የኤርትራው ፕሬዝዳንት ጅቡቲን ሊጎበኙ ነው

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%8A%A4%E1%88%AD%E1%89%B5%E1%88%AB%E1%8B%8D-%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%8B%9D%E1%8B%B3%E1%8A%95%E1%89%B5-%E1%8C%85%E1%89%A1%E1%89%B2%E1%8A%95-%E1%88%8A%E1%8C%8E%E1%89%A0%E1%8A%99-%E1%8A%90/

(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 27/2011) የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጅቡቲን ሊጎበኙ ነው።

የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትላንት እንዳታስታወቁት የኤርትራው መሪ በቅርቡ ጅቡቲን የሚጎበኙ ሲሆን የጅቡቲውም ፕሬዝዳንት በተመሳሳይ ኤርትራን እንዲጎበኙ መርሃ ግብር መዘጋጀቱም ተመልክቷል።

ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ከድንበር ጋር በተያያዘ ሲወዛገቡ የነበሩትና መጠነኛ ወታደራዊ ግጭትም ያደረጉት ኤርትራና ጅቡቲ ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ ግኑኝነታቸው እየተሻሻለ መቷል።

የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሙሐመድ አሊ የሱፍ ለቱርክ የዜና አገልግሎት አናዱሉ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የወሰዱት ርምጃ በአካባቢው መረጋጋትንና ሰላምን እያመጣ ነው ብለዋል።

ለጅቡቲና ለኤርትራ ግንኙነት መሻሻል የዶክተር አብይ አህመድ ሚና የጎላ መሆኑንም ለአናዲሉ ምስክርነት ሰጥተዋል።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂና የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ጊሌህ በመስከረም ወር መገናኘታቸውን ርሳቸውም ከኤርትራው አቻቸው ጋር መወያየታቸውን የጠቀሱት የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ሚስተር ሙሃመድ አሊ የሱፍ በውስጣዊና በውጫዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ባለ ራዕይ መሪዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

“ተስፈኞች ሆነናል ምክንያቱም ሁኔታዎች ለመሻሻላቸው ምክንያቶችን አይተናልና ወደፊት ደግሞ ይበልጥ እናያለን” ያሉት የጅቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሙሃመድ አሊ የሱፍ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጅቡቲን የሚጎበኙበትን ቀን ግን በግልጽ አላስቀመጡም።

ጅቡቲና ኤርትራን ወደ ውዝግብና ግጭት የወሰደው በቀይ ባህር ዳርቻ የሚገኘው ራስ ዱሜራ የተባለው ቦታ ሲሆን ከ10 ዓመት በፊት በሰኔ ወር 2001 ለሶስት ቀናት መዋጋታቸው ይታወሳል።

The post የኤርትራው ፕሬዝዳንት ጅቡቲን ሊጎበኙ ነው appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.