የቋሚ ሲኖዶስ – የኮሮና ቫይረስ መከላከል ውሳኔ: የአፈጻጸም ማብራሪያ እየተዘጋጀለት ነው

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2020/04/02/%E1%8B%A8%E1%89%8B%E1%88%9A-%E1%88%B2%E1%8A%96%E1%8B%B6%E1%88%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%AE%E1%88%AE%E1%8A%93-%E1%89%AB%E1%8B%AD%E1%88%A8%E1%88%B5-%E1%88%98%E1%8A%A8%E1%88%8B%E1%8A%A8%E1%88%8D-%E1%8B%8D/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2020/04/3421.jpg
  • ማብራሪያውን ከማስገንዘብ በኋላ፣ ጠንካራ የአፈጻጸም ክትትል ይደረጋል፤
  • ከውጭ ሀገራት የገቡ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በለይቶ ማቆያ ይገኛሉ፤
  • ከቦሌ በቀጥታ ወደ ማረፊያቸው በሔዱት አባት ጉዳይ ማጣራቱ ቀጥሏል፤
  • ምግባረ ሠናይ ሆስፒታል ለተመላሽ አባቶች ለይቶ ማቆያ ተጠቁሞ ነበር፤

***

3421

ዓለም አቀፉን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት እና የኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል፣ ቋሚ ሲኖዶስ ትላንት ያሳለፋቸው የጥንቃቄ ውሳኔዎች፣ የአፈጻጸም ዝርዝር/ማብራሪያ/ እየተዘጋጀላቸው እንደኾነ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ገለጹ፡፡

በሰዎች መሰባሰብ እና ንክኪ የሚስፋፋውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ ትላንት መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ፣ ባለአምስት አናቅጽ የጥንቃቄ ውሳኔዎችንና ድጋፎችን የያዘ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ከእኒኽም ውስጥ፣ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር የሚቆዩ እና በቤተ መቅደሱ መንፈሳዊ አገልግሎቱን የሚፈጽሙ ካህናት፣ በጣም ውስን መኾን እንዳለባቸው፣ ሌሎች ካህናት እና ምእመናን ግን፣ ለጊዜው በየቤታቸው በጸሎት እንዲወሰኑ የሚያዝዘው ይገኝበታል፡፡

ከምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንና ወቅታዊ ከኾኑ ሌሎች አገልግሎቶች አፈጻጸም አኳያ፣ “ውሳኔው የተፍታታ ማብራሪያ አልሰጠም” በማለት ከአገልጋዮች እና ምእመናን እየተነሡ ስላሉ ጥያቄዎች፣ ሸገር ኤፍ.ኤም ራዲዮ 102.1 በስልክ ያነጋገራቸው ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ዝርዝር ማብራሪያ የሚያዘጋጅ ልኡክ ተሠይሞ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

“ወረርሽኙ ከሚያመጣው አበሳ ለመጠበቅ፣ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ የሚሰበሰበውን ሰው ቁጥር መቀነስ፣ አልፎም መገደብ ግድ የሚልበት ወቅት መጥቷል፤” ያሉት ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ ከውሳኔው ዝርዝር አፈጻጸም አኳያ፣ ጉዳዩ ይበልጥ የሚመለከታቸው መክረው ለውሳኔ እንዲያቀርቡ ሥራ እንደ ተሰጣቸውና የተደረሰበትን ዝርዝር ውሳኔም በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ እንደሚያሳውቅ ለሸገር ኤፍ.ኤም ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ሥርዓትን የማሻሻል ሥልጣን እንዳለውና በዚህ ረገድ የሚያሳልፈውን ውሳኔም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ እና ምእመን የኾነ ወገን፣ ለመረዳት መጠየቅ እና መፈጸም እንጂ መቃወም እና አፈጻጸሙን ማስታጎል እንደማይችል፣ ቋሚ ሲኖዶስ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ትላንት ያሳለፈውን የጥንቃቄ ውሳኔ አስመልክቶ፣ ከኢኦተቤ-ቴቪ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሳስበዋል፡፡

Quwami Synod COVID Restriction

በተያያዘም፣ የካህናት እና የምእመናንን ቁጥር ከመወሰኑ ውጭ፥ የሚቋረጥ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት እንደማይኖር፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ለኢኦተቤ-ቴቪ ገልጿል፡፡

ከወረርሽኙ አደገኛነት አንጻር ለጥንቃቄ የተወሰነ ሲኖዶሳዊ ውሳኔ በመኾኑ፣ በኹሉም የቤተ ክርስቲያን አካላትና አባላት ዘንድ መፈጸም ይኖርበታል፤ ያሉት የመምሪያው ዋና ሓላፊ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ፣ ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ለተባሉ የውሳኔው ነጥቦች፣ ብፁዓን አባቶች እና ሊቃውንት ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጡና ይህም በቤተ ክርስቲያን ሚዲያዎች እንደሚገለጽ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውጭ፣ ከቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የተነሣ፥ ቤተ ክርስቲያን እንደተዘጋች፣ ጥምቀት፣ ቊርባንና ፍትሐት እንደተከለከለ ተደርጎ የሚናፈሰው አረዳድ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው፤ ብለዋል፡፡

የውሳኔው ማብራሪያ ከተዘጋጀ እና በስፋት የማስገንዘብ ሥራ ከተሠራ በኋላ፣ በየደረጃው በተቋቋመው ግብረ ኃይል አማካይነት ጠንካራ የአፈጻጸም ክትትል ይደረጋል፤ ወረርሽኙን ለማስቆም የተላለፈውን ውሳኔ በማይፈጽሙት እና ለአፈጻጸሙ ዕንቅፋት በሚኾኑ ሓላፊዎች፣ ሠራተኞች እና አገልጋዮች ላይ፣ ከአስተዳደራዊ እስከ ቀኖናዊ ርምጃ እንደሚወሰድም ተመልክቷል፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ለካህናት እና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል፣ ባለፈው መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው መግለጫ፥ ሥርዐተ ቅዳሴን ጨምሮ እንደ ስብሐተ ነግህ፣ ሰዓታት፣ ማሕሌት፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት የመሳሰሉት፣ ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና በውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈጸም ወስኗል፡፡

በዕለት የሚቆርቡ ምእመናን ብቻ ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፤ በጸሎት እና በሕክምና በቤት የሚቆዩ ሕሙማንም፣ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት በልዩ ኹኔታ እንዲያገኙ አዟል፡፡ አክሎም፣ ከቅዳሴ ጋራ የተያያዙ ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮች፣ በግብረ ኃይሉ ተዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚላከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን፣ በበላይነት የመምራት እና የመቆጣጠር ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚፈቅደው መሠረት፣ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፥ የማውጣት፣ የማሻሻል እና የመሻር ሥልጣን አለው፡፡ ቋሚ ሲኖዶስ፣ ከቅዱስ ሲኖዶሱ አካላት አንዱ ሲኾን፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቁ ሕግጋት፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ውሳኔዎች፣ በሥራ ላይ መተርጎማቸውን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፡፡

በሌላ በኩል፣ ከተለያዩ የውጭ አገሮች፣ በልዩ ልዩ ቀናት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንደሚገኙ ተጠቆመ፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል እንደተመለሱ የተጠቆመ ሲኾን፣ በደርዘን ከሚቆጠሩ ሌሎች መነኰሳት እና ካህናት እንዲሁም መምህራንና አገልጋዮች ጋራ፣ ለ14 ቀናት ለይቶ ማቆያ በተወሰኑት የስካይ ላይት እና ግዮን ሆቴሎች፣ የጥንቃቄ ቆይታ ጊዜአቸውን በመፈጸም ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ከሦስቱ ብፁዓን አባቶች መካከል፣ ትላንት ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ፣ በቀጥታ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያቸው ደርሰው ብዙም ሳይቆዩ የተመለሱት ብፁዕ አባት ይገኙበታል፡፡ “ከቤት የምይዘው ዕቃ ስላለ ነው፤” በማለት በሕክምና ባለሞያዎች እና በአየር መንገዱ ሰዎች ታጅበው እንደ መጡና ወዲያው ከማረፊያቸው ይዘዋቸው ወደ ለይቶ ማቆያው እንዳስገቧቸው ተገልጿል፡፡

በአገራችን የወረርሽኙ ተጠቂዎች ይዞታ፣ በአመዛኙ የተጓዥነት ታሪክ ካላቸው ጋራ በመያያዙ፣ እኒህ ብፁዕ አባት፣ ከአየር ማረፊያው በቀጥታ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ እንዲገቡ የተፈቀደበት ኹኔታ፣ ከትላንት ማምሻውን ጀምሮ ብዙዎችን እያነጋገረና እያጠያየቀ ይገኛል፡፡ በአየር መንገዱ መኪና ከአየር መንገዱ ሰዎች እና የሕክምና ባለሞያዎች ጋራ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ማረፊያቸው መምጣታቸውን የጠቀሰው ሙሐዘ ጥበባት ዲን. ዳንኤል ክብረት፣ የአየር መንገድ ሰዎች ማን ሥልጣን ሰጣቸው? ሐኪሙስ እንዴት ተባበረ? የጸጥታ አካላትስ እንዴት አሳለፉ? መኪናውንስ ማን ፈቀደ?” በሚሉ በርካታ ጥያቄዎች መነሻነት ማጣራት እየተካሔደ እንደ ኾነ በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል፡፡

አዎ፥ ጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ፣ ቅዱስነታቸውን ጨምሮ በዕድሜም የገፉ በርካታ ብፁዓን አባቶች የሚኖሩበት እንደመኾኑ፣ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቀላሉ ተጋላጭ እንዳይኾኑ የተጠናከረ ጥበቃ እና ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ወረርሽኙ እስኪገታ ድረስ፣ በቀጣይ ከውጭ ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ብፁዓን አባቶችም፣ እንደ ምግባረ ሠናይ ሆስፒታል ያሉትን ምቹ ቦታዎቿን፣ ቤተ ክርስቲያን በራሷ እንድታዘጋጅ በሚመለከተው አካል የተጠየቀችውንም ልታጤነው ትችላለች፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.