የቦስኒያ ክሮሺያ ጄኔራል በችሎቱ ፊት መርዝ ጠጥተው ሕይወታቸውን አጠፉ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%89%A6%E1%88%B5%E1%8A%92%E1%8B%AB-%E1%8A%AD%E1%88%AE%E1%88%BA%E1%8B%AB-%E1%8C%84%E1%8A%94%E1%88%AB%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%89%BD%E1%88%8E%E1%89%B1-%E1%8D%8A%E1%89%B5/

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 21/2010)በሔግ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደታቸውን ሲከታተሉ የነበሩት የቦስኒያ ክሮሺያ ጄኔራል በችሎቱ ፊት መርዝ ጠጥተው ሕይወታቸውን አጠፉ።

በቦስኒያ ሙስሊሞች ላይ በተፈጸመ የጦር ወንጀል ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸውና በ20 አመት እስራት እንዲቀጡ የተፈረደባቸው ጄኔራል አሟሟት ጉዳይ በመጠራት ላይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የቀድሞ የቻይና ጄኔራል በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው ባለበት ወቅት ሕይወታቸውን ማጥፋታቸው ታውቋል።

አንድ የቀድሞው የቦስኒያ ክሮሺያ ጄኔራል በሔግ ፍርድ ቤት ውስጥ የፍርድ ውሳኔያቸውን በመስማት ላይ እያሉ መርዝ ጠጥተው መሞታቸው ታውቋል።

የ72 አመቱ ጄኔራል ስሎቦዳን ፕራልጃክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1992 እስከ 95 በቦስኒያ ሙስሊሞች ላይ በተፈጸመ የጦር ወንጀል በሔግ ኔዘርላንድ የሚገኘው ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ብይን ሰጥቶ በ20 አመት እስራት እንዲቀጡ ከዚህ በፊት የወሰነውን ውሳኔ ይግባኝ ለማለት ነበር ትላንት ፍርድ ቤት የቀረቡት።

ዋናው ዳኛ የ20 አመቱ እስራት እንደሚጸናና ይግባኛቸው ውድቅ መሆኑን ሲናገሩ ጄኔራሉ ግን “እኔ የጦር ወንጀለኛ አይደለሁም ፍርዳችሁንም አልቀበልም” የሚል መልስ ከሰጡ በኋላ በኪሳቸው በብልቃጥ ይዘው የገቡትን መርዝ ጨልጠዋል።

በሁኔታው የተደናገጡት ዳኛ የፍርድ ቤቱ ሂደት እንዲቋረጥ አዘው መጋረጃው እንዲዘጋ ጠባቂዎችም ብልቃጡን እንዳይነኩ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ዳኛው ትዕዛዙን የሰጡት በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተፈጸመው ራስን የማጥፋት ድርጊት በባለሙያዎች እየተመረመረ በመሆኑ ነው።

ጄኔራሉም “መርዝ ጠጥቻለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጄኔራል ስሎቦዳን ፕራልጃክ መርዙን እንደጠጡ ወዲያውኑ ወንበራቸው ላይ ተዝለፍልፈው መውደቃቸው ታውቋል።

በፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ከተደረገ በኋላም በአስቸኳይ ሄግ በሚገኝ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሕይወታቸውን ግን ማትረፍ አልተቻለም።

በቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረው የፍርድ ሂደት የተፈጠረው ያልተለመደ ድርጊት በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኗል።-ሆኖም ግን ከቦስኒያ፣ክሮሺያና ሰርቢያ በጦር ወንጀል ተከሰው የራሳቸውን ሕይወት ሲያጠፉ ጄኔራሉ የመጀመሪያ አይደሉም።

ከዚህ በፊት ሁለት የሰርቢያ ተከሳሾች በ1998ና በ2006 ራሳቸውን ሰቅለው መግደላቸውን ሮይተርስ የፍርድ ቤት መዛግብትን ጠቅሶ ዘግቧል።

ላለፉት 24 አመታት እየተካሄደ ባለው የፍርድ ሂደት በሄግ የተቀመጠው የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ አለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የ161 ተከሳሾችን ጉዳይ የተመልከተ ሲሆን እስካሁን በ83ቱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል።

ከዚህ ውስጥ 60ዎቹ ሰርቢያውያን መሆናቸው ታውቋል።

ዋናው ተጠርጣሪ የቀድሞ ዩጎዝላቪያና ሰርቢያ ፕሬዝዳንት ስሎቦዳን ሚሎሶቪች በ2006 በልብ ድካም መሞታቸው ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ የቀድሞ የቻይና ጄኔራል በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ጥያቄ እየቀረበላቸው ባለበት ወቅት ሕይወታቸውን ማጥፋታቸው ታውቋል።

ጄኔራል ዛንግ ያንግ በጉቦና ንብረት በማጋበስ ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደነበር ሺንዋ በዘገባው አስፍሯል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.