“… የኢትዮጵያን መንግሥት እድሜ ሊመኝ የሚገባው ትግሬ ነው”… ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ…

Source: http://welkait.com/?p=12160
Print Friendly, PDF & Email

(ምስጋናው አንዱዓለም)

በዚህ ወቅት የአድዋ ድልና መሪው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መታሰቢያነት ስለ ትግራይ ብሄረተኝነት፣ ስለኢትዮጵያ ብሄረተኝነት፣ ስለ ጉራጌ ብሄረተኝነት እና አማራ ብሄረተኝነት ትንሽ ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ እንደሚታየው የትግራይ ብሄረተኝነት ቁንጮ የሆነው ህወሀት የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት ለ42 አመታት ሲዋጋና ሲያደማ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ዋና ማእከል ነው ብሎ ያሰበውን የአማራ ህዝብም ካላጠፋሁ ብሎ ሲያደርግ የቆየው የሚታወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት ለማዳከም እና የአማራን ህዝብ ለመበደል የነደፈው ቅጥ ያጣ እና የታወረ የትግራይ ብሄረተኝነት አሁን አገሪቷን ለማንም ወደማትሆንበት አቅጣጫ እንደመራት ግልጽ ነው፡፡

የትግራይ ብሄረተኝነት በእርግጥ በአማራ ህዝብ መጥፋት ላይ ተመስርቶ የራሱን ስኬቶች ሊጎናጸፍ እና በኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ምትክ ራሱን ሊያንሰራፋ በሚችልበት መንገድ ነው ሲሰራበት የቆየው፡፡ ይሁንና የትግራይ ብሄረተኝነት የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት ለማጥፋት በሙሉ አቅሙ ሲዘምት እና የዛን ጥፋት የተፈረደበትን የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ማእከል የሆነ የአማራ ህዝብ ለማጥፋት ሲታትር በእቅዱ ያላካተተው አንድ ነገር ነበር፡፡ እርሱም የአማራ ብሄረተኝነት ነው፡፡ የትግሬ ብሄረተኞች የአማራ ብሄረተኝነት ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ተነጥሎ በራሱ ይቆማል የሚል መረዳት የነበራቸው አይመስልም፡፡ ስለሆነም የአማራ ብሄረተኝነት ቢነሳ በምን እንከላከለዋለን ወይስ ምን ተለዋጭ እቅድ ይኖረናል የሚለውን አልሰሩበትም፡፡ ይሄ ያልታሰበው የአማራ ብሄረተኝነት ግን በማይታመን ክስተትነት እና ፍጥነት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ንፍቀ-ክበብ ላይ ርእደ-ፖለቲካ አካሄደ፤ እያካሄደም ነው፡፡

በዚህም ሳቢያ የአማራን ብሄረተኝነት በተመለከተ የቆየና የታሰበበት እቅድ ያልነበረው የትግራይ ብሄተኝነት ማጣፊያው አጠረው፡፡ አሁን እየተዋከበ ባለበት ሰአት እያደረጋቸው ያሉትን ነገሮች ስናይም ራሱን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት ጓዳ ለማስገባት እየተጣደፈ ይመስላል፡፡ ለትግራይ ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት የተሻለ ነገር ቀድሞውንም አልነበረም፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በሚለው መጽሀፉ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 1993 ዓ.ም ያሳተመው) ውስጥ ትግሬን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡- “ከቀሩትም የኢትዮጵያ ነገዶች ይልቅ የኢትዮጵያን መንግሥት እድሜ ሊመኝ የሚገባው ትግሬ ነው፡፡” ገብረ ሕይወት የአድዋ ተወላጅ እና አውሮፓ የተማረ፤ በአጼ ምኒልክ ዘመን ሹመኛ የነበረ ትግሬ ነው፡፡ ይህንን ትግሬ የኢትዮጵያን መንግስት እድሜ በተለየ ሁኔታ መመኘት ነበረበት ያለውን ንግግር የጻፈው አጼ ምኒልክ በትግሬ ውስጥ በደል አለማድረሱን፣ የትግሬ ህዝብ በወቅቱ ምኒልክን ማማቱ ስህተት መሆኑን ነቅፎ ከጻፈ በኋላ ነው፡፡ ጸሀፊው ቃል በቃልም የትግሬ “ባላባቶችም ዘወትር እርስ በእርሳቸው ሲዋጉ ይኖራሉ፡፡ ምስኪኑም የትግሬ ባላገር አጤ ምኒልክ ያጣልዋቸው እየመሰለው በሸዋው ንጉሥ ላይ ብዙ ይፈርዳል፡፡ አጤ ምኒልክን የሚያውቅ ሰው ግን ይህንን ሐሜት ሲሰማ ይስቃል፡፡ የቸሩ ምኒልክን ባህርይ የያዘ ሰው ያፋቅራል እንጅ አያጣላም፡፡ ሰውንም ፈጽሞ ሊጎዳ አይችልም፡፡ የማያውቃቸው ሰው ግን በብዙ ክፉ ነገር ያማቸዋል፡፡…. የደንቆሮ ህዝብ ንጉስ መሆን… ሐሜት ያመጣል” (ገጽ 10)፡፡

ይህን የተናረው ገብረ ሕይወት እጅግ ሊታመን የሚገባው ሰው እና ምስክርነቱም ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባው ሰው ነው፡፡ ምክንያቱም ንጉሱን ለማስደሰት ብሎ ይሄንን ተናገረ ተብሎ ስለማይታሰብ፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው እዚያው መጽሀፉ ውስጥ ስለ ትግራይ የኢትዮጵያ ቀደምት ስርነት፣ ስለ ትግሬ ጦረኝነትና ታላቅነት ብዙ ስለጻፈ፡፡ ስለ ትግሬ በድፍረት የጻፈው አባባሉ እንዲያውም ከቀደምት የትግሬ ብሄረተኞች እንደ አንዱ የሚያስቆጥረው ነው፡፡ እናም በዚህም አመክንዮ ስለ ንጉሱና የትግሬ ህዝብ በወቅቱ የተናገረው እውነተኛ ምስክርነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ትግሬ የኢትዮጵያን መንግስት እድሜ (ወይም የኢትዮጵያ መንግስትነት አስተሳሰብ/ ብሄረተኝነት) እድሜ ሊመኝ የሚገባው እንደሆነ በገብረ ሕይወት ቀደምት እይታም አይተናል፡፡ አሁንም ስናየው ለትግሬ ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ውጭ የረዥም ጊዜ ዋስትና የለውም፡፡ ነገር ግን የትግሬ ሊቃን በጊዜያዊ ድል በመታበይ እጃቸው ላይ የነበረውን እድል ማለትም የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት በአስተማማኝነት የመገንባት ስራ አምክነዋል፡፡ በምትኩ ከአጼ ምኒልክ ዳግማዊ ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ (በተለይም በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ) የተሰራውን የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት አበላሽተዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት ወደኋላ 180 አመት ቀልብሰዋል፡፡ አሁን የኦሮሞ ብሄረተኝነት ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ሙሉ በሙሉ አፈንግጦ በራሱ ቆሟል፡፡ የትግራይ ብሄረተኝነት ለጊዜመው ቢሆን በራሱ ጸንቶ ከመቆም አልፎ የኦሮሞን ብሄረተኝነት አፋፍቶ ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት አስተሳሰብ ነጥሏል፡፡ የዚህ በእብሪት የታወረው የትግራይ ብሄረተኝነት የኦሮሞን ብሄረተኝነት እና የትግራይን ብሄረተኝነት በመፍጠር የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት መለመላውን ከማስቀረት አልፎ ሌላ አዲስ ሀይል እንዲፈጠር በሩን ከፍቷል፡፡ ይሄውም በኢትዮጵያ ብሄረተኛነት ተፈትኖ መውደቅ እና በትግሬና ኦሮሞ ብሄረተኝነቶች መፋፋት ሳቢያ ለራሱ ህልውና አደጋ ውስጥ የወደቀው የአማራ ህዝብ ወጣት ልጆች አይቀሬውን፣ የመጨረሻውን እና ሀይለኛውን የአማራ ብሄረተኝነት ፈጥረዋል፡፡ በዚህም አማራ ምርጫ በማጣት የመጨረሻውን የራሱን ሰይፍ መዟል ማለት ነው፡፡

በዚህ ክስተት ግን ቀድሞ እንደተጠቀሰው የትግራይ ብሄረተኝነት ማጣፊያው እንዲያጥረው ሆነ፡፡ ምክንያቱም በማፍረስ ላይ የተመሰረተው የትግራይ ብሄረተኝነት በኢኮኖሚ እና መሰል ጉዳዮች ራሱን ችሎ የሚቆም አልነበረም፡፡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ብሄረተኝቱ ከኢትዮጵያ በመነጠል በራሱ በስኬት መቆሙ ሀቅ ነው፡፡ ግን ዘለቄታዊ እድል የለውም፡፡ አጠፋዋለሁ ያለው አማራ የራሱን ብሄረተኝነት ወደ መገንባት መግባቱ የትግራይን ብሄረተኝነት ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ፣ ጥገኛ እና ተስፋ ቢስ አድርጎታል፡፡

የትግራይ ብሄረተኝነት ከኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ተነጥሎ፣ የአማራ ብሄረተኝነት ለራሱ በቆመበት ሁኔታ ሕይወት አልባ ነው፡፡ ለዛም ይመስላል ለይምሰልም ቢሆን አሁን ገድሎ ወደ ቀበረው የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት አስተሳሰብ ለይስሙላም ቢሆን የመመለስ አዝማሚያ እያሳየ ያለው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ እየወጡ ያሉ ሙዚቃዎችን ብናይ ይሄንን የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት እስትንፋስ ለመዝራት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ የውስጡን ማወቅ ባይቻልም ሑኔታው ዘመቻም ይመስላል፡፡ የትግራይዋ አቀንቃኝ ሄለን በርሀ እንኳ አዲስ “ፊታውራሪ” የተሰኘ ሙዚቃ ብዙ የሚናገረው ነገር አለው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ያለው የትግራይ ሊቃን ስብስብ ከልቡ የኢትዮጵያን ብሄረተኝነት ይቀበላል እና ያራምዳል ተብሎ ባይታሰብም ለህልውናው ሲል ለይስሙላም ቢሆን ማቀንቀኑ ግልጽ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ የመጨረሻውን፣ ምርጫ አልባውን፣ እና ሀይለኛውን የአማራ ብሄረተኝነት መቀልበስ እና መልሶ ወደ ኢትዮጵያ ብሄረተኝነት መወሸቅ ለትግራይ ብሄረተኝነት የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ለዛም ይመስላል አሁን የትግሬ ሊቃን ባይነጋገሩም እንኳ በደመነፍሳዊ ቁርኝት ከኦሮሞ፣ ጉራጌ (እና ሀድያ) እና መሰል ብሄረተኞች ጋር አንድ ላይ ተሰልፈው የምናያቸው፡፡ ስለ እነዚህም ትንሽ ማለት ያስፈልጋል፡፡

የመጨረሻው፣ ምርጫ አልባው እና ሀይለኛው የአማራ ብሄረተኝነት አነሳሱ የህልውና ስጋት ነው፡፡ ነገር ግን አማራ ለራሱ ህልውና በመነሳቱ ብቻ የሌሎችም ብሄረተኞች የህልውና አደጋ ውስጥ እንዲወድቁ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ብሄረተኞች የአማራ ብሄረተኝነት ባልተነሳበት ሁኔታ የህልውና ስጋት ውስጥ ሊወድቁ አይችሉም፡፡ የእነሱ ሕይወት የተመሰረተው በአማራ ብሄረተኝነት አለመኖር፤ በሌላ አነጋገር በአማራ መጥፋት ላይ ነው፡፡ አማራ ለራሱ መቆሙ ግን እነሱንም ጥያቄ ውስጥ ከቷል፡፡ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ፡- የትግሬ ብሄረተኝነት በአማራ ብሄረተኝነት መነሳት ምክንያት ትግራይ ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ አሁን ቅንጡነት ለለመደው የትግሬ ሊቃን ስብስብ ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለትግራይ ህዝብም መልካም አይደለም፡፡ ስለዚህ የአማራ ብሄረተኝነት የትግራይን ብሄረተኝነት የህልውና ስጋት ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ ለዛም ነው የጣለውን የኢትዮጵያ ብሄረተኝነት መልሶ እንዲያንሰራራ በማድረግ አማራውንም ወደዛው ለመመለስ እየጣረ ያለው፡፡

የኦሮሞ ብሄረተኝነት የሳለውን ካርታ ይዞ የራሱን አገር ለመመስረት ወይም ካልተሳካ ኢትዮጵያን አንዲት የኦሮሞ መንደር ለማድረግ የሚችለው የአማራ ብሄረተኝነት በሌለበት ነው፡፡ ብሄረተኛ ያልሆነ አማራ በቀላሉ ወደ ኦሮሞነት መቀየር ይችላል፡፡ ብሄረተኛ የሆነ አማራ ግን ኦሮሞ አልሆንም፣ በራሴ አማራ ሆኘ እቀጥላለሁ ይላል፡፡ በዚህ የአማራ ብሄረተኝነት መነሳትም ምክንያት የኦሮሞ ብሄረተኛ ካቀዳቸው ሁለት እቅዶች አንዱንም አያሳካም፡፡ ለዚህም ነው የኦሮሞ ብሄረተኞች አማራውን “አበጀህ! በል! በል!” እያሉ ወደ ኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ለመመለስ ከትግሬ ብሄረተኞች እና የጉራጌ ብሄረተኞች ጋር እየሰሩ ያሉት፡፡ ለምሳሌ ባህር ዳር ላይ የተካሄደውን የአማራ ሰማእታትን ደም ያረከሰ ዳንኪራ የኦሮሞ ሊቃን ከውጭ አገር እስከ ውስጥ ባርኮት ሰጥተውታል፤ የደቡብ (የጉራጌ ብሄረተኞች) ዋና አስተባባሪ ሆነው ታይተዋል፤ የትግሬ ልሂቃን በወኪላቸው ብአዴን አማካኝነት አቀናብረዋል፡፡

የጉራጌ ብሄረተኞች የተወሰኑ የሀድያ ብሄር ተወላጆችን እና ስብጥር ማንነት ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን በማስከተል እንዲሁም በራስ-ጠል አማሮች በመታጀብ ግንቦት 7 በተባለው ድርጅታቸው አማካኝነት የአማራን ብሄረተኝነት በመፈታተን ላይ ይገኛሉ፡፡ የጉራጌ (እና ሀድያ) ሊቃን ራሳቸውን የትግሬና ኦሮሞ ብሄረተኞች ተፎካካሪ አድርገው ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ በተለይ የጉራጌ ብሄረተኞች በትግሬ ብሄረተኝነት የተነጠቁትን የኢኮኖሚ የበላይነት ለማስመለስ ፖለቲካዊ የበላይነት መቆናጠጥ እንደሚገባቸው ከትግሬ ብሄረተኝነት አፈጣጠርና ጉልምስና ተምረዋል፡፡ ስለሆነም በእነሱ ብሄረተኝነት የሚመራ ውጩ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛ ቅብ የፖለቲካ አሰላለፍ ፈጥረዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ዋና መሳሪያ ተቆጥሮ የነበረው የአማራ ህዝብ ባልታሰበ ጊዜ የራሱን አስተሳሰብ ይዞ በመነሳቱ የእነሱ እቅድ መና ሆኖ ቀርቷል፡፡ በአንጻሩ በኦሮሞ ብሄረተኝነት፣ በአማራ ብሄረተኝነት እንዲሁም በትግሬ ብሄረተኝነት ቁርቁስ መካከል የእነሱ ሚና እንደሌለ እንዲቆጠር የሚሆንበት እድል ተፈጥሯል፡፡ እያሰቡት የነበረውን ራሳቸውን በትግሬ ብሄረተኝነት የመተካት እና ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ህልም ለማስቀጠልም የአማራ ብሄረተኝነት ዋና ጠላት ሆነው ቆይተዋል፡፡ ያለፈውን ሶስት አመት ጉዞ ለተመለከተ በአማራ ብሄረተኝነት ላይ የትግሬ ብሄረተኝነት ካደረሰው ጥፋት የሚተካከል ጥፋት ፈጽመዋል፡፡ ይሄንን የአማራን ብሄረተኝነት ለማክሰም ብዙ ሰርተዋል፡፡ እንዋጋዋለን ከሚሉት የትግሬ ብሄረተኝነት ጋር፣ እናጠፋዋለን ከሚሉት የኦሮሞ ብሄረተኝነት ጋር እና ከብአዴን-ህወሀት ዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት ጋር በማበር የአማራን ብሄረተኝነት እየወጉ ይገኛሉ፡፡

እንግዲህ የአማራ ብሄረተኝነት የእነዚህን ሁሉ ብሄረተኝነቶች ስጋት ውስጥ ጥሏል፡፡ ስጋት ውስጥ ልጣል ብሎ ሳይሆን የፖለቲካ ጥልፍ አሰራሩ አንዱ ሲሳብ ሌላው እንዲጎተት ሆኖ የተሰራ ነባራዊ ሀቅ ስለሆነ፡፡ ስለሆነም የአማራ ብሄረተኝነት አራማጆች የነካኩት ሀረግ ብዙ እባብ የሚመዝ መሆኑን አውቀው ጸንተው መቆም ይገባቸዋል፡፡ ህዝቡም ከዚህ በኋላ ወደኋላ መመለስ በራስ ላይ የባሰ ጥፋት ማወጁን ማወቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም የአማራን ብሄረተኝነት እንደሌለ ቆጥረው የየራሳቸውን እቅድ ያቀዱ ሁሉ አሁን አማራን ያካተተ እቅድ ማቀዳቸው አይቀሬ ስለሚሆን (ስለሆነም)፡፡

የአእምሮየን ባልናገር አማራን እጎዳለሁ!

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.