የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት የ495 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተናገረ፡፡

Source: http://amharic.abbaymedia.com/archives/28432

ከሞቱት መካከል 462ቱ ሲቪል ሲሆኑ ፤ 36ቱ የፀጥታ አስከባሪዎች መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ኮሚሽኑ ያደረገውን የምርመራ ውጤት ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርብ ነው፡፡

በክልሉ የተፈጠረውን አለመረጋጋትና ተቃውሞውን የመሩ በመንግሥትም በአሸባሪነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች በህግ መጠየቅ አለባቸው ብሏል ኮሚሽኑ፡፡
ለ56 ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውና በእሬቻ በአል ላይ ለደረሰው አደጋም በፌዴራልና ክልል ያሉ ባለሥልጣናት በደረጃ በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው በኮሚሽኑ ተነግሯል፡፡

ዶክተር አዲሱ እንዳሉት በእሬቻ በአል ላይ ተቃውሞ ለማካሄድ የተዘጋጁ ወጣቶች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ወደ ቢሾፍቱ ከተማ በአይሱዙ ተጭነው መግባታቸው እየታወቀ በዓሉ እንዲካሄድ መደረጉ ኃላፊነት የጐደለው ነው ብለዋል፡፡

በዓሉን በመከልከል አደጋውን ማስቀረት ይችሉ የነበሩ የክልል ባለሥልጣናት ይህንን ባለማድረጋቸው በህግ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡

በበዓሉ ላይ የነበሩ ሰዎች በመረጋገጥና በሆራ ሀይቅ አካባቢ ባለው ገደል በመግባት መሞታቸውን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል፡፡
ገደሉንም ቀድሞ መድፈን የነበረበት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ይህንን ባለማድረጉ የሥራ ኃላፊዎቹ በህግ እንዲጠየቁ ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ በመንግሥት የተወሰዱ እርምጃዎች ሕጋዊና ተመጣጣኝ ናቸው ያላቸውንና የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር እየተቻለ ያልተመጣጠነ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ያላቸውንም ከነምክንያቶቻቸው ለምክር ቤቱ በዝርዝር አቅርቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ብቻ በተፈጠረው አለመረጋጋት 495 ሰዎች መሞታቸውን፣ 464 ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና በመቶ ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት መውደሙንም ኮሚሽኑ ተናግሯል፡፡

በአማራና ደቡብ ክልል ያደረገውን የምርመራ ውጤትም ዛሬ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እያቀረበ ነው፡፡

 

Share this post