የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ያረጋል አይሸሹም የቀብር ስነ ሥርዓት ዛሬ ተፈጸመ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%8B%A8%E1%89%80%E1%8B%B5%E1%88%9E%E1%8B%8D-%E1%8B%A8%E1%89%A4%E1%8A%92%E1%88%BB%E1%8A%95%E1%8C%89%E1%88%8D-%E1%8C%89%E1%88%9D%E1%8B%9D-%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%88%AD%E1%8B%95%E1%88%B0/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ያረጋል አይሸሹም የቀብር ስነ ሥርዓት ዛሬ ተፈጸመ፡፡

የቀብር ስነ-ስርዓታቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው በተገኙበት በአዲስ አበባ ጴጥሮስ ወጳውሎስ የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር ተፈጽሟል።

የአቶ ያረጋል አስከሬን ሲኤምሲ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፖሊስ ማርሽ ባንድ ታጅቦ አሸኛኘት የተደረገለት ሲሆን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አሻድሌ ሐሰንን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።
በፕሮቴስታንት ኃይማኖት ስርዓት መሰረትም ጸሎት ተደርጎ የቀብር ሥነ-ስርዓታቸው ተፈጽሟል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የተለያዩ የክልልና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አሻሌ ሐሰን አቶ ያረጋል አይሸሹም ክልሉን በኃላፊነት በመሩበት ወቅት ከኋላቀርነትና ከድህነት ለማላቀቅና ሁለንተናዊ እድገት ለማስመዝገብ በከፍተኛ ሃላፊነትና ቁርጠኝነት መስራታቸውን ተናግረዋል።

ክልሉ ያለበትን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታትና የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም ግብርናውን በማሻሻል ረገድ እውቀትና ጉልበታቸውን ሳይሳሱ በርካታ ስራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ክልሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተስማምተው ተፋቅረውና ተከባብረውና በእኩልነት እንዲኖሩ ኃላፊነታቸውን ስለመወጣታቸውም ምስክርነት ሰጥተዋል።

አቶ ያረጋል ከአባታቸው ከአቶ አይሸሹም ብርሃኔና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሽታዬ ይማም በ1961 ዓ.ም በድባጤ ከተማ ነው የተወለዱት።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በድባጤ ሚሽን ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን በቻግኒ ተከታትለዋል።

በኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላም በቀድሞው ባሌ ክፍለሃገር በመምህርነት ማገልገላቸው በተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ተጠቅሷል።

በክልሉ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት የሰሩት አቶ ያረጋል በተለይ ከ1987 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የክልሉ አራተኛው ርዕሰ መስተዳድር ሆነው አገልግለዋል።

አቶ ያረጋል ከ2002 እስከ 2007 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም ደሞ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል።

አቶ ያረጋል በተወለዱ በ50 ዓመታቸው ሕዳር 8 ቀን 2012 ዓ.ም በድንገተኛ ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

አቶ ያረጋል የአንድ ሴትና የሶስት ወንድ ልጆች አባት እደነበሩ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.