የአማራ ብሄርተኝነትና ብሄርተኞች የግድ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ነጥቦች

Source: http://welkait.com/?p=10914
Print Friendly, PDF & Email

1. እርሥ በርሥ መከባበር፣ የትኛውም አይነት ልዩነት ቢኖረን እንኳን ፊት ለፊት መጨቃጨቅ ማቆምና የግልን ጉዳይ በጓዳ ጨርሶ መምጣትን ባህል ማድረግ አለብን። ማንም የመሠለውን ሀሳብ ሲያነሳ ሀሳቡን ማክበር ያሥፈልጋል። ለአማራ ህዝብ ይጠቅማል ብሎ ሀሳብ የሠነዘረን ሁሉ ሀሳቡን ማክበር መልመድ አለብን! ከትግራይና ኦሮሚያ ብሄርተኞች መማር ይኖርብናል። ሁለቱ ብሄርተኞች የራሳቸውን ጉዳይ በጓዳ ጨርሠው ነው ወደ አደባባይ የሚመጡት። በአደባባ ፍቅር በፍቅር ሆነው ሲታዩ በጓዳ የሚጣሉ አይመሥሉም። ይልቁንሥ እነዚህ ብሄርተኞች የራሳቸውን ጉዳይ ዱላ ቀረሽ ክርክር አድርገው ጭቅጭቃቸውን አጠናቀው ነው ወደ ፊት ለፊት የሚመጡት። እኛም እንደዛ ማድረግ ይልመድብን!

2. የአማራ ብሄርተኝነት መሪዎችን መሠየምና መሪዎቹን መከተል መልመድ አለብን። እርግጥ ነው የአማራ ብሄርተኝነት በአጭር ጊዜ ውሥጥ ብዙ ጀግና ልጆችን ማፍራት ችሏል። ይሁን እንጅ ተደማጭነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የአማራ ብሄርተኝነትን የሚመሩ ጥቂት ጀግኖችን የበለጠ በማጀገን የትግሉ መሪ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርብናል። ሌሎች ብሄርተኞች ጀግናቸውን ፈጥረው ማጀገን ችለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ ደካሞች ነን። ሥለሆነም በአማራ ብሄርተኝነት ዙሪያ ለሚነሡ ማንኛውም አይነት ጉዳዮች በቅድሚያ አይን የሚጣልባቸው መሪዎች ያሹናል! ይህንን ቀንበር የሚሸከሙ ሠዎችን ማዘጋጀት ብሄርተኝነት ትግሉ ወጥና አቅጣጫ ያለው እንዲሆን ያግዘዋል።

3. አማራ የራሡ የሆነ ሚዲያ ያሥፈልገዋል። በዘመናዊው አለም ቀርቶ በጥንት ዘመን እንኳን የሚዲያ ሃያልነት የሚታበይ አይደለም። አባቶቻችን “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚሉት የሚዲያን ሃያልነትና አሥፈላጊነት ሲያሥረግጡ ነው። በመሆኑም የአማራ ብሄርተኝነትን ለማቀጣጠል ልጆቹ የሚመክሩበት፣ ችግር መከራውን የሚነግሩበት፣ ታሪካችን የሚተነትኑበት፣ ወግ ባህሉን የሚያወጉበት፣ አቅጣጫ የሚያሣዩበት የራሡ ነጻ ሚዲያ ያሥፈልገዋል። ለተግራዊነቱ ደግሞ አማራ ከበቂ በላይ ትንታግ የሆኑ የሚዲያ ልጆችን ታድሏል። እንኳን የአማራ ሚዲያን ሌላውንም ከፍተን ሥናየው በአማራ ልጆች የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን! ሥለዚህ ሚዲያ ማቋቋም ለነገ የሚባል መሆን የለበትም። ጉዳዩ የዛሬ የቤት ሥራችን ነው ለማለት ነው።

4. ወንድማማችነትን ማጠናከር ይኖርብናል። ወንድማማችነቱ በየትኛውም አካባቢ በሚፈጠሩ መደበኛና ኢ-መደበኛ ግንኙነቶች መጠናከር አለበት። የገበያ ትሥሥር መፍጠርን ጨምሮ የትኛውን መተጋገዝ ያማከለ ወንድማማችነት። ከእኔ አንተ ቅደም የሚያሥብል ወንድማማችነት!

5. የአማራ ህዝብ ቱባ ባህሎችን መላበሥ ያሥፈልጋል። እያንዳንዳችን የአማራ ባህል መገለጫዎች መሆን ይጠበቅብናል። ተንቀሳቃሽ የባህል ማዕከል መሆን ይኖርብናል። ታላላቆችን ማክበር፣ ተሳዳቢ አለመሆን፣ ታማኝና ኩሩ መሆን፣ ካልነኩን በፍጹም አለመንካት፣ ድንበር አልፎ ለሚመጣ ፍጹም አራሥ ነብር መሆን፣ የአባቶቹን አደራ የማይበላ ትውልድ መሆን ይጠበቅብናል።

እነዚህን ካሟላን የአማራን ህዝብ ከተጋረጠበቅ አደጋ ማዳን እንችላለን!!

GashawMersha እንደከተበው

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.