የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት አንድ ጊዜ በቋሚነት በአዲስ አበባ ብቻ እንዲካሄድ ተወሰነ

Source: https://fanabc.com/2019/02/%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8D%8D%E1%88%AA%E1%8A%AB-%E1%88%85%E1%89%A5%E1%88%A8%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%8C%89%E1%89%A3%E1%8A%A4-%E1%89%A0%E1%8B%93%E1%88%98%E1%89%B5/

አዲስ አበባ፣የካቲት 5፣2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት አንድ ጊዜ በቋሚነት በአዲስ አበባ ብቻ እንዲካሄድ ተወሰነ።

በ32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ህብረቱ እያካሄደ ባለው ሪፎርም መሰረት የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በዓመት ስንት ጊዜ እና የት ይካሄድ በሚለው አጀንዳ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚሁ መሰረትም  በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ሪፎርም መሰረት የህብረቱ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ ነው የተገለፀው።

ከሪፎርሙ በፊት የህብረቱ  መሪዎች ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በየስድስት ወራት ልዩነት በአዲስ አበባ እና በዙር በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት  ከተሞች ሲካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።

በአዲሱ ውሳኔ  መሰረትም ቀጣዩ 33ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ጥር 21 እና 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል ።

የዘንድሮው  የህብረቱ መሪዎች ጉባኤ ውሳኔ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና የሰጠመሆኑ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ውሳኔው  ኢትጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ ተቀባይነት ያገናዘበና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ያሰጠበቀ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.