የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ዘላቂ ሀገራዊ ትስስርን ለማሳደግ መስራት አለባቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

Source: https://fanabc.com/2019/02/%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%88%AD%E1%89%80-%E1%88%B0%E1%88%8B%E1%88%9D-%E1%8A%AE%E1%88%9A%E1%88%BD%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%89%A3%E1%88%8B%E1%89%B5-%E1%8B%98%E1%88%8B%E1%89%82-%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AB/

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ዘላቂ ሀገራዊ ትስስርን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታውቅዋል።

የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት የመተዋወቂያ መድረክ በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።

የመተዋወቂያ መድረኩ ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የኮሚሽኑ አባላት ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት ምልእክትም፥ ይህ በመቶ ዓመት አንዴ የሚገኝ ሀገርን ከማቀራረብ እና ሰላምን ከማምጣት አንጻር ትልቅ እድል ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ አባላት ከዘር፣ ከሀይማኖት እና ከመድሎ በፀዳ መልኩ ስራቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

መንግስት በእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ስራ ጣልቃ እንደማይገባ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ቢሮ ከማዘጋጀት ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ግን ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ አባላት ሀገራዊ ትስስርን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው ተናግረው ለሌላ ሀገራት ተምሳሌትሊሆን የሚችል ስርዓት እንዲፈጥሩ አበረታተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፥ እርቅ ንፁህ አእምሮን ይፈልጋል፤ ለዚህም በሀቅ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

መንግስት ለኮሚሽኑ ስራ ስኬት አስፈላጉውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

በትውውቅ መድረኩ ላይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቅራቢነት የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ እና ምክትል ተሹመዋል።

በዚህም መሰረት በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጵጵስ ብፁእ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስን የብሄራዊ እርቅና ሰላም ኮሚሽን ሰበሳቢ ሆነው ተሹመዋል።

የህግ ባለሙያዋን የትነበርሽ ንጉሴን ደግሞ የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን ተሹማለች።

የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምከንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፤ እውነት እና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅን ለማውረድ እንዲያግዝ ነው የተቋቋመው።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ለብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን 41 አባላትን መሾሙም ይታወሳል።

የኮሚሽኑ አባላትም ከሀይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲከኞች፣ ከምሁራን፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከታዋቂ ሰዎች እና ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተውጣጡ ናቸው።

 

በአፈወርቅ አለሙ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.