የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ስዩም ተሾመ ታሰሩ

Source: http://www.yegnagudday.com/2018/03/09/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%9D%E1%89%A6-%E1%8B%A9%E1%8A%92%E1%89%A8%E1%88%AD%E1%88%B2%E1%89%B2-%E1%88%98%E1%88%9D%E1%88%85%E1%88%AD-%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%88%B5%E1%8B%A9%E1%88%9D-%E1%89%B0%E1%88%BE/

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ስዩም ተሾመ ታሰሩ

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ መታሰራቸው ተነገረ፡፡

አቶ ስዩም ከዩኒቨርሲቲ መምህርነታቸው ባሻገር፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡

በስልጣን ላይ የሚገኘውን አገዛዝ አምባገነናዊ አስተዳደር በመቃወም ትችቶችን የሚያቀርቡት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከደህንነት ሰዎች ማስፈራሪያ እየደረሳቸው እንደሚገኝ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ስርዓቱን ወቅሰው በሚያቀርቧቸው ጽሁፎቻቸው የተነሳ፣ ማስፈራራያ እና ዛቻ ሲደርሳቸው የቆዩት አቶ ስዩም፤ በመጨረሻም ዛቻው ወደ አፈና ተቀይሮ በዛሬው ዕለት ለእስር ሊዳረጉ ችለዋል፡፡

አቶ ስዩም ተሾመ ለእስር የተዳረጉት ዛሬ ሐሙስ የካቲት 29 ቀን 2010 ሲሆን፤ ወሊሶ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው በፖሊሶች ከተያዙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተወስደዋል፡፡

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስም በአዲስ አበባ በሚገኝ እስር ቤት እንደሚገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

ወደ ወሊሶ ያቀኑት ፖሊሶች፣ መምህሩን በቁጥጥር ስር ካዋሏቸው በኋላ፣ ቤታቸውን አገላብጠው መፈተሻቸውን የጠቆሙት መረጃዎች፤ ከፍተሻው በኋላም ፖሊሶቹ ከአቶ ስዩም ቤት አንዳንድ ወረቀቶችን መውሰዳቸውንም መረጃዎቹ አክለዋል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ ኢትዮ-ቲንክ ታንክ የተባለ ድረ-ገጽ ከፍተው፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ትንታኔ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በተጨማሪም በስማቸው በከፈቱት የፌስቡክ ገጽም፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን ሲያቀርቡ የነበሩት አቶ ስዩም፤ በሚያቀርቧቸው ፖለቲካ ነክ ጹሁፎች የተነሳ በአገዛዙ ጥርስ ተነክሶባቸው እንደነበር ከመታሰራቸው በፊት ሲናገሩ ነበር፡፡

ከአገዛዙ ሲደርስባቸው የነበረውን ማስፈራሪያ ችላ በማለት፣ በፖለቲካዊ ትንታኔያቸው እና ትችታቸው የገፉበት የአምቦ ዩኒቨርሲቲው መምህር፤ በዛሬው ዕለት ለእስር ተዳርገዋል፡፡

አቶ ስዩም ባለፈው ዓመት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ለሶስት ወራት እስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፡፡

Share this post

One thought on “የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ስዩም ተሾመ ታሰሩ

 1. ኮማንድ ፓስት የደቦ ወቃጭ ማኅበር
  አሁን ማን ሊጠቀም ነገር ቢካረር
  ሁሉ ሥልጣን ቢለቅ እንደ ኃይለመለስ
  ተራራ አንቀጥቃጩም እቦታው ቢመለስ
  ሰላምና አንድነት ለሕዝቡ ቢለገስ
  ሉዓላዊነት ባሕልና ሃይማኖት ባይፈርስ
  ትውልድ በማንነት ወዠብ ባይተራመስ
  በርሃብ ፍርሃት እልቂት ወሬ ባንታመስ
  በዘረኝነት ጎጥ አድልዎ ሀገር ባይሸበርስ
  ያለን ሳያልቅ እኛም ላንጠፋ የነበረን ይመለስ
  ቅን አሳቢ ትውልድ መካሪ ሰው ቢሰየም
  ሀገር ወዳድ ፈጣሪን ፈሪ አስተዋይ ቢሾም
  በሰነበር ላይ ሰንበር በቂም ላይ ቂም
  መደብደብ ማሰር ያመረቅዛል ቁስል አይድንም
  እግዚኦ ክፉን አርቅልን ደግ ደጉን አሰማን
  በማወቅም ባለማወቅ አንታሰር ይፍቱን/ተፋቱን።
  በለው!

  Reply

Post Comment