የሶማሊ ክልል የመብት ተሟጋቾች እየተካሄደ ባለው የሶህዴፓ ግምገማ ደስተኞች እንዳልሆኑ እየገለጹ ነው

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%88%B6%E1%88%9B%E1%88%8A-%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B5-%E1%89%B0%E1%88%9F%E1%8C%8B%E1%89%BE%E1%89%BD-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%88%84/

የሶማሊ ክልል የመብት ተሟጋቾች እየተካሄደ ባለው የሶህዴፓ ግምገማ ደስተኞች እንዳልሆኑ እየገለጹ ነው
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ/ም ) ክልሉን ለረጅም ጊዜ ሲያስተዳድር የነበረው ሶህዴፓ፣ በሊቀመንበሩ በአቶ አብዲ ሺዴ አማካኝነት ግምገማ እያካሄደ ቢሆንም፣ የመብት ተሟጋች የክልሉ ተወላጆች እንደሚሉት ግን በክልሉ መሰረታዊ የሆነ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ፍላጎት ይኖራል ብለው ለማመን እየተቸገሩ ነው።
የሶህዴፓ አመራሮች እና አባላት በግምገማው ወቅት እጅግ በርካታ ወንጀሎችን ዘርዝረው ያቀረቡ ቢሆንም፣ በወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑ ክልሉን በጊዚያዊነት የሚመሩትን ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት በተሃድሶ ስም መልሶ ወደ ስልጣን ለማምጣት የሚደረገው ሩጫ በክልሉ ውስጥ የህዝብ ጥያቄ የሚመልስ ለውጥ የመጣል ብለው ተስፋ እንዳያደርጉ አድርጓቸዋል።
በግምገማው ወቅት፣ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ሴቶች በቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ እርሱን ከላይ ሆነው ያዝዙ በነበሩ የህወሃት ባለስልጣናት እና አብዲ ኢሌ በሾማቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲደፈሩ እንደነበሩ መናገራቸው ታውቋል። የክልሉን ሃብት በአብዲ ኢሌና ሸሪኮቹ ቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ፣ ዜጎችን በፈለጉት ጊዜ የማሰርና የመግደል እርምጃ ይወሰድ እንደነበርም በዚሁ ግምገማ ወቅት ተነስቷል።
የመብት ተሟጋቾች እንዲሚሉት በቅርቡ በኦሮሞ፣ አማራና ሌሎችም ብሄር ተወላጆች ላይ ግድያ እንዲፈጸም ፣ ቤተክርስቲያኖች እንዲቃጠሉና ሌሎችም ህዝብን ከህዝብ የሚጋጩ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በይፋ በማህበራዊ ሚዲያ ትዕዛዝ ሲሰጡ የነበሩት የአሁኑ የክልሉ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ መደረጋቸው፣ የክልሉ ባለስልጣናት እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት ተዘጋጅተዋል ወይ ብለው እንዲጠይቁ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ 3 የስራ አስፈጻሚ አባላትና የክልሉን አፈ ጉባኤ ጨምሮ 5 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ከስልጣን ማንሳቱ የተገለጸ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ በስልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች አብዲ ኢሌ ሹሞ ያሳደጋቸው ሰዎች በመሆናቸው እና በግምገማ ስም ወደ ስልጣን ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ደስተኞች እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
በክልሉ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ ተንኮታኩቷል የሚሉት የመብት ተሟጋቾች፣ መንግስት በውድ ዋጋ የገዛቸው ቪ 8 የሚባሉ ዘመናዊ መኪኖች፣ የተለያዩ ማሽነሪዎች፣ የቢሮ ወንበሮችና ዋጋ ያወጣሉ የተባሉ እቃዎች ሁሉ ወደ ሶማሊያ፣ ጁባ ላንድና ወደ ሶማሊላንድ እየተወሰዱ በመሸጥ ላይ ናቸው። የመንግስት ሰራተኞች ያለፉትን ሁለት ወራት ደሞዝ አልተከፈላቸውም። በፊት በአንድ ግለሰብ ላይ ተንጠልጥሎ የተመሰረተው ስርዓት አሁን ሙሉ በሙሉ የለም በሚባልበት ደረጃ ደርሷል የሚሉት የመብት ተሟጋቾች፣ መንግስት ሁሉንም የክልሉን ተወላጆች ባሳተፈ መልኩ ውይይት አካሂዶ፣ ለክልሉ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንዳለበት መክረዋል።
በሌላ በኩል ታዋቂዎቹ የሶማሊ ክልል የመብት ተሟጋቾች አቶ ጀማል ድሪዬ ካሊፍና አብዱሂ ሁሴን ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ። የአብዲ ኢሌን አገዛዝ ለረጅ ጊዜ በጽናት ሲታገሉ የነበሩት አቶ ጀማል ነገ አዲስ አበባ ሲገቡ ፣ ከተለያዩ የክልሉ ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር በክልሉ የተሻለ አስተዳደር እንዲፈጠር የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ለኢሳት ተናግረዋል። የተለያዩ የቪዲዮ ማስረጃዎችን ይዞ በመውጣት የአብዲ ኢሌ አገዛዝ በአለማቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ እንዲታወቅ ያደረገውና በስዊድን አገር ሆኖ የመብት ትግል ሲያካሂድ የቆየው አብዱላሂ ሁሴንም እንዲሁ ነገ አዲስ አበባ ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ መከላከያ ሰራዊት በአንድ አባሉ ላይ የግድያ እርምጃ ከተወሰደበት በሁዋላ፣ በአካባቢው ታጣቂዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰዱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ይህን ተከትሎ በአካባቢው በሰላም መንቀሳቀስ መቻሉን ምንጮች ገልጸዋል።
የአብዲ ኢሌ ታጣቂዎች ወደ ሶማሊላንድ ለመግባት ሙከራ ቢያደርጉም፣ የሶማሊ ላንድ መንግስት ወደ አገሩ ለማስገባት ፈቃደኛ አለመሆኑን ገልጸዋል። የሶማሊላንድ መንግስት አገራችሁን አተራምሳችሁ እኛንም እንድታተራምሱን አንፈቅድም ማለታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

The post የሶማሊ ክልል የመብት ተሟጋቾች እየተካሄደ ባለው የሶህዴፓ ግምገማ ደስተኞች እንዳልሆኑ እየገለጹ ነው appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

One thought on “የሶማሊ ክልል የመብት ተሟጋቾች እየተካሄደ ባለው የሶህዴፓ ግምገማ ደስተኞች እንዳልሆኑ እየገለጹ ነው

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.