የናይጀሪያዊው ባለሀብት የዳንጎቴ ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ እና ሁለት ኢትዮጵያውያን የሥራ ባልደረቦቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመገደላቸው ዋናው መስሪያ ቤት ማብራሪያ ሰጠ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%8A%93%E1%8B%AD%E1%8C%80%E1%88%AA%E1%8B%AB%E1%8B%8A%E1%8B%8D-%E1%89%A3%E1%88%88%E1%88%80%E1%89%A5%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%8B%B3%E1%8A%95%E1%8C%8E%E1%89%B4-%E1%88%B2%E1%88%9A%E1%8A%95/

የናይጀሪያዊው ባለሀብት የዳንጎቴ ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ እና ሁለት ኢትዮጵያውያን የሥራ ባልደረቦቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመገደላቸው ዋናው መስሪያ ቤት ማብራሪያ ሰጠ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 09 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው በተፈጸመው ግድያ ሀዘናቸውን መግለጻቸው ተነግሯል።
የድርጅቱ የማርኬቲንግ ምክትል ሥራ አስኪያጁን አቶ ታሪኩ አለማየሁ ለብሉምበርግ በስልክ እንደገለጹት ዲፕ ካማራ እና ሁለቱ ኢትዮጵያውያን የድርጅቱ ሠራተኞች ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
ሦስቱም የተገደሉት ከአዲስ አበባ 90 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሙገር ሲሚንቶ አቅራቢያ በጠራራ ጸሀይ እንደሆነ፣ የኩባንያው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኤድኒን ዳቫኩማር ከሌሎስ በኢሜይል ገልጸዋል።
ገዳዮቹ መጀመሪያ ላይ ትልልቅ ድንጋዮች ከሚጓዙባት መኪና ፊት በማስቀመጥ ሾፌሩን እንዲያቆም ማስገደዳቸውን የጠቀሱት ዴቫኩማር፣ ልክ መኪናዋ መቆሟን ተከትሎ ዲፕ ካማራ በመውረድ ለማምለጥ ሲሞክር ተኩሰው እግሩን እንደመቱት ገልጸዋል።
ህንዳዊው ሥራ አስኪያጅ ተመልሶ ወደ ጂፕ መኪናዋ ዘልሎ ለመግባት ሲሞክር ሰዎቹ በመቅረብ በበርካታ ጥይት በተደጋጋሚ ተኩሰው እንደገደሉት እና እሱን ከጨረሱ በኋላ ሾፌራቸውንና ጸሀፊያቸውን በተመሣሳይ መንገድ መግደላቸውን ዴቫኩማር አብራርተዋል።
“የተፈጸመው ንጹሀንን የመጨፍጨፍ ወንጀል ነው” ብለዋል የኩባንያው ዋና ኃላፊ ከሌጎስ በሰጡት በዚሁ መግለጫ።
ዳንጎቴ ሲሚንቶ የሚተዳደረው በናይጀሪያው ቢሊየነር በአሊኮ ዳንጎቴ ሲሆን፣ ባለሀብቱ በኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጃቸውና ሠራተኞቻቸው ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢኦትዮጵያ የሚገኘው የህንድ ኤምባሲ በበኩሉ የዲፕ ካማራን አስከሬን ወደ ቤተሰቦቹ ህንድ ለመላክ አስፈላጊውን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ በሆኑት በዲፕ ካማራና በሁለት ኢትዮጵያውያን የስራ ባልደረቦቻቸው ላይ በትናንትናው ዕለት በተፈጸመው ግድያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀዘናቸውን መግለጻቸውን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
ዶክተር አብይ በዚሁ መግለጫቸው ለሟቾቹ ቤተሰቦች እና ለመላው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሰራተኞች መፅናናትን የተመኙ ሲሆን፣ መንግስት ግድያውን የፈጸሙትን አካላት እያጣራ መሆኑን እና አጥፊዎችን ለህግ እንደሚያቀርብም ቃል ገብተዋል።

The post የናይጀሪያዊው ባለሀብት የዳንጎቴ ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ እና ሁለት ኢትዮጵያውያን የሥራ ባልደረቦቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመገደላቸው ዋናው መስሪያ ቤት ማብራሪያ ሰጠ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.