የበሬ ስጋ እየበላህ የአህያን ስጋ መከልከል አትችልም

Source: http://hornaffairs.com/am/2017/04/03/commentary-donkey-meat-commerce/

“አህያ!” – “ደደብ፥ ደነዝ፥ የማይገባው” ለማለት፣ “በቅሎ አባትሽ ማን ነው ቢሏት አጎቴ ፈረስ ነው አለች” – ለአህያ ያለንን ዝግተኛ ግምት ያሳያል፣ “አህያ ሰባ ምን ሊረባ” – የአህያ ሥጋ እንደማይበላ ይጠቁማል፣ …ወዘተ። እድሜ ለአለም አቀፉ የገበያ ትስስር (Globalization)፣ በሀገራችን ክብር የተነፈጋት እና ዝቅተኛ ግምት የመሚሰጣትን አህያ የሚፈልግ እንግዳ ከሩቅ ምስራቅ ድረስ መጥቷል። የአህያን ሥጋ ቬትናሞች ለምግብ፣ ቻይናዎች ደግሞ ቆዳዋን ለመድሃኒት በጥብቅ እየፈለጉት እንደሆነ ሰሞኑን ተሰምቷል። ስለዚህ፣ እኛ የማንፈልገውን ፈልጎ ደጃፋችን ድረስ የመጣን እንግዳ በአግባቡ ማስተናገድ እንጂ ሌላ ሁኻታ መፍጠር ተገቢ አይመስለኝም።

በመጀመሪያ ደረጃ ነገሩ ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም-አቀፋዊና አህጉራዊ ጭምር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። በእርግጥ የአህያ ሥጋ ከቬትናም በተጨማሪ በቻይና እና አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ለምግብነት እንደሚውል ይታወቃል። ነገር ግን፣ አህያን በጣም ተፈላጊ ያደረጋት ከሥጋዋ ይልቅ ቆዳዋ ነው። በቻይና የአህያ ቆዳ በጣም ተፈላጊ ነው። ምክንያቱም፣ ቻይናዊያን የአህያን ቆዳ በመቀቀል ከውስጡ ¨gelatine” የተባለ ንጥረ ነገር የሚያመርቱ ሲሆን ይህ ደግሞ ”Ejiao” ለተባለው የቻይና ባህላዊ መድሃኒት ዋና ግብዓት ሆኖ ያገለግላል።

በቻይና የአህያ ቆዳ ተፈላጊነት እንዲጨምር ያደረገው መካከለኛ ገቢ ያላቸው የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩና ስለ ”Ejiao” ፍቱን መድሃኒትነት በሚቀርቡ የማስታወቂያ ሥራዎች እንደሆኑ ዘገባዎች ያስረዳሉ። ዛሬ በቻይና አንድ ኪሎ ግራም “Ejiao” እስከ £300 ፓውንድ በሚደርስ ዋጋ ይሸጣል። በዚህ ምክንያት በቻይና የአህያ ቁጥር እ.አ.አ. በ1991 ከነበረበት በእጥፍ መቀነሱን ዘገባዎች ያስረዳሉ። በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥም ከፍተኛ የሆነ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ተፈጥሯል። ለዓለም ገበያ በአንድ አመት ውስጥ 1.8 ሚሊዮን የአህያ ቆዳ ለሽያጭ የሚቀርብ ሲሆን ዓመታዊ የገበያ ፍላጎቱ ግን 4 እስከ 10 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል።

Photo - A donkeyPhoto – A donkey

የአህያ ቆዳ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት፣ ለምሳሌ በቡርኪና ፋሶ የአንድ አህያ የመሸጫ ዋጋ እ.አ.አ. 2014 ከነበረበት 60 ዶላር ወደ 108 ዶላር ጨምሯል። እንደ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካና ታንዛኒያ ባሉ ሀገራት ደግሞ አህዮችን ለቆዳቸው ሲባል በሕገወጥ መንገድ መስረቅና በየስርቻው ማረድ እንደተጀመረ አንዳንድ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። በአህያ ብዛት በአፍሪካ ቀዳሚ በሆኑት ኬኒያና ኢትዮጲያ ደግሞ በመንግስት እውቅና የተሰጠው የአህያ ማረጃ “ቄራ” ተከፍቷል።

ሰሞኑን ከወደ ቢሾፍቱ (ደብረዘይት)የተሰማው ዜና ከላይ የተጠቀሰው አለም አቀፋዊና አህጉራዊ እውነታ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በዘገባው መሰረት፣ በቢሾፍቱ ከተማ በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ “የአህያ ቀራ” መገንባቱ እና የአህያ ስጋና ቆዳን ወደ ዉጪ መላክ ሊጀመር እንደሆነ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሌላ የአህያ ቄራ በኦሮሚያ ክልል፥ አርሲ ዞን፥ አሰላ አከባቢ በቻይናዊያን ባለሃብቶች እየተገነባ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ከላይ የተጠቀሰው ዜና ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ ሰንብቷል። “የአህያ ስጋና ቆዳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በሀገራችን ሊከፈት አይገባም”፣ “ፋብሪካው እንዲከፈት በመፍቀድ መንግስት የሀገሪቱን ሞራላዊ እሴት ጥሷል” እና የመሳሰሉት ዓይነት አስተያየቶች በስፋት እየተደመጡ ይገኛል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ከጥቂት ወራት በፊት በቢሾፍቱ የተገነባው ፋብሪካ የዚህ ዓይነት አመለካከት ባላቸው ሰዎች በእሳት ተለኩሶ እንደነበር ዘገባዎች ያስረዳሉ።

በእርግጥ የአህያ ስጋን አለመብላት መብት ነው። ሌሎች ሰዎች እንዳይበሉ መከልከል ግን ወንጀል ነው። በዚህ መሰረት፣ ከላይ የተጠቀሰው ድርጅት የተቋቋመበትን ዓላማና ተግባር እንዳያከናውን እንቅፋት መሆን ከሞራልና ኢኮኖሚያዊ መርህ አንፃር ተቀባይነት የለውም። ለዚህ ደግሞ ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።

1ኛ) የጅብ ቆዳን እየገዛን የአህያ ቆዳ እንዳይሸጥ መከልከል

የአህያ ቆዳ በቻይና ተፈላጊ የሆነበት ምክንያት ለባህላዊ መድሃኒት ማምረቻ ግብዓት ሆኖ ስለሚያገለግል ነው። በቢሾፍቱ ከተማ የተቋቋመው ድርጅትም የአህያ ቆዳን ለዚሁ ገበያ የማቅረብ ዓላማ እንዳለው ተገልጿል። በተመሣሣይ፣ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች የጅብ ቆዳ እና የጃርት ስጋ ለባህላዊ መድሃኒት እንደሚውሉ ይታወቃል። ስለዚህ፣ እኛ በሀገራችን የጅብ ቆዳን ለባህላዊ መድሃኒትነት እየተጠቀምን ቻይናዎች የአህያ ቆዳ ለተመሣሣይ ዓላማ እንዳያውሉ መከልከል በፍፁም አግባብ ሊሆን አይችልም።

2ኛ) የበሬ ስጋን የሚበላ የአህያ ስጋን መከልከል አይችልም

ኢትዮጲያ ውስጥ የበግና የበሬ ስጋ ተወዳጅ እንደሆነ ሁሉ ቬትናም ውስጥ የአህያ ስጋ ተወዳጅ ነው። በቢሾፍቱ የተቋቋመው ድርጅትም የአህያ ስጋን ለሀገር ውስጥ ገበያ ሳይሆን ለቬትናም ገበያ የሚያቀርብ ነው። የገና እና ኢድ በዓል በመጣ ቁጥር በሬና በግ በየመንገዱና በየሰፈሩ የሚያርድ ማህብረሰብ ዘመናዊ የአህያ ቄራ በመቋቋሙ ምክንያት የሚያጣው ነገር ምንድነው?

እውነት ለመነጋገር፣ እስኪ በየከተማው ያሉ ሥጋ (ሉካንዳ) ቤቶችን ልብ ብላችሁ ተመልከቷቸው። ከምግብ ቤት ይልቅ የሰው ልጅ ጭካኔ ማሳያ እኮ ነው የሚመስሉት። የቤት እንስሳት ያለ ርህራሄ አካላቸው ተተልትሎና ተጨፍጭፎ ወደ ተሰቀለበት ሉካንዳ ቤት ሄደን ለመብላት ዘወትር የምንጎመዥ እኮ ነን። ቀን በወጣና በገባ ቁጥር የበሬ፥ በግ፥ ፍየልና የዶሮ አንገትን ያለ ርህራሄ በቢላ ስንቀነጥስ፣ ስጋቸውን ስንበላና አጥንታቸውን ስንግጥ ያልነበረ የሞራል ስብዕና ዛሬ “አህዮች በዘመናዊ ቄራ ታርደው ሥጋቸው ወደ ቬትናም ሊላክ ነው” ሲባል ከወደየት መጣ? በአጠቃላይ፣ እኛ የበሬን ስጋ እየበላን ቬትናሞች የአህያ ስጋን እንዳይበሉ መከልከል አንችልም።

3ኛ በአህዮቹ ላይ የመወሰን ስልጣን ያለው አርሶ አደሩ ብቻ ነው

አብዛኛው የኢትዮጲያ አርሶ አደር አንድ ውሻና አህያ ከቤቱ አይጠፋም። ምክንያቱም፣ እነዚህ ሁለት እንስሳት ከአርሶ አደሩ ኑሮና አኗኗር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ናቸው። አርሶ አደሩ በተለይ አህያን ለገበያ የሚያቀርበው ወይ ሌላ ትርፍ አህያ ስላለው ነው አሊያም ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመው ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ በጤና እና እድሜ ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ አህዮች ሲሞቱ ጠብቆ ለጅብና ጥንብ-አንሳ ከመስጠት በስተቀር ሌላ አማራጭ የለውም። በአጠቃላይ፣ አህዮችን ከአንድ ቦታ ገዝተው ወደ ሌላ ቦታ ወስደው ከሚሸጡ ነጋዴዎች በስተቀር አርሶ አደሩ አህያን አርብቶ ለገበያ የማቅረብ ልምድ የለውም።

ይህ “አህያ ሰባ ምን ሊረባ” ከሚለው የሞራል እሳቤ በተጨማሪ የእንስሳቱ የውልደት መጠን በጣም ውስን በመሆኑ ለእርባታ ምቹ አይደሉም። ነገር ግን፣ የአህያ ስጋና ቆዳ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በቢሾፍቱ ከተማ መቋቋሙ አርሶ አደሩ አህያውን በተሻለ ዋጋ እንዲሸጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል። በጤና እና እድሜ ምክንያት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ አህዮችን ተንከባክቦ ለገበያ የማቅረብ እንዲችል እድል ይፈጠርለታል። በዚህም ለጅብና ለጥንብ-አንሳ ይተወው ከነበረው የአህያ ሥጋና ቆዳ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል። በዚህ መልኩ አርሶ አደሩ አህያውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

በተቃራኒው፣ ይህ ተግባር “ከእምነቴና ሃይማኖቴ ጋር አብሮ አይሄድም። ስለዚህ አህዮቼን ለድርጅቱ አልሸጥም” ካለም መብቱ ነው። በአህዮቹ ላይ የመወሰን ስልጣንና መብት ያለው አርሶ አደሩ እንጂ የተወሰኑ የከተማ አፈ-ጮሌዎችና የሃይማኖት ሰባኪዎች አይደሉም።

በአጠቃላይ፣ የእኛ ባልሆነ ንብረት ላይ የማዘዝ ስልጣንና መብት የለንም። ስለዚህ፣ አህዮቹን ለቄራ የመሸጥና ያለመሸጥ ውሳኔን ለአርሶ አደሩ መተው አለብን። ከዚህ በተጨማሪ፣ እኛ የጅብ ቆዳን ለባህላዊ መድሃኒት እንደምንጠቀመው ሁሉ ቻይናዎችም የአህያ ቆዳን መጠቀም ይችላሉ። በተመሣሣይ፣ እኛ የበሬ ስጋ እየበላን ቬትናሞች የአህያ ስጋን እንዳይበሉ መከልከል ደግሞ ተገቢ አይደለም።

*********

Share this post

One thought on “የበሬ ስጋ እየበላህ የአህያን ስጋ መከልከል አትችልም

 1. —የሆርን አፌርስ አምደኛ ታድሶ/ተሃድሶ አልተማረም የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጎጠኝነትን ዘረኝነት አስተምረው እኛ ወጣቱ ላይ ሲሰርፅ ነው የምንነቃው” ኃይለመለስ
  ** “የዴሞክራሲ አብዮት በኢኮኖሚ አብዮት አይጨናገፍም!”ሰላምና ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ የፖሊስን ተግባር እየተወጣ፣ የመንግስትን ክፍተት እየሸፈነ እና የሕዝብን ጥያቄ ወደ ጎን እየገፋ መቀጠል አይችልም። ስለዚህ፣ ከተወሰነ ግዜ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ለኢህአዴግ መንግስት የሥልጣን ማራዘሚያ ሆኖ መቀጠል ይሳነዋል። ይህ መቼ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መገመት ቢከብድም ግዜው የኢህአዴግ መንግስት መጨረሻ ስለመሆኑ ግን ጥርጥር የለውም። ከዚህ አንፃር፣ ሥር-ነቀል ታሃድሶ ከማድረግ ይልቅ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በማራዘም ችግሩን ለማድበስበስ መሞከር ራስን ለውድቀት ማመቻቸት ነው።” ” የሜንጫ አብዮትን እንደጀመርነው እናስጨርሰዋለን!”ማለቱ ነው ።

  **”የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው “ኢኮኖሚ አብዮት” በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ግቡን አይመታም።ይህ የኢኮኖሚያ አብዮት በስህተት ላይ ስህተት በመደጋገም፣ አንዱን ስህተት በሌላ ስህተት ለማረም መሞከር ነው። ”
  ** ዛሬ በቻይና አንድ ኪሎ ግራም “Ejiao” እስከ £300 ፓውንድ በሚደርስ ዋጋ ይሸጣል። በዚህ ምክንያት በቻይና የአህያ ቁጥር እ.አ.አ. በ1991 ከነበረበት በእጥፍ መቀነሱን ዘገባዎች ያስረዳሉ። በዚህ ምክንያት በዓለም አቀፉ ገበያ ውስጥም ከፍተኛ የሆነ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ተፈጥሯል። ለዓለም ገበያ በአንድ አመት ውስጥ 1.8 ሚሊዮን የአህያ ቆዳ ለሽያጭ የሚቀርብ ሲሆን ዓመታዊ የገበያ ፍላጎቱ ግን 4 እስከ 10 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል።
  *-ለምሳሌ በቡርኪና ፋሶ የአንድ አህያ የመሸጫ ዋጋ እ.አ.አ. 2014 ከነበረበት 60 ዶላር ወደ 108 ዶላር ጨምሯል።እኛ በሀገራችን የጅብ ቆዳን ለባህላዊ መድሃኒትነት እየተጠቀምን ቻይናዎች የአህያ ቆዳ ለተመሣሣይ ዓላማ እንዳያውሉ መከልከል በፍፁም አግባብ ሊሆን አይችልም!።”የቻይና እና ቬትናም የአህያ እርካታ በኦሮሞ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ በተሰነቀረ ጠባብነት ይሳካልን? ከኦሮሞው ላይ ፻፰ ዶላር ትገዙታላችሁ? ገበሬው ምርቱን ውሃውን ቁሳቁሶችን በምን ያጓጓዝ?ከተማ እንዳይስፋፋ የማስተር ፕላኑን ቱማታ ከበቀለ ገለባ ፅሑፍ ብዙ ይረዷል። የኢኮኖሚ አብዮት ተፃራሪ የኢኮኖሚ ምሁር ለባዕድ ኢኮኖሚ ዕድገት ምን አስቃዠውና ሕዝብና ሃይማኖተኞችን ለመሳብ ደፈረ ? ይህ ተግባር “ከእምነቴና ሃይማኖቴ ጋር አብሮ አይሄድም። ስለዚህ አህዮቼን ለድርጅቱ አልሸጥም” ካለም መብቱ ነው። በአህዮቹ ላይ የመወሰን ስልጣንና መብት ያለው አርሶ አደሩ እንጂ የተወሰኑ የከተማ አፈ-ጮሌዎችና የሃይማኖት ሰባኪዎች አይደሉም!። በተሃድሶ ሰበብ የውሸት አስረውት ታሳሪውን እንዴት ይሰልል እንደነበር “በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል በአንድ የማደሪያ ክፍል ውስጥ በአማካይ 100 ሰልጣኞች (እስረኞች) አብረው ያድራሉ። እኔ በነበርኩበት ክፍል ውስጥም 98 ሰልጣኞች (እስረኞች) ነበርን። ገመቹ የአምስት ልጆች አባትና በጣም ታታሪ ሰው ነው። ዘወትር በሥራ እንደተጠመደ ነው። ከስልጠና መልስ የተለያየ ቀለም ያላቸውን የሲባጎ ገመዶችን በመጎንጎን የኢትዮጲያና የኦሮሚያ ባንድራ ምስል ያላቸው የጥርስ መፋቂያዎችን እየሰራ አንዱን በ10 ብር ይሸጣል። ገመቹም ወደ አርሲ ሮቤ ሲመለስ በየትኛው የሥራ መስክ ተደራጅቶ መስራት እንደሚፈልግ በመጠይቁ ላይ ሞልቷል። ያን ዕለት ማታ “ገሜ… አሁንማ መንግስት በማህበር አደራጅቶ የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግልህ ነው። በየትኛው የሥራ-መስክ ለመሰማራት አቀድክ?” ስል ጠየቅኩት። የገመቹ ምላሽ ግን በጣም አስገራሚ ነበር። “ማ… እኔ?! እኔ አምስት ልጆች አሉኝ። ከማንም ሰነፍ ጋር ተደራጅቼ አገልጋይ ከምሆን ከልጆቼ ጋር ተደራጅቼ ብሰራ ይሻለኛል። የመንግስት ድጋፍ ከምር ከሆነ ለእኔና ልጆቼ ብድር ቢሰጠን መልካም ነበር” አለኝ።” ቆፍጣናው ገመቹን በግ፡ፍየል፡ዶሮ፡ላም በሬ አርብተው የአማራ ሃይማኖትና ባሕል አዲስ አበቤን ከምታበለፅግ አህያ አርባና ሃይማኖተ ቢስ ሆነህ በዶላር በዩሮ ፅደቅ እያለ የሚያሸብር ቱሪናፋ መድሐኒት ማቀነባበሪያ እዚሁ ይከፈት አላለም፡ጅብ የሚበላው አህያ ከሌለ የገመቹ ልጆች እንደሚበሉ አይገባውም ጀዝባ…! የጆሮ ጠቢነቱን ቆሌ የገፈፈውን ኢትዮጵያዊ የአሩሲ ሮቢ ገበሬ ጤናና በረከት ከሞላው ቤተሰቡ ጋር ይሁን ድንቄም ምሁር !?

  Reply

Post Comment