የኤርትራ ማዕቀብ መነሳት ለቀጠናው ምጣኔ ሀብታዊ ውህደት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Source: https://fanabc.com/2018/11/%E1%8B%A8%E1%8A%A4%E1%88%AD%E1%89%B5%E1%88%AB-%E1%88%9B%E1%8B%95%E1%89%80%E1%89%A5-%E1%88%98%E1%8A%90%E1%88%B3%E1%89%B5-%E1%88%88%E1%89%80%E1%8C%A0%E1%8A%93%E1%8B%8D-%E1%88%9D%E1%8C%A3%E1%8A%94/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኤርትራ ላይ ለዘጠኝ ዓመታት ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ መነሳት በምስራቅ አፍሪካ አንድ የጋራ የምጣኔ ሀብት ውህደት ለመፍጠር የተጀመረውን እንቅስቃሴ ይበልጥ እንደሚያጠናክረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ዲፕሎማሲያዊ ድሉ የኤርትራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ድልም ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል።

በኤርትራ ላይ በመንግስታቱ ድርጅት የተጣለው እና ለዘጠኝ ዓመታት የዘለቀው ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ የበኩሏን ሚና ስትወጣ መቆየቷንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የማዕቀቡ መነሳት በቀጠናው ያለውን አዲስ የሰላም ትብብር መንፈስ ያጠናክረዋል ያሉት አቶ መለስ ዓለም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ ሀገራት መካከል ለረጅም ጊዜ ያህል አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ ማየት እና የማጠልሸት እንቅስቃሴ ይደረግ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይህ ሁኔታ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ሳይጠናከር እንዲቆይ ካደረጉት ችግሮች አንዱ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ግጭት በነገሰበት አካባቢ የልማት እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የማይታሰብ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ በቀጠናው ስለጦርነት ከማሰብ መውጣት ትልቅ ትርጉም ያለው ሲሆን፥ በገንዘብ የማይተመን ዋጋ እንዳለውም ነው የተናገሩት።

ከአፍሪካ ህብረት የ2063 እቅድ ውስጥም አንደኛው የግንባታ ጡብ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ከጸጥታ እና ሰብዓዊ ጉዳዮች ወጥቶ የልማት ጉዳዮች ላይ ማተኮር መሆኑንም አስረድተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ሲታሰቡ የቀጠናውን ሀገራት ለማስተሳሰር ታሳቢ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት ቃል አቀባዩ፥ የባቡር መስመር ዝርጋታ የጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በስላባት ማናዬ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.