የሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል በዓል በክልል ደረጃ በባህርዳር ከተማ የፊታችን እሁድ እና ሰኞ ይከበራል

Source: https://fanabc.com/2019/08/%E1%8B%A8%E1%88%BB%E1%8B%B0%E1%8B%AD%E1%8D%A3-%E1%8A%A0%E1%88%B8%E1%8A%95%E1%8B%B5%E1%8B%A8-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%88%B6%E1%88%88%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%8B%93%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%8A%AD%E1%88%8D/

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 13 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የሻደይ፣ አሸንድየ እና ሶለል በዓል በክልል ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ በባህርዳር ከተማ የፊታችን እሁድ እና ሰኞ ይከበራል።

በዓሉ ከወዲሁ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከነሃሴ 16 እስከ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚከበር ሲሆን፥ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቁን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በባህርዳር ለሚከበረው የበዓሉ ማጠቃለያ መርሀ ግብር ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የባህል አምባሳደሮች ይገኛሉ።

በበዓሉ ላይ ከ700 በላይ የሚሆኑ ልጃገረዶችም የባህል ጨዋታ እንደሚያቀርቡም ነው አቶ መልካሙ የተናገሩት።

በአጠቃላይ ባህርዳር ላይ ለሚከናወነው ክብረ በዓልም ከ50 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ለክብረ በዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበልም በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው የተባለው።

አቶ መልካሙ እንዳሉት ባህላዊ ጨዋታውን “የኢትዮጵያ ልጃገረዶች ጨዋታ” በሚል በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከትግራይ ክልል ጋር እየተሰራ ነው።

ከዚህ ባለፈም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ጥናቶች እና መረጃዎች ተሰብስበው ለቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን መላካቸውንም ጠቅሰዋል።

 

 

በዙፋን ካሳሁን

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.