የአረንጓዴ አሻራ ቀን የንቅናቄ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሄደ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/133226

(ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ቀን የንቅናቄ መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሶስት ሚሊየን ችግኝ ተከላ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስተዳደሩ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

በዛሬው ዕለትም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት የአረንጓዴ አሻራ ቀን የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ግብዣ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው፡፡
በንቅናቄው ላይ የተለያዩ የኪነ ጥብብ ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች መድረኩ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሃምሌ 22 ቀን ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ በመዲናዋ 116 ወረዳዎች ወጣቶችን በማሳተፍ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ጉድጓዶች የተዘጋጁ ሲሆን፥ ለዚህ ፕሮግራም ከ400 በላይ የመትከያ ስፍራዎች መዘጋጀታቸው ተነግሯል፡፡
በዚሁ ፕሮግራም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የሚሳተፉበት ቦታ መዘጋጀቱን ነው የተገለፀው፡፡
በዕለቱ የሚሰሩ ስራዎችን የሚመራ ግብረ ሃይል የተቋቋመ ሲሆን 100 ሺህ ወጣቶች የእለቱን ዝግጅት የሚያስተባብሩ ይሆናል፡፡
ሰፋፊ የመትከያ ቦታ የሌላቸው የአራዳ፣ ልደታ፣ ቂርቆስና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ በወረዳቸው በመገኘት ችግኞችን በመውሰድ በጊቢያቸው መትከል ይችላሉ ተብሏል፡፡
በማስፋፊያ አካባቢ የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በየአካባቢዎቻቸው በተዘጋጁ የመትከያ ጣቢያዎች እንደሚተክሉ ነው የተናገሩት፡፡
በዕለቱ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች በሙሉ የችግኝ ተከላ ላይ ስለሚሳተፉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንደማይሰጡም ታውቋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.