የአቶ ጌታቸው አሰፋ  ክስ መታየት ጀመረ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%8C%8C%E1%89%B3%E1%89%B8%E1%8B%8D-%E1%8A%A0%E1%88%B0%E1%8D%8B-%E1%8A%AD%E1%88%B5-%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%A8%E1%89%B5-%E1%8C%80%E1%88%98%E1%88%A8/

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2011)በከባድ የሌብነት ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህነንት መስሪያ ቤት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ዛሬ  ክስ መታየት ጀመረ።

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክሳቸው የተሰማው አቶ ጌታቸው አሰፋ በተለያዩ ስውር ቤቶችና በፌደራል መንግስት ስር በሚታወቁ እስር ቤቶች ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ከባድ ግርፊያ፣ ድብደባና ጥፍር በመንቀል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው አስደርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በእሳቸው ስር የነበሩ የመምሪያ ሃላፊዎችም በተመሳሳይ ወንጀሎች ተጠርጥረው ክስ እንደቀረበባቸው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሌሉበት ክሳቸው ዛሬ መታየት የጀመረው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በስውር ማፈኛ ቤቶች በሚፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎች የሚያስጠይቅ የክስ ፋይል እንደተከፈተባቸው ነው የተገለጸው።

በልደታ ምድብ ችሎት መታየት የጀመረው የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት አመራሮች የክስ ሂደት ከአቶ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሌላ ፣ አቶ አጽበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይና አቶ ሺሻይ እንዳልተገኙም ተመልክቷል።

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በተለያዩ መምሪያዎች በሃላፊነት የሰሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፣አቶ ተስፋዬ ገብረጻዲቅ፣ አቶ ጎህ አጽብሃ ገብረህይወት፣ አቶ ቢኒያም ማሙሸትና አቶ ሸዊት በላይ ላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌብነት ወንጀሎች ክስ ቀርቦባቸዋል።

እነዚህ ሃላፊዎች የጸረ ሽብር መምሪያ፣ የአዲስ አበባ ደህንነት መምሪያ፣ የውስጥ ደህንነት መምሪያና የኦፕሬሽን ክፍል መምሪያ በተሰኙ ከፍተኛ ሃላፊነቶች ላይ በነበራቸው ሚና በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ከባድ ወንጀልን በበላይነት መምራታቸው ተገልጿል።

እነዚህ የቀድሞ የደህንነት ሃላፊዎች በኃይል አስገድዶ ምርመራ በማካሄድ፤ የሰብአዊ መብት ረገጣ በመፈጸም፤ በምርመራ ላይ የጥፍር መንቀልን ጨምሮ በድብቅ እስር ቤት ውስጥ ዓይን ሸፍኖ ከባድ ድብደባ መፈጸም የሚሉት ወንጀሎች ተጠቅሰው ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በምርመራ ወቅት በድብደባ የተነሳ ህይወቱ ያለፈ ሰውም ተጠቅሶ በክስ መዝገቡ ላይ ተነስቷል።

በአቶ ጌታቸው ላይ የቀረበው ክስ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያልታወቁ እስር ቤቶች ውስጥ በኦነግና ግንቦት ሰባት ስም የተያዙ ሰዎችን በማሰቃየትና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በመፈጸም የሚል ነው።

አቶ ጌታቸው አሰፋ  ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል በተጨማሪ ከባድ የሌብነት ወንጀል መፈጸማቸውን በክሱ ላይ ተመልክቷል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል የእስር ትዕዛዝ ቢወጣም የትግራይ ክልላዊ መንግስት አሳልፎ ላለመስጠት በመወሰኑ በአካል ሊገኙ እንዳልቻሉ ታውቋል።

 

The post የአቶ ጌታቸው አሰፋ  ክስ መታየት ጀመረ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.