የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ምንድን ነው? በፈቃዱ ዘኃይሉ

Source: http://www.mereja.com/amharic/534339

የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ምንድን ነው?

“የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጥናት ሰነድ” የሚል ባለ 46 ገጽ ሐተታ እና በዚሁ መሠረት የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ በኢንተርኔት ተለቀዋል፡፡ አዘጋጁ ኦሕዴድ የሚመራው የኦሮሚያ መንግሥት ነው ተብሎ ቢገመትም በኦፊሴላዊ መንገድ ስላልተለቀቀ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም፡፡ ሆኖም፣ ይህን ያክል ሲወራለት እስካሁን ማስተባበል የነበረበት መንግሥታዊ አካል ስላላስተባበለ እና ከውዥንብሩ ስላላዳነን፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሰፈሩት አንዳንድ ጉዳዮች ትችት የሚያስፈልጋቸው አሳሳቢ ጉዳዮች በመሆናቸው የሚከተለውን አስተያየት አሰፍራለሁ፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49/5 እንዲህ ይነበባል፣ “የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ [የተነሳ] ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡”

የረቂቅ አዋጁም በመግቢያው ላይ ዓላማውን “ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” በተባለው መሠረት እንደሆነ ይናገራል፤ “የጥናት ሰነዱም” የተዘጋጀው ሕገ መንግሥቱን መሬት ላይ በማውረዱ ሒደት እንደሆነ ያትታል፡፡ ቢያንስ ጥናቱ፣ በአዲስ አበባ ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ሳቢያ ተቆስቁሶ ለብዙ ንፁኃን ሕይወት ማለፍ መንስዔ የሆነውን በርካታ ጥያቄዎችን ያነገበው ሕዝባዊ አመፅ እንደምክንያት በመጥቀስ እውነት ለመናገር መድፈር ነበረበት፡፡ የዚህ ሰነድ ባለቤት ኦሕዴድ ቢሆንም የሕወሓትን ይሁንታ ሳያገኝ እዚህ ደረጃ እንደማይደርስ መገመት ቀላል ነው፡፡

“የጥናት ሰነዱ” በሕገ መንግሥቱ ላይ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሊያገኝበት ይገባል ከተባለው ቁም ነገር ይልቅ አዲስ አበባ ስትቆረቆር ነዋሪ የነበሩት “የቱለማ ኦሮሞ” ጎሳ አባላትን ከመጥፋት ለመታደግ ያለመ ይመስላል፡፡ የአዋጁ መግቢያ ደግሞ በአንቀጽ 2/7 ላይ ““የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ከመመሥረቱ በፊት ጀምሮ ነባር ነዋሪ የነበሩ ወይም አሁንም በከተማው ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዎች ማለት ነው” በማለት ሁሉም የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን እንደሚመለከት ይጠቁማል፡፡ አንዳንድ አንቀጾቹ የኦሮሞ ብሔር የከተማው ነዋሪዎችን ነጥሎ የሆኑ መብቶቻቸው ይከበሩላቸዋል ማለቱ ሌሎቹ አይከበሩላቸውም ወይም የኦሮሞ ተወላጆች በተለየ ይታያሉ የሚል አንድምታ እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡ ይህም አዋጁ የሰብኣዊ መብት ምንነት እና የከተማ ኑሮ ግንዛቤ ያላቸው ባለሞያዎች አርቅቀውት ይሆን ወይ የሚለውን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡

አዲስ ነገር

ረቂቅ አዋጁ በአምስት ክፍሎች እና በ34 አንቀጾች ተከፋፍሏል፡፡ በውስጡ በታመመ አዕምሮ ጠንሳሽነት ከተሰገሰጉት እና ከአዲስ አበባ ውጪ ረግጦ የማያውቀውን ብዙኃኑን ካገለሉት አንቀጾች ውጪ አዲስ ነገር ይዟል ሊባል የሚችለው በሁለት አንቀጾቹ ብቻ ነው፡፡ በጠቅላላ ድንጋጌው ‹አዲስ አበባ› እና ‹ፊንፊኔ› – ሁለቱም የከተማዋ ኦፊሴላዊ መጠሪያ ይሆናሉ (አንቀጽ 5) እንዲሁም አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ የከተማዋ የሥራ ቋንቋ ይሆናሉ (አንቀጽ 7) ይላል፡፡ ሁለተኛው፣ አፋን ኦሮሞ ከአማርኛ ጎን የኢትዮጵያ የሥራ ቋንቋ ይሁን ለሚለው የቆየ ጥያቄ ማስታገሻ ይመስላል፡፡

አሳሳቢ ጉዳዮች

1). “የኦሕዴድ ልዩ ጥቅም”

የረቂቁ አንቀጽ 10 “የልዩ ጥቅሙ መርሖዎች” ብሎ ያስቀመጣቸው ነጥቦች (ከሕገ መንግሥቱ በተፃራሪ) የአዋጁ ዓላማ በአዲስ አበባ መስፋፋት የባሕል፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የአካባቢ ተፅዕኖ ስለሚያርፍባቸው በፊንፊኔ ዙሪያ የሚኖሩትን የኦሮሞ ሕዝቦች መጥቀም ሳይሆን በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩትን የኦሮሞ ተወላጆች የተለየ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ የኦሕዴድ ባለሥልጣናት ራስ ወዳድ ፍላጎት ያመነጨው ሐሳብ እንደሆነ ለመገመት አይከብድም፡፡ ይህንን ድምዳሜ የሚያጠናክሩ ሌሎችም አንቀጾች አሉ፡፡ አንቀጽ 11/2 የኦሮሞ ተወላጆች የአዲስ አበባ ምክር ቤት በሕዝቡ ውስጥ ካላቸው ውክልና በተጨማሪ 25 በመቶ እንዲመደብላቸው ይደነግጋል፡፡ አንቀጽ 11/4 የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አዲስ አበባ እንዲገባ ይፈቅዳል፤ አንቀጽ 12/2 እና 12/3 ለኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎች እና ሠራተኞች (ለማስመሰያ “እንዲሁም የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች” የሚል ማሳሳቻ በመጨመር) ኦሕዴዶች (በአገራችን ፖለቲካ በፓርቲ እና በመንግሥት መካከል ልዩነት ስለሌለ) ከሁሉም የበለጠ/የቀደመ መብት በአዲስ አበባ እንዲሰጣቸው ይደነግጋል፡፡ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መብቶች” በሚል የኦሕዴድ መንግሥት በአዲስ አበባ አስተዳደር ላይ ስለሚኖረው ሥልጣን የተዘረዘሩት 5 ንዑስ አንቀጾችም የዚሁ የኦሕዴዶች ልዩ ጥቅም ማሳያ ናቸው፡፡

አዋጁ “የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባዔን” ያቋቁማል፡፡ ይህ ጉባዔ ዝርዝር ሥልጣኑ ሲታይ ከከተማዋ መስተዳደር ያነሰ አይመስልም፡፡ አንቀጽ 18/4 ለጉባዔው የአዲስ አበባን ከንቲባ የመምረጥ ሥልጣን በማጎናፀፍ ኦሕዴዶችን ጮቤ የሚያስረግጥ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ ጉባዔው ከአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት ጋር የጋራ ምክር ቤትም ይኖረዋል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ልዩ ጥቅሙን ያስጠብቃል፡፡ በተዘዋዋሪ የአዲስ አበባ መስተዳድር ተጠሪነቱ (በሕገ መንግሥቱ መሠረት) ለፌዴራል መንግሥቱ መሆኑ ይቀርና ለኦሕዴዱ የኦሮሚያ መንግሥት ይሆናል፡፡

2). የቀድሞዋ አዲስ አበባ፤ የወደፊቶቹ አዲስ አበባ እና ፊንፊኔ

“አስተዳደራዊ ጥቅሞች” በሚል በአንቀጽ 11 ሥር አስቀያሚ አንቀፆች ታጭቀዋል፡፡ ለምሳሌ አንቀጽ 11/1 “በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት ይኖራቸዋል” ይላል፡፡ ይህ በእውነቱ ምን ማለት እንደሆነ ራሱ ለመረዳት ያዳግታል፡፡ የከተማ ሕዝብ አሰፋፈር ተሰባጥሮ እንጂ በብሔር ተቧድኖ እንዳልሆነ የሚረዳ ሰው ያረቀቀውም አይመስልም፡፡ የራሳቸውን ዕድል የሚወስኑት ምን ለማድረግ ነው? በከተማው መስተዳደር አንታቀፍም እንገንጠል ብለው ነው? በቋንቋችን እንማር፣ ወይም እንዳኝ ብለው ነው? የትኛውንም ቢሆን ከከተማ ባሕሪ አንፃር በፍፁም ተፈፃሚ ሊሆን የማይችል፣ ለይስሙላ የተቀመጠ ነገር ግን በነዋሪዎች መካከል የውዝግብ መንስዔ ሊሆን የሚችል አንቀጽ ነው፡፡ ይፈፀም ከተባለ ደግሞ ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ፣ እንደ አፓርታይድ የኦሮሞ ተወላጆችን በአንድ አካባቢ በመሰብሰብ ሌሎቹን ደግሞ በሌላ ማድረግ የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል (በተራ ቁጥር 3 እንደሚዘረዘረው) የኦሮሞ ተወላጅ ነዋሪዎች ከሌሎች ተነጥለው ይሰጧቸው የተባሉት ጥቅማጥቅሞች ከተማዋን የሁለት ሕዝቦች ከተማ ለማድረግ ካልሆነ የሕዝቡን ጥያቄ አይመልስም፡፡

የኦሮሞ ተወላጆች በቋንቋቸው እንዲማሩ እና እንዲሠሩ ከተፈለገ ትምህርትና ሥራ በቋንቋው እንዲሰጡ ማድረግ እና አገልግሎቱን ማስፋፋት እንጂ በማይተገበር “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” አንቀጽ ሸብቦ መያዝ ማታለል ነው፡፡

3). “…አንዳንድ ሰዎች የበለጠ ዕኩል ናቸው”

“ስለማኅበራዊ የአገልግሎት ጥቅሞች” የሚዘረዝረው አንቀጽ 12 ዜጎች የተቃወሙትን የአዲስ አበባን ወደአጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች መስፋፋት የፈቀደ ይመስላል፡፡ አብዛኛዎቹ በዚህ ሥር የተዘረዘሩት ንዑስ አንቀፆች በኦሮሚያ የፊንፊኔ ዙሪያ አካባቢዎች የሚደረጉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች/ዝርጋታዎች በመስተዳድሩ ወጪ እንዲሆን ይደነግጋሉ፡፡ በእርግጥ አስፈፃሚው አልተጠቀሰም፡፡ በዚህ አንቀጽ ሥር አሳሳቢዎቹ ግን ንዑስ አንቀፅ 2 እና 3 ናቸው፡፡

አንቀጽ 12/2 “ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የኦሮሞ ተወላጆች የመኖሪያ ቤት በከተማ አስተዳደሩ ከሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በ15% ቅድሚያ የማግኘት ወይም የመከራየት መብት ይኖራቸዋል” ይላል፤ ቀጥሎም በአንቀጽ 12/3 ላይ ደግሞ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች አደባባዮች፣ ማዕከላት፣ አዳራሾች፣ ስታዲየሞች፣ ሜዳዎች…ወዘተ አገልግሎት ማግኘት ሲፈልጉ ቅድሚያ የመጠቀም ሙሉ መብት ይኖራቸዋል” ይላል፡፡ አንቀጾቹ ‹ሁሉም ሰዎች ዕኩል ናቸው፤ አንዳንዶች ግን የበለጠ ዕኩል ናቸው› የሚለውን የፖለቲካ ስላቅ ያስታውሳል፡፡ ኦሕዴዶች ለራሳቸው ምቾት በኦሮሞ ሕዝብ ሥም የጠየቁት ይሔ አንቀጽ አዲስ አበባ ውስጥ ሰዎች ሠርተው/ፈቅደው ባላገኙት ብሔራቸው የተለየ ክብር ወይም ውርደት እንዲቀበሉ ያስገድዳል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ በዚህ መልኩ ከፀደቀ በርግጥም ዝምተኛውን የአዲስ አበባ ሕዝብ ለአመፅ ይጋብዘዋል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡

ሌሎችም አመፅ ጋባዥ አንቀጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ “ስለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች” የሚያወራው አንቀጽ 14 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 “በከተማው የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከመሬታቸው ያለመፈናቀል ዋስትና እንዳላቸው” እና “ለልማት በተነሱበት አካባቢ በዘላቂነት የመቋቋም መብት አላቸው” ይላሉ፡፡ ይህ ዕድል/መብት የተሰጠው በከተማው ውስጥ ላሉ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ተነጥሎ ነው፡፡ ምናልባትም ከኦሮሞ ተወላጅ ጎረቤቱ ቀድሞ ኗሪ የነበረ የሌላ ብሔር ተወላጅ ከመሬቱ ሲፈናቀል ጎረቤቱ ግን በብሔረሰብ ግንዱ የተለየ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡

አንቀጽ 18/4 “ኦሮሞዎችን ወክለው የከተማ አስተዳደሩን የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች ከንቲባ እና ሌሎች የካቢኔ አባላትን ተጠቁመው በምክር ቤቱ እንዲጸድቅ ያስደርጋል” የሚል ግልጽ ያልሆነ ድንጋጌ አለው፡፡ ነገርዬው በጉባዔው አማካይነት ከንቲባነትን ለኦሮሞዎች ብቻ ለመገደብ የሚያስችል አንቀጽ ይመስላል፡፡

“ልዩ ጥቅም” ሲባል ይህንን የጠበቀ ሰው አልነበረም፡፡ ማንም ጤናማ አዕምሮ ያለው የሕግ ባለሙያ እንዲህ ዓይነት አዋጅ ያረቅቃል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብም ቢሆን ለሌሎች የተነፈገ መብት ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ አላቀረበም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን ረቂቅ ውድቅ የማድረግ ልምድ ስለሌለው ረቂቁ ፀድቆ አዋጅ የሆነ ዕለት ለሚከተለው ቀውስም አብሮ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

4) ድምፅ አልባው አዲስ አበቤ ይታዘባል

የከተማ ሕይወትን እምብዛም የማያውቁት ሕግ አውጪዎች ከአዲስ አበባ ውጪ አይቶ የማያውቀው ብዙኃን የአዲስ አበባ ነዋሪ ከተማውን የሚያይበትን መንገድ የተረዱ አይመስሉም፡፡ ነዋሪው ከአካባቢው ጋር ያለው ሥነ ልቦናዊ ትስስርም አልገባቸውም፡፡ ሕወሓት የ1997 ምርጫ ጫናን ተከትሎ፣ ከዚያ በፊት ስንት ሰዎች ሲጨፈለቁበት የኖሩበትን ጥያቄ ኦሕዴድን ተጠቅሞ በማፅደቅ የኦሮሚያ ዋና ከተማን ከአዳማ ወደ ፊንፊኔ አዙሮታል፡፡ ውሳኔው መልካም ቢመስልም በውጤቱ አዳማ ከተማ ብትጎዳም ኦሕዴዶች ተጠቅመው ይሆናል እንጂ የኦሮሞ ሕዝብ የተጠቀመው ነገር የለም፡፡ ዛሬም የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ ለማስቀየስ አዲስ አበባን የመስዋት በግ አድርጎ ማቅረብ የኦሮሞ ሕዝብን አይጠቅምም፤ የአዲስ አበባ ሕዝብን ግን ይጎዳ ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ በዘውግ ብሔርተኞች ፅንፍ መሐል እየታሸች ድምፅ አልባ ሆና መክረሟ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በገዛ ዕጣ ፈንታዋ ሌሎች እንዲወስኑ አዋጅ ይረቀቅባታል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ረቂቅ አዋጁ በጣም አሳፋሪ ጎኑ በአዲስ አበባ መስፋፋት ተፅዕኖ ሰለባ እየሆኑ ያሉትን የአጎራባች አካባቢዎች ጥቅም ዋነኛ የአዋጁ ዓላማ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ሕዝብን ከመጤፍም አለመቁጠሩ ነው፡፡

አዲስ አበባ የሁሉም ነዋሪዎቿ እንደመሆኗ በዕጣ ፈንታዋ የመወሰን ዕድሉም የሁሉም አዲስ አበቤ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ አጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች የተፅዕኖው ሰለባ መሆናቸውን ለመረዳት አይከብደውም፡፡ ሚዛናዊ “ልዩ ተጠቃሚነታቸውንም” አይቃወምም፡፡ እንደ አንድ አዲስ አበቤ ግን የከተማዋ ነዋሪዎች በኦሮሞ ሕዝብ ሥም ለተራ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ ለመሆን የሚፈቅድ ነዋሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ዝምታ ድንቁርና አይደለም፤ ይታሰብበት፡፡

Share this post

One thought on “የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ምንድን ነው? በፈቃዱ ዘኃይሉ

 1. ይህ አዋጅ በልማታዊ ካድሬዎች የተፃፈ እንጂ በሕግ ባለሙያ ስላልተሰራ ዓላማው ነፍጠኞች ምን አሉ ? ተበዳይ/ተገንጣዮች እንዴት ቦረቁ? ብልጦች የያዙትን ይዘው እንዴት ያለቅሳሉ ?ድምፅ አጥፊዎችስ አስቸኳይ /ፈጣኑ አዋጅ ሲነሳ(ከተነሳ?) ከልዩ ጥቅማጥቅም ሰጪነት ህወሓት የነባር ሜጫና ቱለማ ግዛት ይውጣ!ከተባለስ ?
  **ገና የውጭ ቋንቋ ስያሜ ያላቸው የህወሓት ድርጅቶች ሱቆች ማናቸውም የታጋይ መንደሮች ሁሉ የኦሮሞ ሥም መሠጠትም አለበት ።
  **ኃይለመለስ በሱዳንና በአፋር/አሰብ ለህወሓት የባቡር መስመር ማሰቡ ፡ ስብሃት ነጋ የኢፈርትን ገንዘብ ምንጭና መድረሻ የሚጠይቅ እብድ እንጂ ሰው (የተማረ) የለም ማለቱ በእውነቱ ኦህዴድ በዚህ ቻርተር ሻንጣ ተሸካሚነቱን አስመሰከረ ደህዴን ዜጎች በሱዳን ሌባ ሲያስገድል ሲያዘርፍ ከአድዋ ድል መልስ አዲስ አበባ ይርጋ የተሰጣቸውን የደቡብ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ዜጎቹን ያለ ጥቅማ ጥቅም ሸጡ ?። ብአዴን ድሮም የአማራ ጠላት እንጂ አማራ መሰል/አማሳይ ስለሆነ የመጀመሪያው እውቅና ሰጭ ነው ከጋምቤላ ጎንደር ለሱዳን የሸጠ ምንደኛ ራስ ዳሸን ተራራ ትግራየገፋ፡ ወልቃይትን ሁመራን አላማጣን ከባሕር ወደብ ጋር የሸቀለ ለሸዋ መዲና አራዳ ይጨነቃል ??

  የጫካው ማኒፌስቶ የከተማው ሕገመንግሥታዊ ልዩ ጥቅም !?
  “ኧረ ማነው ሰጪ ማነውስ ከልካይ
  ሰው እንዳሻው ቢኖር በሀገሩ ላይ ?
  ******
  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች አደባባዮች፣
  ማዕከላት፣ አዳራሾች፣ ስታዲየሞች፣ ሜዳዎች…ወዘተ አገልግሎት ማግኘት ሲፈልጉ
  ቅድሚያ የመጠቀም ሙሉ መብት ይኖራቸዋል።……..
  *** የመፃፍ የመጠየቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሳያሳውቁና ሳያስፈቅዱ ከኤርትራውያን ስደተኞች ቀጥሎ/እኩል መብት ተሰጣቸው ? በእርግጥ ይህ ንቀትና ስድብ የተመፅዋችነት ማዕረግ ነው ።ለመሆኑ ከኦሮምያ ክልላዊ ሠፈር የሚኖሩት ተመሳሳይ መብት አላቸውን?ሕገመንግሥቱ የአዲስ አበባን ተወላጅ፡ከሁለትና ከሶስት ነገድ የተወለዱ፡ከጎሳቸው ውጭ ተዋልደው ሀብት አፍርተው የሚኖሩትን በየትኛው አንቀጾች እና ልዩ ድንጋጌ መብታቸው ተከበረ ተቀበረ እንጂ!? ።
  *** ይህ ቻርተር ከአውስትራሊያ ፡አሜሪካ፡ ካናዳ “ሬድ ኢንዲያን አክት ” ቃል በቃል ነጥብ ሳይቀር የተገለበጠ “የሜጫና ቱለማ አክት” ወይም የቅኝ ተገዢ መብት በእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች የተሰጠ የእከክልኝ ልከክልህ የማኒፌስቶ ልዩ ጥቅማጥቅም ተብሎ ያሳዝናል ኦሮሞ ይህን ያህል የወረደው በምን ቢገመት ነው ? ዘይገርም!

  አዲስ አበባ በዘውግ ብሔርተኞች ፅንፍ መሐል እየታሸች ድምፅ አልባ ሆና መክረሟ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በገዛ ዕጣ ፈንታዋ ሌሎች እንዲወስኑ አዋጅ ይረቀቅባታል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ረቂቅ አዋጁ በጣም አሳፋሪ ጎኑ በአዲስ አበባ መስፋፋት ተፅዕኖ ሰለባ እየሆኑ ያሉትን የአጎራባች አካባቢዎች ጥቅም ዋነኛ የአዋጁ ዓላማ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ሕዝብን ከመጤፍም አለመቁጠሩ ነው፡፡

  ***”አዲስ አበባ የሁሉም ነዋሪዎቿ እንደመሆኗ በዕጣ ፈንታዋ የመወሰን ዕድሉም የሁሉም አዲስ አበቤ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ አጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች የተፅዕኖው ሰለባ መሆናቸውን ለመረዳት አይከብደውም፡፡ ሚዛናዊ “ልዩ ተጠቃሚነታቸውንም” አይቃወምም፡፡ እንደ አንድ አዲስ አበቤ ግን የከተማዋ ነዋሪዎች በኦሮሞ ሕዝብ ሥም ለተራ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ ለመሆን የሚፈቅድ ነዋሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ዝምታ ድንቁርና አይደለም፤ ይታሰብበት!፡፡አራት ነጥብ ።

  Reply

Post Comment