የአዋጅ ረቂቁ – ኦሮምኛ ቋንቋን አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ “ሰምተውት የማያውቁት ልሳን” አስመስሎ አቅርቦታል። (ማስረሻ ማሞ ነኝ)

Source: http://amharic.abbaymedia.com/archives/33499

እንዴት ከረማችሁ የተወደዳችሁ የማማ መሰናዶ ተከታታዮች? 
ባለፈው መሰናዶ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ አዲሳ’ባን “በልዩ ጥቅም” ቁማር እንደ ጆከር ሊመዛት ማሰቡን አውግተን ነበር። የተሰነባበትነውም የቋንቋ ጉዳይና ሌሎቹን ተዛማች – የማኅበራዊ መስተጋብር ትስስሮችን የሚያሳየውን መሰናዶ ለማቅረብ ቀጠሮ በመያዝ ነበር።

የአዋጅ ረቂቁ – ኦሮምኛ ቋንቋን አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ “ሰምተውት የማያውቁት ልሳን” አስመስሎ አቅርቦታል።

ለመኾኑ አዲስ አበባ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሞ ገበሬዎች ከከተሜው ጋራ የሚግባቡት በምን ቋንቋ ነበር? የሚል ቀለል ያለ ጥያቄ ጣል አድርገን እንጀምር።

በየትኛውም ቅርጹ በቋንቋ የመገልገል መብት ማንም ሊገስሰው የማይገባ መሠረታዊ መብት ነው። አዲስ አበባ ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ሊከፈቱ ነው የሚለው ዜና ለእኔ “አንድ ርምጃ ወደፊት” የኾነ ሐሳብ ነው። ምክንያት ከተባልኹ ኦሮምኛ ለአዲስ አበቤ እንግዳ ቋንቋ ስላለኾነና ሁሉም አዲስ አበቤ አቀላጥፎ ሊናገረው የሚገባ የኢትዮጵያ ቈንቋ ስለኾነ እላለሁ።

ኦሮምኛ ቋንቋ አለመቻሌ ከምቆጭባቸው ነገሮች አንዱ ነው። ኦሮምኛ ቋንቋ ለእኔ እንግዳ ቋንቋ አይደለም። እንደመታደል ኾኖ ብዙ የሱሉልታ ኦሮሞዎች በየቀኑ ከቤታችን ሲያውካኩ፣ ሲስቁና ሲጫወቱ ይውሉ ነበር። በልጅነት ሕይወቴ ውስጥ በደማቁ የተጻፉ ሰዎች ናቸው።

የራሳቸውን ጉዳይ በኦሮምኛ ያጣድፉታል። እኔና እናቴን ጠላ ለማዘዝ ሲፈልጉ ደግሞ በሚጣፍጥ ኮልታፋ አማርኛ “አንቴ ማስራሻ፦ እስኪ አንዲ ጣሳ አምጣ/አምጪ?’ ይሉን ነበር። እነ እትዬ ነዲ፣ እነ እትዬ አረጋሽ፣ እነ ጋሽ በቀለ፣ እነ ጋሽ ማሩ . . . . ሌሎችም ብዙዎች በቀጨኔና በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች አይብ፣ ወተት፣ ቅቤና እንቁላል፤ እንዲኹም ለማገዶና ለቤት መሥሪያ የሚኾን እንጨት ያቀርባሉ።

የሚያስፈልጋቸውን ከገበዩ በኋላ ጠላ የሚወድ ጠላውን፣ ጠጅ የሚወድ ጠጁን፣ አረቄ የሚወድ አረቄውን ሳብ ሳብ ያደርጋሉ። ከዚያ በቡድን በቡድን ኾነው እየጨፈሩ – ጨለማ የዋጠውን የእንጦጦ ጫካ በዘፈን እየሰነጠቁ ወደ ሱሉልታ ይገሰግሳሉ። በቀን 20 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ።

ኦሮሞ ሲባል በፍጥነት አእምሮዬ ውስጥ የሚመጣው ቸርነትና ለጋስነት ነው። እትዬ ነዲ የሚባሉት ደንበኛችን በሳምንት አንድ ጊዜ አይብ፣ እንቁላልና ቅቤ በነጻ ለእናቴ ያመጡላት ነበር። እትዬ አረጋሽም አልፎ አልፎ እንዲሁ ያደርጋሉ። የሚገርመኝ ታዲያ እናቴ ብድሯን ለመመለስ “ዛሬ የጠላ ሂሳብ በእኔ ነው” ስትላቸው በፍጹም አለመስማማታቸው ነበር። ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት ዝምድና በኋላ የሱሉልታ ኦሮሞዎች ለአንተ ምንድን ናቸው? ብባል፦ እምዬዎች ናቸው የሚል መልስ እሰጣለሁ።

አዲስ አበባ በከተማው ውስጥ የሚኖሩባት ሰዎች ከተማ ብቻ አይደለችም። 20 ኪሎ ሜትር በእግሩ እየኳተነ ላቡን ሲያፈስ የነበረው የሱልልታ ነዋሪም ከተማ ናት፤ በሁለት እግሯ እንድትቆም አድርጓታልና። አዲስ አበባ፦ የካራ፣ የሰበታ፣ የከታና የሱሉልታም ጭምር ናት፤ የጋራ ከተማ ናት።

ኦሮምኛን ቋንቋችን ማድረግ ኢትዮጵያን አጥብቆ ይሰፋታል እንጂ በምንም መልኩ ስጋቷ አይኾንም። ኦሮምኛንና አማርኛን በአግባቡ የሚያውቅ ትውልድ ከፈጠርን – ብዙ ጸጋዬ ገብረመድኅኖችን፣ ብዙ ሰለሞን ዴሬሳዎችን፣ ብዙ በድሉ ዋቅጅራዎችን . . . እና ውብ ሰብእናዎችን ለማፍራት ተዘጋጅተናል ማለት ነው።

ይልቅ ይልቅ . . . ለእኛ እንግዳ ያልኾነውን ኦሮምኛ ማስተማሩ ሁሉን አቀፍና አካታች እንዲኾን – ለኦሮሞም እንግዳ ባልኾነው የግዕዝ ፊደል ቢዘጋጅም መልካም ነው እላለሁ።

በሌላ በኩል አንዳንዶቻችን የአዲስ አበባን ሚና ጠቅልለን “የእቴጌ ጣይቱና የዳግማዊ ምኒልክ” ስጦታና ቱሩፋት ብቻ ለማድረግ ስንጥር፤ ሌሎቻችን ደግሞ – ቅድመ ምኒልክ በዕቅድና በፕላን ተሠርታ ያለቀችና የተነጠቀች ከተማ ፈጥረን “በአያት – ቅድመ አያት- የውርስ ይገባኛል” ጥያቄ ስንዳክር፤ መሬት ላይ ለዘመናት የተገመደውን ገመድ እንዳንበጥስ መጠንቀቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በአዲስ አበባ ላይ ሕወሓት ሊቆምር የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ቁማር በጥንቃቄ ማየት ያለብን ይመስለኛል። በኔ እምነት የአዋጅ ረቂቁ በስግብግብነት በሽታ በተለከፉ በህወሓትና በኦፒዲዮ ለሂቃን መካከል መካከል የሚደረግ የጥቅም መላፊያ ቁማር ነው።

አዲስ አበባ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ፍትኅ እጦት የምትሰቃይ ከተማ ናት። ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትኅ የተጠሙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያንና አክቲቪስቶች አዲስ አበባን በሚቆምሩባት አምባገነኖች “ሽብርተኛ” ተብለው ተፈርጀዋል። በቀለ ገርባም፣ አንዳርጋቸው ጽጌም፣ እስክንድር ነጋም፣ መረራ ጉዲናም፣ ሌሎችም በ 10 ሺሕ የሚቆጠሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፍትኅ አቀንቃኞች በአገዛዙ የወጣላቸው ስም “አሸባሪ” የሚል ነው።

ንጹሐንን እየገደለ፣ ሕዝብን እያፈነና እያሠረ፣ በልማት ስም የምስኪኖችን የመቶ ዓመታት ታሪክ እየነቀለ፤ ከልማዳቸው እያፋታ፣ ከወጋቸው እየነጠለ፣ ከባህላቸው እያጣላ፤ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያልተለወጠ ኀይል በምንም መለኪያ ነው “የልዩ ጥቅም” ችግር ፈቺ ሊኾን የሚችለው?

የአዲስ አበባም ኾነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄ – የፍትህ፣ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ እንጂ “የልዩ ጥቅም” ጉዳይ አይደለም። የልዩ ጥቅም ሐሳብ በራሱ ፍትህን የሚያዛባ፣ እኩልነትን የማይቀበልና ዴሞክራሲን የሚጻረር ነው። በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ከሚያገኙት ጥቅም ውጪ ሌላ “ልዩ ጥቅም” እፈልጋለሁ ማለት ነዋሪውን እንደ ባይተዋር መቁጠር ነው። ያልነበረና የሌለ ባይተዋርነትን መፍጠር ነው። ለፍርድም አይመችም።

“የልዩ ጥቅም” ተጠቃሚ መኾን በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ እኩልነት ያዛባል። ይኼ የእኩልነት መዛባት ደግሞ ኅብረተሰባዊ መናጋትን ይፈጥራል። ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስን ያስከትላል። በከተማዋ እኩልነት የሰፈነበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትህ ማምጣት የሚቻለው ነዋሪዎቹን በከተማዋ ነዋሪነታቸው ሚዛን በመለካትና – በልፋትና ድካማቸው ልክ እንዲኖሩ ለማድረግ የሚያስችል ኹኔታ በመፍጠር እንጂ – በባይተዋርነት መስቀል ላይ እንዲቸነከሩ በመግፋትም አይደለም።

አዲስ አበባ ያገሪቱ የፖለቲካ የሙቀት መለኪያ ከተማ ናት። ንቅናቄዎች ከባሌም ይነሱ ከባቢሌ፣ ከሳህልም ይነሱ ከደደቢት፣ ከጠፈርም ይምጡ ከጠረፍ መክተምና መተከል የሚፈልጉት አዲስ አበባ ላይ ነው። አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ማዕከላዊ ነርቭ ናት። ይኼ ነርቭ እንዳይነካ ሁሉም ዜጋ መጠንቀቅ አለበት። አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያንን ዕጣ ፈንታ መወሰኛ ማዕከል ናት። የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ሚና ኩታ ገጠም ነው፤ እንዲያውም ወደ ሳንቲም ግልባጭነት ሳይጠጋ የሚቀር አይመስለኝም። አዲስ አበባ የማትወክለው የኅብረተሰብ ክፍል የለም። የሁሉ ቤት – የሁሉ ማደሪያ ናት።

የሕወሓት “የልዩ ጥቅም” ፖሊሲ በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የኾነ የሞራል ልሸቀት እንዲንሰራፋ በማድረጉ ለከፍተኛ ጥቃት የተጋለጠች ከተማ ናት። “በይዞ መገኘት” እና “በጥሎ ማለፍ” – ሥርዐት ዐልበኝነት የተለከፉ ብዙ ሰዎችን እያስተናገደች ነው።

አንድ ወዳጄ “አዲስ አበባ እንዴት ከረመች?” ስለው ያለኝን ላካፍላችሁ።

“አዲስ አበባ ከፍተኛ የኾነ የስግብግብነት ቀውስ ውስጥ እንዳለች ከሚያሳዩህ ነገሮች አንዱ፦ የትራፊክ እንቅስቃሴው ነው። ወደ ደሴቱ ለገባው ቅድሚያ ስጥ የሚለው ሕግ አዲስ አበባ ላይ ጅልነት ነው። ሞኝነትና ከርፋፋነት ነው። ሁሉም ሰው የሚፈልገው መቅደም ብቻ ነው። ቅድሚያ መስጠት ለሚገባው ቅድሚያ ሳይሰጥ በተቆላለፈ የመንገድ ሥርዐት ውስጥ ሊቀድም ይፈልጋል። ልክ እንደ ኢሕአዴግ። ፓርቲው ውስጥ ያለው የስግብግብነት መንፈስ ፈንድቶ የአዲስ አበባን ጉሮሮ አንቆታል።” ነበር ያለኝ።

“የልዩ ጥቅም” ፖሊሲ አራማጆች ቢልዮን ዶላር መዝባሪዎችናን 100 ሚልዮን ተመዝባሪዎችን ፈጥሯል። የሃይማኖት ሰዎች ሳይቀሩ ሚልየነር የመኾን ሩጫ ላይ ናቸው። ብዙዎች ስለካዝናቸው እንጂ ስለ መንፈሳዊ ተግባራቸው ግድ የላቸውም። የልዩ ጥቅም አዚም በጋርድ የሚጠበቁ ጳጳሳትንና ፓስተሮች አንበሽብሾናል። ራሳቸውን ከእነ ዋይን ሩኒ ጋራ በማወዳደር “አጋንንት ላባረርኹበት 20 ሚልዮን ሲያንሰኝ ነው” የሚሉ ኮሚክ ፓስተሮችንም አፍርቶልናል። ከምዕመናንም ባሻገር የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዲያቆናትን በድግሪና በማስተርስ በሚያጠምቁ ፓስተሮች የአዲስ አበባ ቆዳ ሲገሸለጥም ተመልክተናል።

የአማኞችን አስራትና በኩራት – መባና ስለት ለመብላት የሚራኮቱ ሽጉጥ ታጣቂ ቄሶችንም ያየነው በዚሁ የልዩ ጥቅም የፖለቲካ ዘመን ነው። በተፈጠረው ማኅበራዊ ምስቅልቅል ለስነ ልቡና መቃወስ ችግር የተጋለጡ ወጣቶችን በአደባባይ በመስቀል የሚገርፍ ‘ትምህርትና መምህር” የተመለከትነውም በዚሁ “የልዩ ጥቅም” የበሽታ ዘመን ነው።

“ልዩ ጥቅም” አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ያደርጋል። እኩልነትን ያደፈርሳል። ሁለት ዐይነት ዜጋ ይፈጥራል። ጥቂቶችን ባለቤት – ሚልዮኖችን ደግሞ ባይተዋር ያደርጋል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በጥቂቶች እጅ ላይ መኾኑ የአደባባይ ሐቅ ነው። እነዚህ ጥቂቶች በ“ልዩ ጥቅም” ቁማር ያበዱ ናቸው። እነዚህ ጥቂቶች በአንድ ቀን አዳር ለአንድ ግለሰብ 547 ሰዎችን ሰብስበው ሕግ የሚያወጡ ናቸው። እነዚህ ጥቂቶች፦ የሚቃወማቸውን ሁሉ “በሽብርተኝነት” መዝገባቸው ላይ የሚያሰፍሩት ናቸው። እነዚህ ጥቂቶች፦ ያስራሉ፣ ይገርፋሉ፣ ይመዘብራሉ፤ ይገድላሉ።

“በልዩ ጥቅም” ሰንጢ በባይተዋርነት የሚወጉት ደግሞ 20 ሚልዮኖቹ ረሃብተኞች ናቸው፣ አንድ – ሁለት – ሦስት ሚልዮኖቹ በዓለም የተበተኑ ስደተኞች ኾነዋል፤ 17 ሚልዮኖቹ ሥራ አጦች ናቸው። 100 ሚልዮኖቹ ስኳርና ዘይት በራሽን ካርድ የሚከፋፈሉ ናቸው። እነዚህ ቁጥሮች የሚናገሩት አንድ ሐቅ ቢኖር፤ ሥርዐቱ በ26 ዓመት ጉዞው ማኅበረሰቡን 40 ዓመት ወደኋላ እንዲመለስ ማድረጉን ነው።

ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተነቅሎ መውደቅ ያለበት እንዲህ ያለው “በልዩ ጥቅም” አስተሳሰብ ላይ የተገመደ ባላባታዊ “የሌባና የቀማኛ” ባህል ነው።

ስለ “ሌባና ቀማኛ” አዲስ አድማስ አንድ ጽሑፍ አውጥቷል። ጽሑፉ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስለነበር አንድ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ይዳስሳል። ፈላስፋው ወልደ ኅይወት ነው፤ ከመምህሩ ከዘርዐያዕቆብ ጋራ ያላቸውን ምስስሎሽና ልዩነትም ያናጽራል። ጸሐፊው ለዚህ መጣጥፉ “የተዘነጋው ወልደኅይወት” የሚል ርዕስ ሰጥቶታል። በመጣጥፉ ላይ ፈላስፋው ዘርዐያዕቆብ ፍልስፍናን ከሥነ ጽሑፍ ጋራ አጋብቶ ወንበር እንዲኖር ያደረገ መኾኑን ይነግረናል፤ ወልደ ኅይወት ደግሞ ከዘርዐያዕቆብ በተሻለ “የሴቶች መብት እስከ ወሲባዊ ስሜጥ መጠበቅ ድረስ ሊከበር” ይገባዋል ብሎ የኦሪጂናል ሐሳቡ ባለቤት መኾኑንም ይነግረናል። ጸሐፊው ብሩህ ዓለምነህ ይባላል። የፍልስፍና መምህር ነው። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከፍልስፍና ጋራ የተያያዙ መጣጥፎችን ያቀርባል። “የኢትዮጵያ ፍልስፍና – የወልደ ኅይወት ሐተታዎች ትንታኔ ከእነ ሐተታቸው” የሚል መጽሐፍም ጽፏል። በመጣጥፉ ላይ የቀረቡትን ብዙ ሐሳቦች ለእናንተ እንድታነቡት ልተውና አንዲት ሰበዝ ብቻ ስቤ ልጋብዛችሁ። 
ብሩህ ዓለምነህ የኢትዮጵያን ፍልስፍና በማጥናት የሚታወቁት ካናዳዊው ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር ስለ ወልደ ኅይወት ያሉትን ይጠቅሳል። ክላውድ ሰምነር በወልደ ኅይወት ሁለት ነገሮች ይመሰጣሉ። 
አንድ፦ በማስተማር ስነ ዘዴው፤ 
ሁለት፦ ለሥራና ለእጅ ሞያ ባለው ጽኑ አቋም። 
የሰምነር ምስክርነት እንዲህ የሚል ነው፦ 
“ምንም እንኳ የወልደ ኅይወት ሐሳቦች በመሠረቱ ከዘርዐያዕቆብ የወሰዳቸው ቢኾኑም፤ ሐሳቡን ለሰው በማስረዳት ረገድ ግን ወልደ ኅይወት በጣም የተዋጣለት ነው። በተለይ ምክሮችንና ተግሳጾችን በምሳሌና በወግ እያጀበ የሚያቀርብበት መንገድ ሲበዛ መሳጭ ነው። የማኅበረሰቡን ስነ ልቡናም ያገናዘበ ነው። በአጠቃላይ ወልደ ኅይወት ምርጥ መምህር ነው።”
ልብ በሉ እንግዲህ፦ ይኼ ሰው በ17ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ይኖር የነበረ ወልደ ኅይወት የሚባል ፈላስፋ ነው። 
ሌላው ወልደ ኅይወት በሥራና በእጅ ሞያ ላይ ጸኑ አቋም ነበረው። የመሬት ከበርቴው የጭሰኛውን ጉልበት በሚበዘብዝባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ፤ የእጅ ሞያ መሰደቢያ በኾነባት ኢትዮጵያ፤ የጉልበት ሥራ ለመኳንንት ልጆች አይገባም በሚባልባት ፊውዳላዊት ኢትዮጵያ ላይ ወልደ ኅይወት ሥል እጅ ሞያ የጻፈው ነገር እጅግ አስደናቂ ነው። 
በሐተታው ምዕራፍ 18 ላይ እንዲህ ይላል፦ 
“የእጅ ሥራን መሥራት ወደድ፤ ከአኗኗርህ ጋር ይስማማልና። የእጅ ሥራ መሥራት አትፈር። ያል እጅ ሥራ የተፈጠረ ሰው ሁሉ ይጠፋል፤ አኗኗሩም ይፈርሳል። ‘የእጅ ሥራ መሥራት ግን ለድኾችና ለገበሬዎች፤ ለአንጥረኞችና ለግንበኞች፤ ለገባርም ልጆች የተገባ ሲኾን ለታላላቆችና ለከበርቴ ልጆች ግን አይገባቸውም አትበል። የሰው ልጅ ሁሉ በፍላጎቱ እኩል ነው። እንደዚህ የሚል ኅሊና ከትዕቢተኛ ልብ የሚመነጭ ነውና። መሥራት እየተቻለው የሌላውን ድካም የሚበላ ግን ሌባና ቀማኛ ነው። አንተ ግን ከትንሽነትህ ጀምረህ የእጅ ሥራን መሥራት ልመድ።” 
ይኼን የወልደ ኅይወትን ሐሳብ ክላውድ ሰምነር እንዲህ በሚል አስቀምጥጠውታል፦ “በፊውዳላዊ ኢትዮጵያ የሥራ ባህል ላይ የተሰነዘረ አብዮታዊ ሐሳብ”። 
ወልደ ኅይወት ይኼን ትችት ያቀረበው በ17ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ይህ ምክርና ተግሳጽ ከተጻፈ ከ400 ዓመታት በኋላም የወልደ ሕይወት አብዮታዊ ሐሳብ አልተወለደም። ዛሬ ከሚሠሩ እጆች ይልቅ የሚያወሩትን የማያውቁ ምላሶች ሹመትና ካባ ይደረብላቸዋል። በላብ ከመበልጸግ ይልቅ “በሰው ልጆች ደም መታጠብ” ያስሾማል፤ ያሸለማል፤ ከበርቴ ያደርጋል። ይህ የግንቦት 20 ፍሬ ነው። 
“በልዩ ጥቅም” ዙርያ በሚሰባሰቡ ሰዎች ዘንድ ከሚሠሩ እጆች ይልቅ የሚቀሳፍቱ ምላሶች ተፈላጊዎች ናቸው። ለዚያም ነው አቶ መለስ ዜናዊ “ሌብነት ሥራ ነው” የሚል አዋጅ አውጆ የሚያነበንቡ እንጂ የሚሠሩ ሰዎችን ያልሰበሰበው። 
በዚህም ዋናውን “ልዩ ተጠቃሚ”ነት አቶ መለስ ለበኹር ልጁ “ለሜቴክ” ሰጠው። ይኼ የአቶ መለስ ርምጃ አንድ ከኮሎኔል በላይ ማዕረግ ያለውን የቀድሞ በረኸኛን የቪ – 8 መኪና ባለቤት አደረገ። በ65 ሺሕ ዶርላ (በ1.6 ሚልዮን ብር) የቤት መኪና የሚገዛ ቅንጡ ወንበዴዎችን አፈራ፤ የውንብድና ተቋም ገነባ። ይኼን ለማረጋገጥ ከፈለጋችኹ አዋሬ አካባቢ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ “ባለማረጎች” መንደር ጎብኙ። የአቶ መለስ ርምጃ ብዙ ሕንጻ የሚያመርቱ ሌባና ቀማኛ “ጀነራሎችን”ም ፈጥሯል። 
ውድ የማማ ተከታታዮች፦ በአዲስ አበባ ላይ በይደር የተያዘውን “የልዩ ጥቅም” አዋጅ ምክንያት በማድረግ ከዚህም የብዙ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን ሊያስብል የሚችል ነው። ይህን ጉዳይ በርግጥም በሁለት መሰናዶ መጨርስ “ዐባይን በጭልፋ” ዐይነት ነው። ጉዳዩን ከግል ልምዴ ጋራ የያዝኹት እኔ በግሌ ከተማርኩትና ከተገነዘብኹት የተሻለ ምሥክር ላለመጥራት ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሥራም በጓደኝነትም የማውቃቸው ኦሮሞዎች ሩኀሩህ፣ ደግና ከትርፋቸው የሚሰጡ መኾናቸውን አውቃለሁ። ማንነታቸው፣ ሰብዕናቸውና ባህላቸው ውስጥ ሌብነትና ቅሚያ አላየሁም። የልዩ ጥቅም እስረኞች ኾነውም አላገኘኋቸውም። 
የአዲስ አበባ መንደሮች ስም መቀየር ጉዳይ፦ የእኔ ሰፈር ብቻ ሳይኾን የብዙ መንደሮችን ማንነት፣ ባህልና ማኅበራዊ ትስስር ከስሩ ነቅሎ ያጠፋል። የ’ያንዳንዳችን ማንነትና ባህል ተሠርቶ የሚጠናቀቀው በትንሿ መንደራችን ውስጥ ነው። ለመኾኑ የመቶ ኻያ ዓመት የመንደሮች ታሪክ እየሰረዝን . . . ወደፊት ለመራመድ የምንችለው እንዴት ነው? 
ህወሓት/ኢሕአዴግ ላለፉት 26 ዓመታት ሲተገብረው የቆየው “በልዩ ጥቅም” የተተበተበ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም 26 ዓመት ወደፊት እወስዳለሁ ብሎ 40 ዓመት ወደ ኋላ ከመለሰን 120 ዓመት ወደ ኋላ ሊመልሰን የተዘጋጀው “የልዩ ጥቅም” አዋጅ ስንት ዓመት ወደ ኋላ ይወስደናል? ምናልባት ፈላስፋው ወልደ ኅይወት ወደነበረብት ወደ 17ኛው ክፍለ ዘመን? 400 ዓመት ወደ ኋላ???

ማስረሻ ማሞ ነኝ
በቸር ሰንብቱ!

Share this post

One thought on “የአዋጅ ረቂቁ – ኦሮምኛ ቋንቋን አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ “ሰምተውት የማያውቁት ልሳን” አስመስሎ አቅርቦታል። (ማስረሻ ማሞ ነኝ)

 1. የኢትዮጵያወርቅ (የሐረርወርቅ) ጋሻው
  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቅ የሚገባ፣ ዛሬ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋናው፡-
  በኦሮሞው ስደተኛ ስም የሚፈጸም ግፍ የኦሮሞን ብሔር በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ያለውን ሳይሆን ከኢትዮጵያም ውጪ የጎረቤት አገሮች አገሩ በመሆኑ በሕዝባቸው ቆጠራ በሚታወቅበት ጭምር አደጋ ላይ ጥለውት ይገኛል፣ ከወለጋ የወጡት ጥቂት እንክርዳዶች ኦነጎች። ይሄንን ጉዳይ አስመልክቶ እና ሌላውን ኦሮሞ እነዚህ የወለጋ ኦነጎች እንዴት እንደሚያዩት እንደሚርቁት በቅርብ በሰፊው እመለስበታለሁ።
  ፩ኛ፡-
  “ኦሮሞኛ መነጋገር በደርግ ጊዜ ክልክል ነበር፣ በንጉሱም ጊዜ እንዲሁ፣ ማንም ከቤቱ ውጪ በይፋ እንዳይነጋገርበት ይከለከል ነበር።” ይላል።
  አይ ውሸት! እንደው ለካስ የአጎቴ የእናቴ ታላቅ ወንድም ሃደኛቱ የሚለው እውነቱን ነበር ማለትም እናት በሊታ። ኢትዮጵያን እናቱን በሊታ ለማለት ነው።
  ፪ኛ፡-
  ባለፈው አመት እንደጻፉት አሁንም “በደርግ ግዜ መንግስቱ ኃይለማርያም ስልጣኑን ተጠቅሞ ኦሮሞኛን በአማርኛ፣ በትግሪኛ እና በጉራጌኛ ቀይሮት ነበር። በሃሉም የእነዚህ የሶስት ብሄሮች ብቻ እንዲሆን ኦሮሞውን ሲያስገድደው ኖርዋል ይላል።”
  አቤት ቆርጦ ቀጥልነት፣ ሕሌና ማጣት። እውነት እነዚህ የኢትዮጵያ ኦሮሞች ናቸው ወይስ የሶማሌ፣ የኬኒያ፣ የዩጋንዳ ወይስ የሱዳን እራሳቸውን እነሱ እያስቀመጡ እንዳሉት። የኢትዮጵያ ኦሮሞዎች እንዴት እንደሚያስቡ ከዚህ በታች ባጭሩ አስቀምጠዋለሁ ከሃቅ በመነሳት በተለመደው።
  በኦሮሙኛ ሳምንታዊ የሬዲዮ ስርጭት በደርግ ጊዜ ተጀምሮ ይተላለፍ ነበር እንኳን ሊከለከል! ሃቁ በማስታወቅያ ሚንስትር መስሪያ ቤት በጊዜው የነበራችሁ ጋዜጠኞች ለሃቅ የምትመሰክሩ እና ቴፑ እራሱ በኦሮሙኛ ይተላለፍ የነበረው ስርጭት በኢትዮጵያ ሬድዮ ምስክር ነው። ኦነገ እና ጉፋያዎቹ ወዴት ሊገቡ ነው። ዜናውን እና ፕሮግራሞቹን ሲያዘጋጁ እና ሲያቀርቡ የነበሩት ጋዜጠኞች በሕይወት አሉ እኮ።
  ጥቂት ልበል ለመነሻ፡-
  *** እንደሚታወሰው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን በስልጣን ላይ እያሉ እና ከስልጣንም ከወረዱ በኋላ ማግኘቴ ግልጽ ነው። ከስልጣን ሳይወርዱ ከአንድ አመት በፊት፡ በአገራችን በአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤታቸው በይፋ በኢትዮጵያ፡ በሕዝቧ እና መከላከያ ሰራዊቷን እና ሰላም እና እርቅ ከገንጣዮች ጋር እንዲደረግ ጭምር በማስብ የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅ አሳስቦኝ ላለፈው 26 አመት እየሄድነው ያለንው አሳዛኝ ሁኔታ በወያኔ እየተፈጸመ ያለው እንዳይፈጠር በማሰብ፡ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ጋር ሃሳብ መለዋወጤ አይረሳም።
  ታዲያ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ሚዲያ የተመለከቱት ጉዳዩን፡ ለእኛም ድምጻችንን ታሰማለን ብለው፡ የሸዋ ኦሮሞዎች በጊዜው እርዳታ ማስተባበሪያ ይሰሩ በነበሩ እኔን በቅርብ የሚያገኙ ኦሮሙኛ ተናጋሪ የአቃቂ ኗሪ በሆኑት ወንድም አማካኝነት፡ እሳቸውን የሚያውቁ ባስተባበሩት ፡ የአቃቂ እና የአዲስ አበባ፣ የሰላሌ፣ የሸኖ፣ የአንቦ እናም የሰንዳፋ ሰዎችን ያካተተ ኮሚቴ ቀደም ብሎ የነበረ ተሰሚነት አጥቶ በተስፋ ይጠባበቅ የነበረ ጥሪ ባደረገልኝ መሰረት እርዳታ ማስተባበሪያው ውስጥ በነበሩት ወንድም አማካኝነት ተነግሮኝ አብረን በመሄድ በስብሰባው በመገኘት ሃሳባቸውን እና ኮሚቲውን ወክዬ በእየሳምንቱ የሚተላለፈው ኦሮሞኛ ለወለጋዎች ብቻ እንጂ ለእኛ ስለማይገባን ይቀየርል ብለው የጻፉትን እና እኔንም እንድትወክለን ሃላፊነት ውክልና ሰጥተናታል የሚል ጽፈው ፈርመው የሰጡኝን አምኜበት፡ ሰፋ ካለ ሃሳብ መለዋወጥ በኋላ ጠያቂዎቹ የሚሉትን ይዤ ወደ ሚመለከተው ማስታወቂያ ሚንስትር አቅርቤ በመጨረሻም ለኮሎኔል መንግስቱጋ ጉዳዩን ከሚንስትሩ ጋር በመተባበር አቅርበን ጉዳዩ ተቀባይነት አግኝቶ ነበረ። ይሄውም የወለጋውን ኦሮሙኛ ስርጭት እንዳለ ሆኖ ብዙሃኑ በሚሰሙት ኦሮሙኛ እራሱን የቻለ ሌላ የሬዲዮ ስርጭ ቅዳሜ ቀን እንዲቀርብ ተወሰነ ማለት ነው።****
  እስከዚህ ነው እንግዲህ ኦሮሙኛ በህግ ክልክል ነበር በሚል ዛሬ ኦነጎች እያስተጋቡ ያሉት። በጊዜው የነበራችሁ ጋዜጠኞች በሳምንት አንዴ እሁድ እሁድ ኦሮሙኛ ይቀርብ እንደነበረ የምታውቁ ኦነግን ቶሽ! ልትሉት ይገባል። ገነጣጣዮች ከወለጋ የወጡት ጥቂት እንክርዳዶች የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪን እና የኤርትራን ሕዝብ ነፃ አውጪን የኦሮሞ ነፃ አውጪ በሚለው ስማቸው እየመሩ የኢትዮጵያ ቤተመንግስት አስገብተው ትልቁን የኦሮሞ ሕዝብ ትንሽ አድርገው በጉልበት ቁጭ አሉ እንደነሱ አይምሮ በክልል አስቀመጠው። ከዛም አሳልፈው በክልል ሸጠውት ወጡ እነዚህ ወንጀለኞች። አሁንም መኖሪያቸው “ኦሮሞ” ነው።
  በመጨረሻም ፡ እንደሚታወቀው አንድም ቀን አንድም የኢትዮጵያ መንግስት ወይም መሪ እራሱ ኦሮሙኛውን ወደ ቤተመንግስት በጎንደር አስገብቶ የቤተመንግስቱ ቋንቋ ከማድረግ ውጪ፡ ኦሮሙኛ በህግ ይቅር እና በድብቅም ክልክል እንዳልነበረ በሚገባ ከኦሮሞው የተወለደው ቤተሰብ ጭምር የሚያውቀው ነው። የከለከለ መንግስት የለም!። ለኢትዮጵያ የቆምነው ማስረጃ በሚሊዮን የሚቆጠር አለን አገራችንን ኢትዮጵያን ለሕዝቧ የኢትዮጵያ ባለቤትነቱን ለማስከበር።
  ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
  የኢትዮጵያወርቅ (የሐረርወርቅ) ጋሻው
  ዘብሄረ አንዲት ኢትዮጵያ!
  Yehar9@aol.com

  Reply

Post Comment