የኢትዮጵያ ፕሬስ ነጻነት አውሮፓ ካለው ነጻነት ልዩነት የለውም ሲሉ ዶ/ር አርከበ አስታወቁ

Source: http://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%88%B5-%E1%8A%90%E1%8C%BB%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%8B%8D%E1%88%AE%E1%8D%93-%E1%8A%AB%E1%88%88%E1%8B%8D-%E1%8A%90/

ኢሳት (ግንቦት 11 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፕሬስ ነጻነት አውሮፓ ካለው የፕሬስ ነጻነት ምንም ልዩነት እንደሌለው አንድ ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣን ገለጹ።

“ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጸፉት ጋዜጦች አውሮፓ ውስጥ ከሚጻፉት ምንም ልዩነት የላቸውም በማለት ለጀርመን ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም የገለጹት የህወሃት ነባር ታጋይና የጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማሪያም አማካሪ የሆኑት አርከበ ዕቁባይ ናቸው።

አገሪቱ በዲሞክራሲ ጎዳና መጓዝ የጀመረችው ከ1987 አም ህገ መንግስት ከጸደቀ ወዲህ ነው በማለት የገለጹት ዶ/ር አርከበ እቁባይ፣ “ዴሞክራሲ የተራዘመ ጊዜ ስለሚወስድ በመጀመሪያ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን” በማለት አክለው ገልጸዋል።

“የመናገር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና አስተያየትን በነጻነት ለመስጠት ለምን ብዙ ጊዜ ይፈጃል?” ተብለው የተጠየቁት አቶ አርከበ፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ጋዜጦች ላይ የማይጻፍ ነገር የለም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ይህንን ይበሉ እንጂ በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት በመደበኛነት የሚታተሙ የአማርኛ ጋዜጦች ከአምስት የማይበልጡ ሲሆን፣ እነዚህም ጋዜጦች ጠንካራ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አያስተናግዱም። የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋዜጦችም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት የመጀመሪያዎቹ አመታት ብቻ ከ350 በላይ የግል ጋዜጦች ነበሩ።

Share this post

Post Comment