የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪን ለመቆጣጠር እንዲቻል መመሪያ ተዘጋጀ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/147320

የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪን ለመቆጣጠር እንዲቻል መመሪያ ተዘጋጀ
በግል ትምህርት ቤቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተደረገ ያለውን የተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪን ለመቆጣጠር እንዲቻል መመሪያ መዘጋጀቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የመማር ማስተማር እና ምዘና ዘርፍ ኃለፊው አቶ ተሰማ ዲማ ለደ.ሬ.ቴ.ድ እንዳስታወቁት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በተለይም በከተሞች የግል ትምህርት ቤቶች በየጊዜው ምክንያታዊ ያልሆነ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ቢሮው ጥቆማ ይደርሰዋል፡፡ ሆኖም ግን የክልሉ ትምህርት ቢሮ የግል ትምህርት ቤቶችን የመማር ማስተማር ሥራ የሚከታተልበት አሠራር ያለው ቢሆንም ክፍያን በተመለከተ መቁረጥ ስለማይችል ትምህርት ቤቶቹ ሊመሩበት የሚገባውን መመሪያ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት የግል ትምህርት ቤቶች የተማሪዎችን የትምህርት ቤት ክፍያ ላይ ጭማሪ ከማድረጋቸው አስቀድሞ በዓመቱ ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራት ከተማሪ ወላጆች ጋር በጥልቀት በመነጋገርና ምክንያቶችን ዘርዝረው የማስቀመጥ ኃላፊነት እንዳለባቸውም በመመሪያው ላይ በግልጽ መቀመጡን አብራርተዋል፡፡
የተማሪ ወላጆችና ማህበረሰቡ ያላመነባቸው የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ በአሠራሩ መሠረት ተቀባይነት እንደሌለው አውቆ በየአካባቢውና ችግሩ በስፋት በሚስተዋልባቸው ቦታዎች ህዝቡ መብቱን እንዲያስከብርም አቶ ተሰማ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም የክልሉ ትምህርት ቢሮ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርግና ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.