የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢያቸውን ለቀው ወጡ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%89%A3%E1%88%85%E1%88%AD%E1%8B%B3%E1%88%AD-%E1%8B%A9%E1%8A%92%E1%89%A8%E1%88%AD%E1%88%B5%E1%89%B2-%E1%89%B0%E1%88%9B%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%8C%8D%E1%89%A2%E1%8B%AB%E1%89%B8/

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 7/2010) የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢያቸውን ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸው ተገለጸ።

የአማራ ተወላጆች የሚደርስባቸው ጥቃት እንዲቆም በመጠየቅ ባለፉት አራት ቀናት የተጀመረው ተቃውሞ በክልሉ ልዩ ሃይል የሃይል ርምጃ መወሰዱን ተከትሎ ተማሪዎቹ ሻንጣቸውን ይዘው ከግቢ መውጣታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ትላንት ግቢው ድረስ ዘልቆ የገባው ልዩ ሃይል በተማሪዎች ላይ ድብደባ በመፈጸም ከባድ ጉዳት ማድረሱም ታውቋል።

መንገድ ላይ የተገኘ ነዋሪም ሲደብደብ መዋሉን በቪዲዮ ተደግፎ ከወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ተቃውሞ ሲደርግ ቆይቷል።

በዩኒቨርስቲው አራቱ ካምፓሶች ተማሪዎች የጀመሩት ተቃውሞ ከግቢያቸው በመውጣት ወደ ባህርዳር ከተማ ያመራ ሲሆን ከአማራ ክልል ልዩ ሃይል ጋር በተፈጠረ ግጭት ወደ መሀል መዝለቅ ሳይችል መቅረቱ ታውቋል።

ሆኖ ተማሪዎቹ ወደ ግቢያቸው በመመለስ ተቃውሟቸውን ቀጥለው እስከትላንት ድረስ ቆይተዋል።

ትላንት በነበረው ተቃውሞ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል በተማሪዎችና በአካባቢው ባገኛቸው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል።

ልዩ ሃይሉ የታጣቂዎቹን ቁጥር በመጨመርና ወደ ዩኒቨርስቲው ግቢ ዘልቆ በመግባት ተማሪዎችን በየማደሪያቸው ገብቶ ከፍተኛ ድብደባ እንዲፈጸምባቸው ማድረጉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ተማሪዎቹ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም በመጠየቅ የጀመሩት ተቃውሞ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የአማራ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት እየተባባሰ መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁ ሲሆን መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ይህንንም ጥያቄያቸውን በተቃውሞ ሰልፍ በማሰማት ላይ በነበሩ ጊዜ ነው ከአገዛዙ ታጣቂዎች ድብደባና ወከባ የተፈጸመባቸው።

ዛሬ ተማሪዎቹ ግቢያቸውን ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

 

 

The post የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢያቸውን ለቀው ወጡ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.