የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው የአልፋ ቪላን የጥገና ሂደት ጎበኙ

Source: https://fanabc.com/2019/03/%E1%8B%A8%E1%89%A3%E1%88%85%E1%88%8D%E1%8A%93-%E1%89%B1%E1%88%AA%E1%8B%9D%E1%88%9D-%E1%88%9A%E1%8A%95%E1%88%B5%E1%89%B5%E1%88%AD-%E1%8B%B6-%E1%88%AD-%E1%88%82%E1%88%A9%E1%89%B5-%E1%8A%AB%E1%88%B3/
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአርት ጋላሪ እና የመኖሪያ ቤታቸውን የጥገና ሂደት ጎበኙ።
 
ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደገለጹት የእድሳት ስራው ዉስብስብና የጥገናው ሂደቱም በብዙ ነገሩ በጥበብ የተዋቀረ እንዲሆን በመደረጉ የአርቲስቱን ስብዕና፣ ጥበባቸውን እና የአስተሳሰብ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
 
ዶክተር ሂሩት የጥገና ስራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በሚቀጥለው ዓመት ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ገልፀዋል።
 
እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በህይወት በነበሩበት ጊዜ ቤቱን እና የጥበብ ስራዎቻቸውን መንግስት ወራሽ እንዲሆን ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
 
ይህንንም ተከትሎ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ቅርሱን ለአገልግሎት ለማዋል የተለያዩ ስራዎችን ያከናወነ መሆኑን ገልጾ፥ የህግ ሂደቶች ግን ረጅም ጊዜ መውሰዳቸውን ገልጿል።
 
ቅርሱንም ለመጠገን የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር ጥናት በማድረግ፣ አማካሪ ድርጅቶች በመምረጥ፣ ቅርሶቹን የመመዝገብና ጊዜያዊ ማረፊያቸውን ማመቻቸት የንብረት ምዝገባ እና ጥገናው ስራ ከተጠናቀቀ በኋላም ለመመለስ በሚያመች መልኩ በቪዲዮ መረጃ የመያዝ ስራ ተሰርቷል።
 
የጥገና ስራውን እያከናወነ የሚገኘው ድርጅት ኋላፊ አቶ ሸምሰዲን ዳውድ እንደገለፁት የጥገና ስራውን ለማከናወን የተሰሩ የቅድመ ስራ ዝግጅት ስራውች ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገባቸውን የቅርሱን የቀድሞ ማንነትን ለመመለስ ጥረት ተደርጎ የተሰራ እንደሆነ ገልፀው ሙሉ በሙሉ ጥገናው አርቲስቱ የተጠቀሙበትን የቀለም ውህድ መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል።
 
አጠቃላይ የውስጥ ጥገና ስሩው እየተከናወነ መሆኑንና የውጭ ስራውን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እንደሚጠናቀቅ መግለጻቸውን ከባህልና ቱሪዝም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.