የአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ከህወሃት ጋር መጠመድ ህዝብ እያነጋገረ ነው

Source: http://amharic.abbaymedia.com/archives/29004

ኢትዮጵያ አገሩን በመወከል በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች በሩጫ በመወዳደር በርካታ ሜዳሊያዎችን ያስገኘው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሰ ጸረ አገር ከሆነው ህወሃት ጋር መጣበቁ በምን ምክንያት እንደሆነ ህዝብ እያነጋገረ መሆኑን ለትንሴ ከሚደርሰው የህዝብ አስተያየት ለማወቅ ተችሎአል።

ሃይሌ ገብረስላሴ በተለዩ አገሮች ባደረገው ውድድር አሸንፎ አንቱ የሚያስብለውን ገንዘብ ያገኘና አገር ውስጥ በልማት ላይ ያዋለ መሆኑ እየታወቀ በአገር ሃብት ዘረፋ ከከበሩና ለረጅም ጊዜ በህዝባችን ላይ በፈጸሙት የአደባባይ ጭፍጨፋ፤ እስርና እንግልት ከአገር አልፎ አለም አቀፍ ውግዘትና ነቀፋ እየደረሰበት ካለው ዘረኛው የህወሃት አገዛዝ አመራሮች ጋር የፈጠረው ወዳጅነት አብዛኛውን የቀድሞ ደጋፊዎቹንና አድናቂዎቹን ሳይቀር እያስገረመ እንደሆነ ይነገራል።

ድህረ ምርጫ 97 ሟቹ መለስ ዜናዊ አጋዚ የተባለውን ፋሽስታዊ ሠራዊት በከተማ አሰማርቶ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን በጠራራ ጸሃይ ካስጨፈጨፈና የቅንጅት አመራሮችን በሙሉ ከርቼሌ ከሰደደ ቦኋላ የገጠመውን የአገር ውስጥና  የውጪ ተቃውሞ ለማርገብ በሽምግልና ስም በህዝባችን ላይ ክህደት ከፈጸሙ ግለሰቦች አንዱ አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በፈጸመው ስህተት ከመጸጸት ይልቅ የህወሃትን ቅዱስነትና የልማት ተቆርቋሪነት በየመድረኩ ለመግለጽ ሲንደፋደፍ በተደጋጋሚ ታይቷል የሚሉ ታዛቢዎች ከመለስ ዜናዊ ህልፈት ቦኋላ ህወሃት ውስጥ የተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ እረፍት ከነሳቸው ግለሰቦች አንዱ እንደሆነም ይናገራሉ። ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ህወሃትን ለመሸምገል ከሰሞኑ እንቅስቃሴ ከጀመሩት አንዱ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ከአመት በፊት አገራችን ውስጥ በተጀመረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ በተለይም በትውልድ አገሩ በአርሲ ውስጥ በርካታ ዜጎች በአጋዚ አልሞ ተኳሾች እንደተጨፈጨፉ እያወቀ እንኳ አንድም ነቀፌታ አላሰማም የሚሉ ሌሎች ታዛቢዎች ሃይሌ ገብረስላሴ አሰላለፉን ከህወሃት ጋር ለማድረግ የተገደደው በተለያዩ ኢንቬስትመንቶች ላይ ያዋለውን ገንዘብና ንብረት ዋስትና ለማግኘት ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ። ሆኖም ከሰው ህይወትና ከአገር ሉአላዊነት በላይ ለግላቸው ገንዘብና ንብረት የሚጨነቁ ሰዎች ስብዕናቸው የወረደና የሞራል ሃላፊነት የማይሰማቸው ደካሞች እንደሆኑ የተለያዩ አዋቂዎች በህይወት ዘመናቸው ሲያስተምሩ ኖረዋል። ሃይሌ ገብረስላሴ ለንብረቱ ተጨንቆም ይሁን የህወሃትን የፖለቲካ መስመር አፍቅሮ በህዝባችን ላይ ለፈጸመው ክህደት በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም የሚሉ በርካቶች ናቸው።

 

Share this post

2 thoughts on “የአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ከህወሃት ጋር መጠመድ ህዝብ እያነጋገረ ነው

Post Comment