የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ወጪ እንዲቀንሱ ጥብቅ መመርያ ወጣ

Source: https://www.ethiopianreporter.com/content/%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%A5%E1%89%B5-%E1%89%A3%E1%88%88-%E1%89%A0%E1%8C%80%E1%89%B5-%E1%88%98%E1%88%A5%E1%88%AA%E1%8B%AB-%E1%89%A4%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8B%88%E1%8C%AA-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B2%E1%89%80%E1%8A%95%E1%88%B1-%E1%8C%A5%E1%89%A5%E1%89%85-%E1%88%98%E1%88%98%E1%88%AD%E1%8B%AB-%E1%8B%88%E1%8C%A3

በዳዊት እንደሻው

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የፌዴራል ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች በቅርቡ ያሠራጨውን የበጀት ወጪ ቅነሳ ማቅረቢያ ቅጽ ሞልተው፣ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርቡ አዘዘ፡፡ በመመርያው መሠረት በርካታ አላስፈላጊ ወጪዎችን እንዲቀንሱ ጠበቅ ያሉ ክልከላዎች ተደርገዋል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት ተግባራዊ እንዲደረግ ሚኒስቴሩ በቅርቡ ካዘጋጀው የወጪ ቅነሳ መመርያ ጋር አብሮ የወጣው ቅጽ፣ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በጀታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያዛል፡፡ ሚኒስቴሩ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በ2010 ዓ.ም. ወጪያቸውን በመቀነስ በጀታቸውን ቁጠባን መሠረት ባደረገ አሠራር እንዲጠቀሙበት አሳስቧል፡፡

ዓመታዊ ፕሮግራም፣ ግብና ውጤትን መሠረት ያላደረገ የበጀት ዝውውርና የተጨማሪ በጀት ጥያቄ መሥሪያ ቤቶች እንዳያቀርቡ መመርያው ከልክሏል፡፡

መመርያው መደበኛ ወጪን በተመለከተ 19 ያህል ግዥዎችና የተለያዩ ወጪዎች ላይ ጥብቅ የሆነ አሠራርና አንዳንዶቹም ላይ ክልከላን አስቀምጧል፡፡

መሥሪያ ቤቶች በየዓመቱ እንደ ቀን መቁጠሪያ ካላንደር፣ አጀንዳዎች፣ የመጽሔት ኅትመትና የደስታ መግለጫ ካርድ ግዢዎችን ከልክሏል፡፡ በተጨማሪም የወረቀት፣ የቶነር፣ የማስታወሻ ደብተርና የእስክሪብቶ ግዢን መቀነስ እንዳለባቸው፣ ነገር ግን የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) እንዲጠቀሙ ያዛል፡፡

ለሠራተኞች በየመሥሪያ ቤቱ የሚከፋፈሉ የፅዳት አላቂ ዕቃዎችን ግዢ በተመለከተ፣ መሥሪያ ቤቶቹ የግዢውን መጠን እንዲቀንሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በተለምዶ በየመሥሪያ ቤቱ የሚደረጉ የመስተንግዶ ወጪዎችን በተመለከተ ከአሁን በኋላ ለሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ዓውደ ጥናቶችና ሴሚናሮች እንደ ሻይ፣ ቡናና ውኃ ከመሳሰሉት በስተቀር ተጨማሪ ግብዣዎች እንዳይደረጉ ይከለክላል፡፡ የሚደረጉት ስብሰባዎችም በተቻለ መጠን በየተቋማቱ አዳራሾች እንዲደረጉና ለሆቴል የሚወጡ ወጪዎች እንዳይኖሩ ያስገነዝባል፡፡

በተጨማሪም ለስብሰባዎችና ለክብረ በዓላት ቦርሳዎችን፣ ቲሸርቶችን፣ ኮፍያዎችን፣ ስካርፎችንና የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳትን መግዛትም በጥብቅ ተከልክሏል፡፡

የውጭ አገር ጉዞን በተመለከተም መመርያ ወጥቷል፡፡ የሚኒስቴሮችና በሥራቸው ያሉ ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ጭምር የውጭ አገር ጉዞ ፕሮግራም ሲኖራቸው የፕሮግራሙ ዓላማ፣ የተሳታፊዎች ብዛት፣ የቆይታቸው ጊዜና ወጪን የሚያሳይ የውጭ ጉዞ መርሐ ግብር በማዘጋጀት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ መፈቀድ እንዳለበት መመርያው ያሳስባል፡፡

የሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተም በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሲፈቀድ ብቻ መከፈል እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ሌላው ድጋፍና ስጦታን በተመለከተም በመመርያው እንደተገለጸው፣ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በዩኒቨርሲቲዎች ከሚማሩ የክረምት ተማሪዎችና አካል ጉዳተኞች በስተቀር ለማንኛውም ድርጅት ሆነ ግለሰብ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ስጦታ መስጠት አይችሉም፡፡

በተጨማሪም ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎችም በመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እንዳይስተናገዱ በመመርያው ታዟል፡፡

ከካፒታል ወጪ ጋር በተያያዘም በበጀት አዋጁ ከፀደቀው ፕሮጀክት ውጪ ፕሮጀክቶችን ማካሄድ እንደማይቻል፣ የተቀፈዱ ፕሮጀክቶችም በታቀደው ጊዜ፣ ወጪና ጥራት እንዲከናወኑ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሥርዓት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡ 

Share this post

One thought on “የመንግሥት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ወጪ እንዲቀንሱ ጥብቅ መመርያ ወጣ

  1. …አንድ ልዋላዊ ሀገር ሲባል ከራሱ ራስ ገዝ ነጻነት፡ የዳርድንበርና ሰንደቅን ጨምሮ ‘ሀገር አስተዳደር’ የሚባልም እንደሚኖር ግድ ይላል። ኢትዮጵያ ባላፉት ፳፯ ዓመት ከዕቁብና ዕድር ባነሰ መዋቅር ድንብና ሕግ ወርዳ ፓርቲ ፖለቲካ ክልል አንሳ… who is in charge? የሚል አስደንጋጭ ጥያቄን አጭሯል። መሪው ማነው የሚያስብል ሀገር አለን? ከለገሠ መለሰ “የቡድን አመራር”..(ቤተሰባዊና ጎጣዊ ) ወደ ኃይለመለስ ደስአለኝ “የኅብረት አመራር” አመራር በደቦ (በልዩ ጥቅማጥቅም)
    >» ዳኛው የለቀቀውን ተጠርጣሪ የፍርድ ቤቱ ዘበኛ አለቅም አለ። ዳኛው ተይዞ ይቅረብ ያሉት ልዩ ጥበቃ ተደርጎለት ከሀገር እንዲወጣ ተደረገ፡ የአርብቶ አደር ሚ/ር ዩኒቨርሲቲውን መሩ፡ የመከላከያ ሚ/ሩ አዲሱን ባቡር መርቀው ነዱ፡ ከንቲባው የመንቀሳቀስና መዘዋወር ፍቃድ ሰጡ፡ ከልላዊ መንግስት ለፌደራሉ ማስጠንቀቂያ ላከ፡ የጠ/ሚሩን ንግግር የጥናት ቡድኑ አጣጣለው። አማራጭ የሌለው ህዝብ በግዱ ይመርጠናል፡ ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር መጪው ዘመን ብሩህ ነው። የሚሉ ቱማታዎች ሲፈጠሩ ጠርጥር፡እነ ሙሳ ሙሴ ኢኮኖሚውን ሾፈሩት ህወአት/ኢህአዴግን እጁን ይዘው በመርጫው አሻገሩት።

    …” ለስብሰባዎችና ለክብረ በዓላት ቦርሳዎችን፣ ቲሸርቶችን፣ ኮፍያዎችን፣ ስካርፎችንና የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳትን መግዛት ልማታዊ፡ አፍቅሮ ህወአት፡ ራዕይ አስቀጣይ! አስባለ፡፡ የፌደራል ኦዲት መስሪያ ቤት ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት ባወጣቸው የኦዲት ሪፖርቶች፣ ሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የገንዘብ ምዝበራ ላይ መሰማራታቸውን ፲፩ ከመቶ ዕድገት ያመጣው ስለሆነ ደስተኛ ናቸው። የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች ሰበብ እየፈለጉ ከበር መልስ የሚደግሱት፡ አዲሱ የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መመርያ፣ መስሪያ ቤቶች ስብሰባም ሆነ ሴሚናር ሲያዘጋጁ፡ መሥሪያ ቤት ተብዬዎች ለስብሰባ፣ ለስልጠናና ለሴሚናር እየተባለ ክፍለ ሀገር ድረስ መሄድም ሆነ ውድ ሆቴሎችን መከራየት እንዲቆም ያሳሰበው መመርያው፣(የሆቴሎቹ ጥቅማጥቅመኞች ቅር አይላቸውምን?) ስብሰባም ሆነ ሴሚናር በየመስሪያ ቤቶቹ አዳራሽ ውስጥ እንዲካሔድ ፐላስማና እስካፒ መጠቀምም ቆጣቢ ልማት ነበር። ግንይህ ሁሉ ሲቆረጠና ሲቆራረጥ ህወአት/ኢህአዴግ ተመሳሟሾቹን አድርባዮች በምን ሆዳቸውን ይሞላዋል? መልካሙ ነገር ህወአት/ኢህአዴግ የሚወደቀው በተቃዋሚ/ተቋቋሚ ብዛት ሳይሆን በደጋፊ/ተደጋፊዎቹ ጫና እንደሆነ ከ፲፭ ዓመት በላይ የተነበይነው ልክ ነበር። የወጪ ቅነሳ መመርያ የወጣው፣ መንግስት የጎሳ ብጥብጥ፡በሥራ ማቆም አድማ፡የውጭ ንግድ ገቢ መጥፋት፡የተጠራቀመ ወለድ፡በግሪክ ፎርሙላ የተሸጠች ቦንድና ያለተመሠረተው ፲ ስኳር ፋብሪካ፡ የችኮላ አዋጅ ወጪ መናር፤ የአበዳሪ ተቋማትም በጥቅማጥቅም አልባነት ፊታቸውን ማዞር፡ የገንዘብ ዕጥረት ችግር ስለገጠመው እንጂ ሙስናና ልዩ ጥቅማጥቅም የዕደገቱ ቱርፋቶች፡ የመለስ ዚናዊ አስተምህሮት ስልሆኑ ሳይበረዝና ሳይከለስ ይቀጥላል። መለስ ባይሞት ፫ሺህ ፭፻ ባርኮች ይኖሩንና ይህ ሁሉ ችግኝ ይተከል ነበር? እንኳንም ተጠቀለለ ሰው ገሎ ችግኝ የሚንከባከብ የአንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማኅበረሰብና ልዩነታችን ውበታችን!? ድንቄም!።

    Reply

Post Comment