የአ/አበባ ሀ/ስብከት እንዘጭ እንቦጭ! በመዝባሪነቱ የተነሣው ኤልያስ ተጫነ ለ3ኛ ጊዜ በሒሳብና በጀት ሓላፊነት ተመደበ፤ ለውጥ ፈላጊዎች ሁሉ ሊቃወሙት ይገባል

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2018/08/12/%E1%8B%A8%E1%8A%A0-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%88%80-%E1%88%B5%E1%89%A5%E1%8A%A8%E1%89%B5-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%98%E1%8C%AD-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%89%A6%E1%8C%AD-%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8B%9D/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2018/08/lique-tebebit-elias-techane.jpg

lique-tebebit-elias-techane

 • ባለፈው ሰኞ ከተመደቡት 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች አንዱ ነው፤
 • የሒሳብና በጀት አሠራሩ፣ የሀ/ስብከቱ ለውጥ ዋነኛ ማሳያ ነበር
 • ለውጡን የማያሳካ፣ ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ምደባ ነው
 • ከጉድና ጉደኞች እንዳይወጣና እንዳይለወጥ የተረገመ መስሏል

†††

 • አጥቢያዎችን፣ የ112 ሚሊዮን ብር የፈሰስ ባለዕዳ ያደረገ ነው፤
 • ደመወዝ ለማጸደቅ የወር ጭማሪውን በጉቦኝነት ሲበላ ኖሯል
 • የዘመናዊ ቤቶችና ፎቅ፣የባንክ አክስዮንና ግሮሰሪ ባለቤት ነው
 • ለውጥ ፈላጊ ካህናትና ምእመናን ሁሉ፣ሊቃወሙት ይገባል!

†††

ቤተ ክርስቲያናችን በአስተዳደር ስለሚያስፈልጋት የለውጥ አመራር፣ በየስብሰባው እየወተወቱና መግለጫ እያወጡ በተግባር ግን አፈጻጸሙን ማደናቀፍ፤ በቀኖናም በሕግም ሊጠየቁና ሊቀጡ ስለሚገባቸው ግለሰቦች ሕጸጽና ጥሰት በዐደባባይ እየበየኑ በስውር ግን፣ በጎጠኝነትና በጉቦኝነት መሾምና መሸለም ቤተ ክህነታችን የተዘፈቀበት ነባራዊ ተቃርኖ(አያዎ) ነው፡፡ ለችግሩ በዋነኛ ማሳያነት ለሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የዋና ክፍል ሓላፊዎችን ለመመደብ፣ ሰሞኑን በመንበረ ፓትርያርኩ የታየው መራኰት ይህንኑ መስተፃርር የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በጅግጅጋና አካባቢው የነውጠኞች አሠቃቂ ግድያና ውድመት፣ ቤተ ክርስቲያን ሐዘኗን ገልጻ ባወገዘችበት ባለፈው ሳምንት ሰኞ የተካሔደው የቋሚ ሲኖዶሱ ስበሰባ፥በአስተዳደር በደል፣ የአሠራር ጥሰትና ሌብነት በተወገዱት 14 የአ/አበባ ሀ/ስብከት የዋና ክፍል ሓላፊዎች የተተኩት ግለሰቦች ምደባ ጉዳይ ዳግመኛ ታይቶ ውሳኔ ያገኘበት ነበር፡፡

በአዲሱ ሥራ አስኪያጅ የአቀባበል ሥነ ሥርዐት ንግግር ላይ በተጠቆመውና ከዚያም በኋላ በተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት፣ የአስተዳደር ጉባኤን በሞያዊ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው በተሻሉ ሓላፊዎች ለማደራጀት፤ ሌብነትንና ጎጠኝነትን በማጥፋት በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝ፣ በስብከተ ወንጌልና በልማት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስበትን ተቋማዊ ለውጥ ለማሳካት ዕድል የሚያገኝበት ምደባ እንደሚኾን ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡

የምደባው ዝርዝርና ውጤቱ ሲገለጽ ግን፣ ሒደቱን በርቀትም በቅርበትም ሲከታተሉ የቆዩ የጠቅላይ ጽ/ቤት፣ የሀገረ ስብከት፣ የክፍላተ ከተማና የአጥቢያ ካህናትና ሠራተኞችን በእጅጉ አሳዝኗል፤ አስቆጥቷልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን፥ በተሰጣቸው ሓላፊነት ውጤታማ የኾኑ፣ ብቃታቸውን ያሳዩና በላባቸው የሚያድሩ ብቁ ባለሞያ አገልጋዮች እያሏት እንደሌሏት ያህል፣ አዲስ አደረጃጀትና ምደባ ባለበት ኹሉ የሚመላለሱ ‘ጆከሮች’ ኹነኛ ቦታዎችን በጎጠኝነት የያዙበት፣ ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ምደባ ነው፡፡

“የኔ ወገን/ኔትወርክ/ ካልገባ ቃለ ጉባኤውን አልፈርምም” እስከ ማለት ድረስ የተሰማውን ፍጥጫና ቡድነኝነት በጉልሕ ያሳበቀ ምደባ ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት፣ ልዩ ሀገረ ስብከቱን በበላይነት በሚመሩት በፓትርያርኩ በራሳቸው መመሪያ፣ በሌብነቱ ተነሥቶ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተዛወረው ዘራፊው ሊቀ  ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ ለ3ኛ ጊዜ የሒሳብና የበጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ኾኖ የተመደበበት ጥቅምን የማስቀጠል ሹመት ነው፡፡“እነ እገሌን ሠራሁላቸው፤ አሁንም ማንነቴን አሳያቸዋለሁ” እያለ የሚደነፋበትን የበቀል ተልእኮ ያዘለ ምደባ ነው፡፡


ለአ/አበባ ሀ/ስብከት የተመደቡት 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች ዝርዝር

 1. ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ – የበጀትና ሒሳብ ክፍል ዋና ሓላፊ

 2. ሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ – የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ሓላፊ

 3. መጋቤ ጥበባት ሲያምር ተክለ ማርያም – የሰው ኃይል አስተዳደር ሓላፊ

 4. መልአከ ብርሃናት ፍሥሓ ጌታነህ – የቁጥጥር አገልግሎት ሓላፊ

 5. መ/ር ዓይናለም ተጫነ – የዕቅድና ልማት ዋና ክፍል ሓላፊ

 6. መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚእ አሰፋ – የትምህርት ዋና ክፍል ሓላፊ

 7. መ/ር ቀጸላ ጥላሁን – የሕግ አገልግሎት ዋና ክፍል ሓላፊ

 8. መልአከ ሰላም ልዑል በላይ – የመንፈሳዊ ፍ/ቤት

 9. አባ ላእከ ማርያም – የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ

 10. መ/ር ቀለም ወርቅ – የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ

 11. መ/ር ሱራፌል ተፈራ – የሰንበት ት/ቤቶች ማዳራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ

 12. መ/ር ሲሳይ ኦብሴ – የቅርስና ቱሪዝም ዋና ክፍል ሓላፊ

 13. መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ – የምግባረ ሠናይ ዋና ክፍል ሓላፊ

 14. መጋቤ ሃይማኖት መሠረት አያሌው – የጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊ


ከማኅደሩ እንደሚታየው፣ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ ለምደባው አግባብነት ባለው የአካውንቲንግ ሞያ ያስያዘው የትምህርት ዝግጅት፣ ከዲፕሎማ ያለፈ አይደለም፡፡ በዚህም ቢኾን፣ በሀገረ ስብከቱ በሓላፊነት በቆየባቸውና በተደጋጋሚ እየተመላለሰ በተመደበባቸው ኹለት ዐሥርት ዓመታት፣ በምዝበራ ራሱን ከማበልጸግና የቤተ ክርስቲያንን ገንዘብ ለብክነት ከመዳረግ በቀር የሚጠቀስ የአሠራር ለውጥ አላስመዘገበም፡፡

ዘመናዊውን የሁለትዮሽ የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት በጽ/ቤቱ እንደዘረጋ ይመጻደቃል፤ በቲፎዞዎቹም ይደለቃል፡፡ እውነታው ግን፣ በእርሱ ሥልጠና ለሞያው የበቃ ባልደረባ እንደሌለና በውጭ ድርጅትና በኋላም ከድርጅቱ ባለሞያዎች በተቀጠረ ሠራተኛ ከፍተኛ ወጪ እየወጣ እየተሠራ መኾኑ ነው የሚታወቀው፡፡ ይልቁንም፣ በግንቦት 2005 ዓ.ም.፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈውን ውሳኔና በቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጠውን መመሪያ ተከትሎ፣ ታላቅ ጥረት የተደረገበትና ከፍተኛ ድጋፍ ያረጋገጠው የመዋቅር፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ ጥናት እንዲሰናከል ከአጥቢያ ሌቦች ጋራ እያሤረ የተንቀሳቀሰ ሻጥረኛ ከመኾኑም በላይ፣ በትሩፋት ሲደክሙ የነበሩትን ባለሞያዎች፣ “ሊያሠለጥኑን ሳይኾን ሊያሠየጥኑን የመጡ” በማለት በመድረክ በግላጭ የዘለፈ ፀረ ለውጥና በቀለኛ ግለሰብ ነው፡፡ ፀረ ለውጥ እንቅስቃሴው በቲፎዞዎቹ እንደ ውለታ ተቆጥሮለት ለአኹኑ ምደባ እንዳበቃው ተጠቁሟል፡፡ ድለላን፣ ልግመኝነትን፣ ኑፋቄንና የቦታ ኪራይ ምዝበራን እንደሚዋጉ በማስታወቃቸው ብቻ ‘የማኅበረ ቅዱሳን አባል ናቸው’ የተባሉትን አዲሱን ሥራ አስኪያጅ የመጠርነፍና እየሰለሉ ለፓትርያርኩ መረጃ የማቀበል ሚና ይኖረዋልም፤ ተብሏል፡፡

 • ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ ከ1992 እስከ 2003 ዓ.ም. እና ከ2003 እስከ 2008 ዓ.ም. የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ኾኖ በቆየበት ከደርዘን በላይ ዓመታት፣ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን፣ ከማንኛውም ገቢያቸው ለሀገረ ስብከቱ የሚከፍሉትን የ20 በመቶ ፈሰስ አየር በአየር እየጠለፈ ለከፍተኛ ዕዳ የዳረገ አንቃዥና አቆርቋዥ ግለሰብ ነው፡፡ በዚህም፣ ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ የአጥቢያዎቹን የፈሰስ ገንዘብ በመቀርጠፍ ባለዕዳ አድርጓቸዋል፡፡ ቆይቶ አጥቢያዎቹ ውዝፉን ሲጠየቁ፣ ከፍለናል፤ ቢሉም አለቀረላቸውም፡፡ ራሱ በሚቆጣጠረው አካውንት የፈሰስ ክፍያውን ገቢ እንዲያደርጉ እያዘዘ የስሊፑን ዋና ቅጅ በመቀበል፤ ከዓመታዊ ኦዲት አስቀድሞ ሒሳብ ሹሞቹን ያለወቅቱ በማዛወርና በመሳሰሉት ዘረፋውን ለመሸፋፈንም ሞክሯል፡፡
 • ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ አጥቢያዎቹ፣ ከዘመኑ ገቢ በተጨማሪ ውዝፉንም እንዲከፍሉ ሀገረ ስብከቱ ዘመቻ አድርጎ በከፊል ለማስመለስ ችሏል፡፡ ኾኖም የፈሰስ ቀበኛው ኤልያስ፣ ለዘመናት የበላውን ውዝፍ በአንዴ እንዲከፍሉ መገደዳቸው፣የልማት አቅማቸውን ተሻምቷል፤ ካህናት፥ የበዓል መዋያ ቦነስ ይቅርና ደመወዝ በወቅቱ እንዳይከፈላቸውና መንፈሳዊ አገልግሎቱ እንዲዳከም በማድረግ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል፤ ቆይቶም በቀጣይነት ለታየው አለመግባባት አንዱ መንሥኤ ኾኖ ተጠቅሷል፡፡
 • ኤልያስ ተጫነ፣ የሀገረ ስብከቱ ሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ እያለ በተከናወነው የሦስት መኪናዎች ግዥ፣ መርሕንና አሠራርን የሚጥስ ተግባር ፈጽሟል፡፡ ራሱ ፕሮፎርማ ሰብሳቢ፣ ራሱ ግዥና ክፍያ ፈጻሚ ኾኖ በከፍተኛ ደረጃ በግሉ የተጠቀመበትን ሕገ ወጥ ድርጊት እንደፈጸመ፣ የ2007 ዓ.ም. የውጭ ኦዲት ሪፖርት አረጋግጧል፡፡ ወጪው፣ ከተገዛው ንብረት ጋራ የማይጣጣም እንደኾነ ያሰፈረው ሪፖርቱ፣ በማይመለከተው ሰው፥ ፕሮፎርማ መሰብሰቡን፣ ግዥና ክፍያ መፈጸሙን አስፍሯል፡፡ ግለሰቡ አላግባብ የመዘበረውን ገንዘብ እንዲመልስ ሀገረ ስብከቱ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ድጋፍ ቢጠይቅም፣ በሚመለከታቸው ሓላፊዎች ምላሽ ሳይሰጠው፣ የኦዲት ሪፖርቱም ደብዳቤውም ተደብቆ ቀርቷል፡፡
 • አድባራትና ገዳማት፣ በየኹለት ዓመቱና የኑሮ ኹኔታው እየታየ የሚስጨምሩትን ስኬልና የደመወዝ እንዲሁም የአበል ጭማሬ ለማጸደቅ፣ የአንድ ወር ጭማሬውን አስቀድመው በእጅ መንሻነት እንዲከፍሉ በማስገደድ ሲመዝበራቸው የኖረው አንቃዡ ኤልያስ ተጫነ ነው፡፡ እርሱ ከተነሣም በኋላ ይኸው እጅ መንሻ ልማድ ኾኖ ቀጥሎ የነበረ ቢኾንም እንደማይቀጥል በአዲሱ ሥራ አስኪያጅ ተገልጿል፡፡ በደመወዝና አበል ጭማሬ ማጸደቂያ ብቻ ያልተወሰነው ኤልያስ፣ “ካህናት ተጎድተዋል” በሚል “የልማት/የሕንፃ አበል” በዓመት አንዴም ኹለቴም እንዲከፈል እያስደረገ ማጽደቂያውን ሲበላ ቆይቷል፡፡
 • ኤልያስ ተጫነ፣ በአጥቢያ ካህናትና ሠራተኞች ደመወዝና አበል ጭማሬ ብቻ ሳይኾን፣ በዋና ክፍል ሓላፊነቱ ያገኝ በነበረው 8ሺሕ ብር ደመወዝ ላይ በራሱ ውሳኔ 3ሺሕ ብር ጨምሮ ደመወዙን 11ሺሕ ያደረገ ራስ ወዳድ ነው፡፡ እስኪነቃበት ድረስም ለአራት ወራት እየተከፈለው ቆይቷል፡፡ ሲነቃበት ከዋና ክፍል ሓላፊነቱ ተነሥቶ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተዛውሮ የነበረ ቢኾንም፣ አላግባብ የወሰደውን ያህል ከደመወዙ እየተቆረጠ እንዲመለስና ጭማሬውም እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡
 • ኤልያስ ተጫነ፣ በየአድባራቱ በራሱና በቤተ ሰዎቹ ስም በተከራያቸው የንግድ ሱቆች አላግባብ እየተጠቀመ የሚገኝ መዝባሪ ነው፡፡ ከደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል እንዲሁም ከቦሌ ቡልቡላ ፍኖተ ሕይወት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቀድሞው አማሳኞች ጋራ የነበረው ግንኙነት፣ የዓመታት የፐርሰንት ፈሰስ ክፍያቸውን አየር ባየር የመብላት ብቻ ሳይኾን፣ በኪራይ በያዛቸው ሱቆችም ጭምር እንደኾነ ይታወቃል፡፡
 • በመጨረሻም፣ አንቃዡ ኤልያስ ተጫነ፣ ከሁለት ዓመት በፊት፣ ከሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊነት እንዲነሣ የተደረገበት አጋጣሚም ከላይ ከጠቅሰናቸው ምዝበራዎች ጋራ የተያያዘ ሲኾን፣ በተለይም በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል የደመወዝ ጭማሬ ማጸደቅ በስጦታ ስም የተቀበለው 104ሺሕ ብር እጅ መንሻ በማስረጃነት ተይዞ ለፓትርያርኩ በቀረበበት የክሥ አቤቱታ ነው፡፡

በፓትርያርኩ የተሰጠው መመሪያም፣ ያጠፋው ጥፋት ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የገዳማት መምሪያ ጸሐፊ ኾኖ እንዲሠራ ነበር፡፡ ቆይቶ፣ ወደ ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት ተዛውሮ በተቆጣጣሪነት ተመድቧል፡፡ የተጠያቂነት ጠረኑ እንኳ በሌለበት ቤተ ክህነታችን፣ ጥፋቱ እንዲጣራ የተላለፈው መመሪያ ተዘንግቶ፣ ይብሱኑ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ምክትል ሓላፊነት ተሹሞም ወደ ሀገረ ስብከቱ የበጀትና ሒሳብ ዋና ክፍል ሓላፊነት፣ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲመለስ እስከተመደበበት፣ ያለፈው ሳምንት ሰኞ ድረስ ቆይቷል፡፡

ኤልያስ ተጫነ፣ በተዘረዘሩት የምዝበራ ምንጮች አማካይነት፣ ከፍተኛ ሕገ ወጥ ሀብት አካብቷል፡፡ ከተቀማጭ ገንዘብ ባሻገር በመቐለ ባለአራት ፎቅ(የገበያ ማእከል) ባለቤት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ብርጭቆ ፋብሪካ አካባቢ በሚገኘው የኮንዶሚኒየም ሳይት፣ ሁለት የንግድ ቤቶችን ገዝቶ በማጋጠም የመጠጥ ግሮሰሪ ከፍቷል፡፡ እዚያው ሳይት ላይ፣ ባለ2መኝታ ቤት ገዝቶ ይኖርበታል፡፡ በለቡ አካባቢ፣ ባለአንድ ፎቅ ዘመናዊ ቤት እንዳለውና ቦሌ ሐያት አካባቢም ሌላ ተመሳሳይ ቤት እያሠራ እንደኾነም ተጠቁሟል፡፡ በአንድ የግል ባንክም፣ ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ ካላቸው የሀገረ ስብከቱና የአጥቢያ አማሳኞች አንዱ እንደኾነም ታውቋል፡፡

እንግዲህ፣ የ14ቱ የዋና ክፍል ሓላፊዎች ምደባ፣ ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው እንደኾነ የሚተቸው፣ ሀገረ ስብከቱን ከመዝባሪዎችና ጎጠኞች አጽድቶ ዳግም ለማደራጀት ከታቀደበት የለውጥ ርምጃ ጋራ ተፃራሪ የኾኑ እንደ ኤልያስ ተጫነ ዐይነት አንቃዦች ያሉበት በመኾኑ ነው፡፡በሌላ በኩል፣ በደካማ የሥራ ተነሣሽነታቸው፣ በሀገረ ስብከቱ ቀድሞ ከነበራቸው ሓላፊነት ተነሥተው ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ የተወሰነባቸው ኹሉ በጎጠኝነት ተመልሰው ኹነኛ ቦታ ያገኙበትም ምደባ ነው፡፡ በአዋኪነትና የአሠራር ጥሰት የቀረበባቸው አቤቱታ ተጣርቶባቸው ከሌላ ሀገረ ስብከት የተባረሩ ኾነው ሳለ፣በመዲናዪቱ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የዋና ክፍል ሓላፊ እንዲኾኑ የጅምላ ዕድል የተሰጠበትም የሰሞኑ ምደባ!!ሞያውና ልምዱ ያላቸው ቢኖሩም፣ ለምደባው ፈቃደኝነት የሌላቸው እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡

ከትላንት በስቲያ ዓርብ በወጣው ደብዳቤ፣የተወገዱት ሓላፊዎች፣ ነገ ሰኞ ንብረት እንዲያስረክቡ የታዘዙ ሲኾን፣ ባለፈው ረቡዕ የምደባ ደብዳቤ የደረሳቸው እነኤልያስ ተጫነም ቢሮ ተረክበው ሥራ ይጀምራሉ፡፡ በአጠቃላይ ምደባቸው፣ የግልጽነትና አርኣያነት መጓደል ብቻ ሳይኾን፣ ለአዲሱ ሥራ አስኪያጅና የለውጥ አመራራቸውም ጋሬጣ ነው፡፡ በመኾኑም፣ ከሥራ አስኪያጁ በተሰሙት ተስፋዎች የተደሰቱ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ልዩ ልዩ ሠራተኞችና ምእመናን ኹሉ፣ እነኤልያስ ተጫነ ለሦስተኛ ጊዜ ተመልሰው የመጡበት ምደባ በአፋጣኝ እርምትና ማስተካከያ እንዲደረግበት የተቃውሞ ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይገባል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም.)

በአ/አበባ ሀገረ ስብከት 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች ምደባ ቅሬታ አስነሣ

 • ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ምደባ በሚል እየተተቸ ነው፤
 • በተደጋጋሚ በጥፋት የተነሡ ሓላፊ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ተመደቡ፤
 • ተደጋጋሚ ሕጸጽና ምዝበራ የታገዱት አስተዳዳሪም ተመለሰ፤

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ በሙስና፣ በአስተዳደር በደልና በአሠራር ጥሰት የተካሔደውን ማጣራት ተከትሎ፣ 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከቦታቸው ቢነሡም፣ በምትካቸው የተደረገው ምደባ፣ ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ነው፤ በሚል ቅሬታ አስነሣ፡፡

በቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ በተቋቋመው ኮሚቴና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በታዛቢነት በተገኙበት ለአንድ ወር በተካሔደው ማጣራት፣ የአድባራት ካህናትንና ሠራተኞችን አላግባብ ከሥራ በማገድና በማሰናበት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙ ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት የቀረበባቸው የዋና ክፍል ሓላፊዎቹ እንዲነሡ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ኾኖም፣ በቦታቸው ከተተኩት ሓላፊዎች መካከል የአንዳንዶቹ ምደባ፣ ከለውጡ ርምጃ ጋራ የማይጣጣም እንደኾነ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ አገልጋዮችና ሠራተኞች ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል፣ ሓላፊነታቸውን አላግባብ ተጠቅመው በመዘበሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ከፍተኛ የግል ሀብት በማፍራትና አስተዳደራዊ በደል በማድረስ የታወቁ ግለሰቦች በተተኪነት መመለሳቸው፣ለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ ነው፤ አገልጋዩንም ዋስትና የሚያሳጣ ነው፤ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

“በሹም ሽረቱ የግብር ይውጣ ሥራ ተሠርቷል፤” የሚሉት ሠራተኞቹ፣ በ2007 ዓ.ም. በሀብት ብክነት፣ ሙስናና ሓላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት ጋራ ተያይዞ በቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው ማጣራት እንዲካሔድባቸው የተወሰነባቸው የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ በአዲሱ ምደባ በዚያው ዋና ክፍል ለ3ኛ ጊዜ መሾማቸውን በመጥቀስ ምደባው ግልጽነትና አርኣያነት የሌለው እንደኾነ ተችተዋል፡፡

“በቂ ጥናት ሳይደረግና መመዘኛ መስፈርቱ ሳይታወቅ ወደ ሓላፊነት የመጡ ሰዎች ናቸው፤” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከተተኩት መካከል፣ ከቀድሞዎቹ ጋራ የጥቅም ግንኙነት እንደነበራቸው የሚወቀሱም በመኖራቸው፣ የሀገረ ስብከቱን የለውጥ ርምጃ የሚመጥን አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

በቅርቡ ተካሒዶ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ፣ ሙስናን፣ ጥቅመኝነትንና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለዘለቄታው የሚፈታ የአደረጃጀት ለውጥ እንዲደረግ መግባባት ላይ ቢደረስም፣ የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ምደባ ሒደቱን የሚያራምድ እንዳልኾነ ጠቁመዋል፡፡ ጥቅመኝነትን፣ ደላላነትንና ኑፋቄን ለማስወገድ ቃል ለገቡት የሀገረ ስብከቱ የወቅቱ ሥራ አስኪያጅም ፈተና እንደሚኾንባቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ከቦታቸው በተነሡት የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ አላግባብ ከሥራቸው ታግደውና ተሰናብተው በአቤቱታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲጉላሉ የቆዩት ካህናትና ሠራተኞች፣ ደረጃቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ታግደው በቆዩባቸው እስከ ሁለት ያህል ዓመታት ያልተከፈላቸው ወርኀዊ ደመወዝም ተሰልቶ እንዲከፈላቸው መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ኾኖም፣ ከታገዱት ሠራተኞች መካከል፥ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፣ በገንዘብ ምዝበራና በከፋ ምግባር ተደጋጋሚ ጥፋት በመፈጸም ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ፣ ጉዳያቸውም በሊቃውንት ጉባኤ እንዲጣራ በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተላለፈባቸው እንደ አባ ነአኵቶ ለአብ አያሌው ያሉ ግለሰቦች ወደ ደብር አስተዳዳሪነታቸው መመለሳቸው ተጨማሪ ቅሬታ ማስነሣቱ ታውቋል፡፡ ከሃይማኖት ሕጸጽና ከሙስና ነጻ መኾናቸው እየታየ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተሰጠውን አቅጣጫ እንደሚፃረርም ጠቁመዋል፡፡ የሓላፊው ጥፋት በስፋት እንደሚታወቅ የገለጹ አስተያየት ሰጭዎች፣ በውሳኔው አስተማሪነት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ ባለመኾኑ በአፋጣኝ ሊጤን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.