የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ ተመረቀ

የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ ምረቃ ስነ ስርዓት በዛሬው ተካሂዷል።

በፓርኩ ምረቃ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በፓርኩ ምርቃት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፥ ለመላው ኢትዮጵያውያን የመልካም በዓል ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አክለውም፥ ኢትዮጵያውያን አልፎም አፍሪካውያን የሚኮሩባት አዲስ አበባ እንዲህ አይነት ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተገነቡት ፓርኮች የሀገሪቱን እና የከተማዋን ገፅታ ከመገንባት በዘለለ በትብብር ከሰራን ምን አይነት ለውጥ ማምጣት እንደመንችል ህያው ምስክር ነው ብለዋል።

ሀገራችንን የማስዋብ ጥረታችንን ከሌሎች የልማት ጥረቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ካስኬድነው በአጭር ጊዜ የአገራችንን ገፅታ መቀየር እንችላለን ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል።

ፓርኩ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ለበርካታ ቤተሰቦችም መተዳደሪያ ሊሆን የቻለ ነው ብለዋል።

ከዚህ ፓርክ በመነሳት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪዎች በቅንጅት በመሆን ሌሎች አነስተኛ ፓርኮችን ማልማት ላይ ሊሰሩ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በንግግራቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የፓርኩን ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ስራውን ከስር ከሰር በመከታተል እና አመራር በመስጠት ፓርኩ ለኢትዮጵያውያን የአዲስ አበባ የአዲስ ዓመት ስጦታ እንዲሆን በማድረጋቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሸገር ፓርክ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይም ለፓርኩ መገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በተለይም ለቻይና መንግስት እና ለሌሎች አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በቻይና መንግስት ድጋፍ የሚከናወነው እና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው ይህ የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ መስከረም 20 ቀን 2012 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት መጀመሩ የሚታወስ ነው።

ደዋጅነት አደባባይ የሚል ስያሜ የተሰጠው ፓርኩ ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

በፕሮጀክቱ አምስት ግዙፍ ማዕከላት ያካተተ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት የስብሰባ፣ የጥበብ ማቅረቢያ ስፍራ፣ የህፃናት መዝናኛ ማዕከል እና የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ያካተተ ነው።

በሙለታ መንገሻ

The post የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ ተመረቀ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply