የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ሊከበር ነው

Source: https://fanabc.com/2019/08/%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%88%AC%E1%89%BB-%E1%89%A0%E1%8B%93%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%88%8A%E1%8A%A8%E1%89%A0%E1%88%AD-%E1%8A%90%E1%8B%8D/

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 14፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ሆራ ፊንፊኔ” የኢሬቻ በዓልን በአዲስ አበባ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የኦሮሚያ አባ ገዳዎች ህብረትና የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቁ።

የኦሮሞ ህዝብ የምስጋና ቀን የሆነው ኢሬቻ በዓል በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች በዓመት ሁለት ጊዜ ይከበራል።

የመጀመሪያው የክረምት መውጣትን ተከትሎ በውሃማ አካባቢዎች የሚከበር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በበልግ ወቅት በተራራማ አካባቢዎች ይከበራል።

በአዲስ አበባ ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልም በመጪው አዲሱ ዓመት በአዲስ አበባ ለማክበር አስፈላጊው ቅደመ ዝግጅት መጠናቀቁን ነው የኦሮሚያ አባ ገዳዎች ህብረትና የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ዋጋሪ በዓሉን በአዲስ አበባ ለማክበር ለዘመናት ከህዝቡ ሲቀርብ የነበረው ጥያቄ በዚህ ዓመት ምላሽ አግኝቷል ብለዋል።

በዓሉን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጣ በርካታ ህዝብ ይታደመዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል።

በዓሉ የሚከበረው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በጋራ በመሆን ነው ሲሉ የቱለማ አባገዳ እና የህብረቱ አባል አባ ገዳ ጎበና ሆላ ገልፀዋል።

አባ ዱላ ድንቁ ደያስ በበኩላቸው እንዳሉት ለበዓሉ አከባበር ከ20 ሺህ በላይ ፎሌዎች ወይም ወጣት የገዳ ፖሊስ አባላት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ሰላም የማስጠበቅና የማስተባበር ስራ ያከናውናሉ።

ኢሬቻ የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓል በመሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውንም በበዓሉ እንዲታደሙ የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ቀሲስ በላይ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።

ከኦሮሚያ አባ ገዳዎች ህብረትና የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ በተጨማሪ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎችም የበዓሉ ዝግጅት አካል መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.