብራክ ወጣሁ!እኮራለሁ” በማለት። በዚህ ሳያበቃ በተደጋጋሚ ለአማራ ያለውን ጥላቻ በየመድረኩ ይናገር ነበር። በተመሳሳይ መልኩ ሚሎሶቪች የሰርቢያ ሶሻሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆኖ ሲመረጥ ቤልግሬድ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቹ “በውስጥም በውጭም ያሉ የሰርቢያ ጠላቶች (ኮሶቮዎች፤ አልባኒያዎች) ተነስተውብናል። እኛ ግን እንዲህ እንላቸዋለን ‘መቸውንም አንፈራም፤ ከጦር ሜዳም አንሸሽም’” የሚል የትንኮሳ እና እብሪት ንግግር አደረገ። ሚሎሶቪች በዚህ ሳያበቃ በፓርቲው ሚስጥራዊ ስብሰባ ላይ ‘የምንሰራው ስራ ከሰርቢያ ጥቅም አኳያ ብቻ ነው፤ ህገመንግስት፤ ህግ ወይንም የፓርቲ መርህ ብሎ ነገር የለም፤ ዋናው በፌደሬሽኑ ውስጥ የሰርቢያ ጥቅም መከበር ብቻ ነው” አለ። አሁን ያለችውን ትግራይ እና ሰርቢያን ልብ በሉ!

★ መለስ ዜናዊ ስልጣን በተረከበ ገና በሳምንቱ የሃገሪቷን ሃብት በሙሉ እየዘረፈ ወደ ትግራይ እንዲጓዝ አደረገ። መከላከያውን፤ ዲፕሎማሲው፤ ኢኮኖሚ አውታሩ እና ቁልፍ ፖለቲካው በትግሬ ብሄር እንዲወረር አደረገ። የአማራ መሬቶችን ራያን እና ወልቃይትን ወደ ትግራይ በማካለል የትግራይ የበላይነትን ለማረጋገጥ 20 ምናምን አመት ሰራ። ሚሎሶቪች ስልጣኑን ካደላደለ በኋላ ቦስኒያ እና ክሮሺያ ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ወደ ሰርቢያ ለመጠቅለል የማስፋፋት ፖሊሲ ነድፎ ይንቀሳቀስ ነበር፤ ዋና አላማውም ‘ታላቋን ሰርቢያን’ መመስረት ነበር። የዩጎዝላቪያን ዲፕሎማሲ የሚመሩትም የተመረጡት ሰርቦች ብቻ ነበሩ። ክሮሺያዎች ይህንን በመቃወማቸው እና የሰርቢያን የበላይነት መቋቋም ባለመቻላቸው የመገንጠል እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ኋላ ላይ ዩጎዝላቪያ እንድትፈራርስ ምክንያት ሆነ። ሁሉም የዩጎዝላቪያ ብሄሮች ለራሳቸው ግዛት ማስፋፊያ በየፊናቸው መሮጥ ጀመሩ። ታላቋ ሰርቢያ፤ ታላቋ ክሮሺያ፤ ታላቋ አልባኒያ፤ ታላቋ መቄዶኒያ እና ሌሎችም። አሁን ላይ ያለውን ታላቋ ትግራይ፤ ታላቋ ኦሮሚያ፤ የአማራ ሪፓብሊክ፤ የኦጋዴን ነጻ መንግስት ምስረታን ልብ ይሏል።

★መለስ ዜናዊ ሃገሪቱን በአምባገነን ስርአት አፍኖ፤ የትግራይ የበላይነትን ሊያሰፍን ሲሞክር፤ በብሄሮች መካከል ቅራኔ በመፍጠር ኢትዮጵያ የምትባል ጥንታዊት ሃገር እንድትበተን የቤት ስራ ሰርቶ አለፈ። ውጤቱንም በጥቂት አመታት የምናየው ይሆናል። ሚሎሶቪች ኮሚኒስታዊ እና አምባገነናዊ ስርአት መስርቶ፤ የሰርቢያን የበላይነት ለማረጋገጥ ሲጥር፤ በብሄሮች መካከል አጉል ፉክክር እና ጥርጣሬ እንዲፈጠር በማድረጉ በአልባንያ፤ ቦስኒያ እና ኮሶቮ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እና የእርስ በእርስ ጦርነቶች እንዲካሄዱ አድርጎ ዩጎዝላቪያ የምትባል ታሪካዊ ሃገርን ወደ አመድነት በመቀየር 7 ትናንሽ ሃገሮች እንዲፈጠሩ አደረገ። 7ቱም ሃገሮች በአሁን ሰአት ድሃዎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ምንጊዜም ውጥረት እንዲነግስ ሆነ! በኢትዮጵያ ብሄሮች መካከል እያደገ የመጣውን አለመተማመን እና ቅራኔ እናስታውስ!

★ መለስ ዜናዊ በጭንቅላት እጢ ሲሰቃይ ኖሮ ብራሰልስ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል በ57 አመቱ ህይወቱ አለፈች። ሚሎሶቪች በልብ ህመም ምክንያት ባልታሰበ መልኩ ኔዘርላንድ ውስጥ በሚገኝ የጦር ወንጀለኞች ማቆያ ጣቢያ ውስጥ በ65 አመቱ ሞቶ ተገኘ። ሁለቱም አውሮፓ ውስጥ መሞታቸው ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ለፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል፤ ሙስናና እና ሰብአዊ መብት ገፈፋ ቅጣታቸውን ሳይቀበሉ ይህችን አለም ተሰናብተዋል።

ክፉ ስራቸው ግን ለዘላለም አብሮን ይኖራል!

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.