የእነ ነጋ የኔነው የክስ መቃወሚያ

Source: http://welkait.com/?p=11206
Print Friendly, PDF & Email

~ የአንዳንዳችን ላይ የቀረበው ማስረጃ እኛ ያልሰጠነው በመርማሪ ፖሊስ ተዘጋጅቶ በማሠቃያ ክፍል ውስጥ ሆነን ሣናውቀው እና ሣይነበብልን በግዴታ ውስጥ ሆነን የፈረምነው በመሆኑ ከመፈረማችን በፊትም የሕግ ምክር አገልግሎት እንዳናገኝ ተገድበን እና ተገድደን የፈርምነበት እንጅ ወደን እና ፈቀደን ያልሰጠነው ቃል ስለሆነ አሁን ከክሱ ጋር ደርሶን ስንመለከተው ደግሞ አንዱም ቃል እኛ ያልተናገርነው መሆኑን ስላረጋገጥን በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 19(5) መሠረት በማስረጃነት እንደማያገልግል የተረጋገጠ በመሆኑ በግዳጅ የተገኘ ማስረጃ ከክሱ ጋር ሊያያዝ አይገባም ተብሎ ብይን እንዲሰጥልን።

~ የግጭቱ መነሻ ምክንያት ነው የተባለው የወልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ አለመመለስ፣ የአማራ ሕዝብ እየተጨፈጨፈ በመሆኑ ምክንያት ተደራጅተዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ያረጋገጠው እውነታ ነው። ይህን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የገለፀውን እውነታም የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን የሞላው የአማራ ሕዝብ መሆኑ ያረጋግጠዋል።

~ ፍርድ ቤቶች በነፃነት የተከራካሪ ወገኖችን ማስርጃ የመመዘን ሥልጣን እያላቸው ሌላ የፖለቲካ ተቋም ማስረጃዎችህን እኔ አዘጋጅቸልሀለሁ እንዳለ ተቀበል የሚለውን ለሕገመንግሥቱ ተቃራኒ የሆነ ድንጋጌ መሠረት አደርጎ በማስረጃነት የቀረበው ሪፖርት የዳኝነት ነፃነትን በግልፅ የሚቃረን እና የተከራካሪ ወገን መብትንም ፈፅሞ የሚጥስ ነው!

(ፎቶው የ1ኛ ተከሳሽ ነጋ የኔነው ተክሌ)

ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት
አዲስ አበባ

ከሣሽ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ተከሣሾች

1ኛ አቶ ነጋ የኔው ተክሌ ——

2ኛ አቶ ደሣለኝ ማንደፍሮ መንግሥቴ

3ኛ አቶ ሹሜ ዋኘው ሞላ

4ኛ አቶ ፍትሕአለው ወርቅነህ ስሜነህ

5ኛ አቶ ጌጤ አሥራት ስመኝ

6ኛ አቶ ምስጌ ሙጨየ ተሾመ

7ኛ አቶ ጥሩየ አለነ ዘውዱ

የሁሉም ተከሣሾች ጠበቃ አለልኝ ምሕረቱ

በወንጀለኛ መቅጫ ሥ/ሥ ሕግ ቁጥር 130(1) መሠረት የቀረበ የክስ መቃወሚያ
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ/ም በተፃፈ ያቀረበውን ክስ ተመልክተን የሚከተለውን የክስ መቃወሚያ አቅርበናል።

1ኛ መቃወሚያ ይህ ፍርድ ቤት ክሱን ለማየት ክልላዊ ሥልጣን የሌለው ስለመሆኑ፡-

የፀረሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 በአንቀጽ 36(2) ላይ ስለፀረሽብረተኝነት የክስ አመራር የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚዎች እንደሚሆኑ በግልፅ ተደንግጓል። ተከሣሾች የሽብርተኝነት ወንጀል ፈፅማችኋል የተባልነውም ሆነ የወንጀሉ ውጤት ተገኘ የተባለው አማራ ክልል ውስጥ ነው። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 99 እና 100 እንዲሁም የወንጀል ሕግ አንጽ 25(2) ላይ በግልፅ እንደተደነገገው በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ክስ ሊታይ የሚገባው ወንጀሉን ፈፀመ በተባለበት ወይም የወንጀሉ ውጤት በተገኘበት ሥፍራ በሚያስችለው ፍርድ ቤት መሆኑን በአስገዳጅነት ደንግጓል። የዚህ ድንጋጌ ዓላማም በተከሣሾች ላይ በሕግ ከሚፈረድባቸው ውጭ ሌላ ማንኛውም ተጨማሪ እንግልት እንዳይደርስ የወንጀል ሕግ መርህ በመሆኑ እና ድርጊቱ በተፈፀመበት አካባቢ የመከላከያ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ ታስቦ የተደነገገ በመሆኑ ሊጣስ የሚገባው ድንጋጌ አይደለም። በዚህም መሠረት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከክልሉ የሥረነገር ሥልጣኑ በተጨማሪ በፌደራል ጉዳዮች ላይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጣምራ ሥልጣን Concurrent Jurisdiction) እንዳለው በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 80(2) ላይ በግልፅ ተመልክቷል። ይህ ጣምራ ሥልጣንም በሕገመንግሥት የተሰጠ ተጨማሪ ሥልጣን በመሆኑ በማንኛውም መልኩ ሊጣስ ወይም ሊቀነስ የማይገባው ሙሉ ሥልጣን በመሆኑ በአማራ ክልል በሽብር ወንጀል የተከሰሱ የአብዛኛውን ሕዝቦች ክስ በባህርዳር እና ጎንደር ባለው ችሎት እያየ ይገኛል። ስለዚህ በአሁኑ ሰዓት በዚህ ተመሣሣይ ክስ የአማራ ብሔራዊ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባህረዳር እና ጎንደር ላይ ባሉት ችሎቶች የአብዛኛዎቹን ተከሣሽ ሕዝቦች ጉዳይ እየዳኘ ባለበት ሁኔታ ጥቂት ተጠርጣሪዎች ተመርጠን ጉዳያችን አዲስ አበባ ላይ እንዲታይ የተደረገበት በቂ ምክንያት ባለመኖሩ ወንጀሉ ተፈፀመ በተባለበት ክልል ባለው ባለሥልጣን ፍርድ ቤት ሊታይ ይገባል በማለት መዝገቡን ዘግቶ እንዲያሰናብተን። ይህ ታልፎ በዚህ ፍርድ ቤት የሚታይበት ሕጋዊ ምክንያት ካለ ሌሎች የክስ መቃወሚያዎችን አቅርበናል።

2ኛ መቃወሚያ፡- የክስ ሕጋዊነት አስቀድሞ መመርመር ያለበት ስለመሆኑ:_

የክስ አቀራረብ ጉድለቶችን ሙሉ በሙሉ መቃወም እንደሚቻል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ 130(1)ን መሠረት በማድረግ በሰበር መዝገብ ቁጥር 73514 አስገዳጅ ትርጉም ሰጥቷል። በዚህም መሠረት አንድን የወንጀል ክስ ወደፍሬ ነገሩ ገብቶ ማከራከር የሚቻለው በመጀመሪያ ክሱ በሕግ አግባብ ተሟልቶ መቅረቡ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። በተለይም የክስ እና የማስረጃ ሕጋዊነት በተከራካሪ ወገን የሚስተባበል ሣይሆን ፍርድ ቤቶች በቅድሚያ ሊመለከቱት የሚገባ የሕግ ጉዳይ ስለሆነ እነዚህ መሠረታዊ ነጥቦች በፍርድ ቤቱ ተመዝነው ተገቢነታቸው ሣይረጋገጥ ወደክርክር ሊያስኬድ የሚችል የሕግ መሠረት የለም። በዚህም መሠረት በክሱ እና በማስረጃዎቹ በሕጋዊነታቸው ላይ ከዚህ የሚከተሉትን መቃወሚዎች አቅርበናል።

በተከሣሾች ላይ በሰፊው የተዘረዘሩት ፍሬ ነገሮች ተጠቃለው ሲታዩ ሁለት ነጥቦች ናቸው። 1ኛው በ1ኛ ክስ ላይ የዋልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ሊመለስ አልቻለም፣ የአማራ ሕዝብ እየተጨፈጨፈ ነው በሚል ሰበብ የሽብር ቡድን አባል በመሆን በጎንደር ከተማ ቦምብ በማፈንዳት ሽብር ፈጥረዋል፣ መንግሥትን በኃይል ለማስወገድ አስበዋል የሚል ሲሆን 2ኛው ደግሞ በ2ኛ ክስ ላይ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት መንግሥትን ለማስወገድ አሲረዋል የሚሉትን እናገኛለን። ቦምብ ለማፈንዳት ማቀዳችንም ሆነ ማፈንዳታችን በማስረጃ የሚጣራ ቢሆንም ከክሱ ዝርዝር መረዳት የሚቻለው ወይም ክሱ በግልፅ የሚያሣየው የግጭቱ መነሻ ምክንያት ነው የተባለው የዋልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ አለመመለስ፣ የአማራ ሕዝብ እየተጨፈጨፈ በመሆኑ ምክንያት ተደራጅተዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ያረጋገጠው እውነታ ነው። ይህን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የገለፀውን እውነታም የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን የሞላው የአማራ ሕዝብ መሆኑ ያረጋግጠዋል። መነሻ ምክንያቱ ከመብት ጥያቄ ጋር መያያዙን ዐቃቤ ሕግ ካረጋገጠ በዚህ ሁኔታ ድንገተኛ ግጭት መፈጠሩን እንጅ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የአይዲኦሎጂ ዓላማ ይዘን የሽብር ወንጀል መፈፀማችንን ወይም ለመፈፀም መደራጀታችንን ክሱ አያረጋግጥም፣ ተጥሷል ተብሎ የተጠቀሰው የሽብርተኝነት ሕግ ድንጋጌ እና የግጭቱ መነሻ ምክንያት ስለማይመሣሠል ለድርጊቱ መፈጠር ምክንያት የሆነው ነገር ከመብት ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን ክሱ ራሱ እየገለፀ በሕገመንግሥት የተሰጠን መብት ለማስከበር በሚነሣ ጥያቄ የሚፈጠር ድንገተኛ ግጭት ዓላማ ተጥዞበት ከሚፈፀም የአሸባሪነት ወንጀል ጋር ግንኙነት የለውም። በዚህም መሠረት የተጠቀሰው ሕግ እና የወንጀል ድርጊት የተባለው ምክንያት ግጭት ስላለበት የቀረበው ክስ ለማስተባበልም ሆነ ለመከላከል ያማያስችል እና ግልፅነት የጎደለው በመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 112 የተመለከተውን የክስ አቀራረብ ሥርዓት ያልተከተለ ስለሆነ ሊሠረዝ ይገባዋል።

ከላይ የተዘረዘረውን ክስ ያስረዳሉ በተባሉ የሰነድ ማሥረጃዎች ሕጋዊነት ላይ የቀረበ መቃወሚያ፡- የማስረጃ ተአማኒነት (ብቃት) በማስረጃ ምዘና ጊዜ የሚታይ ቢሆንም የማስረጃ ሕጋዊነት ግን ክሱ ተከፍቶ የፍሬ ነገር ክርክር ከመታየቱ በፊት በሕግ አግባብ ያልተገኘ ማስረጃ የክሱ አካል ሊሆን ይችላል ወይስ አይችልም? የሚለው መሠረታዊ ነጥብ ሊታይ ይገባዋል። ከክርክር በኋላ ሊመዘን የሚችለው የማስረጃው እውነተኛነት ብቻ ነው። የማስረጃው ሕጋዊነት የክስ አቀራረብ አንዱ አካል በመሆኑ በመጀመሪያ ደረጃ ማስረጃው የክሱ አካል ሊሆን የሚችለው በሕግ መሠረት የተገኘ ሲሆን ብቻ ስለሆነ በተከሣሾች ላይ የቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ከዚህ በሚከተሉት ምክንያቶች ከክሱ ሊነጠሉ ይገባል።

ከስልክ ንግግር የተገኙ ናቸው ተብሎ በሪፖርት መልክ የቀረቡትን ማስረጃዎች በተመለከተ፡- በሕገመንገሥቱ አንቀጽ 26(2) ላይ በማንኛውም ሁኔታ የግል ግንኙነቶችን ማንም ሰው ወይም ባለሥልጣን ጣልቃ ሊገባበት እንደማይገባ ተደንግጓል። የመንግሥት ባለሥልጣናትም እነዚህን ነፃነቶች ለብሔራዊ ደኅንነት ሲባል በሚወጣ ሕግ መሠረት አገልግሎታቸውን ከማገድ በቀር የማንኛውንም ሰው የግል ምስጢር እንዳይመለከቱ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 26(3) ተከልክለዋል። በፀረሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 14(1) ‹‹የሽብርተኝነት ድርጊትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ (ሀ) በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠረውን ሰው የስልክ፣ የፋክስ፣ … ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል … ይችላል›› በማለት ተደንግጎ ይገኛል። ይህ ድንጋጌ በራሱ ሕገመንግሥቱን የሚቃረን በመሆኑ ተፈፃሚ የማይሆን ከመሆኑ በተጨማሪ አሁን በእኛ ላይ ማስረጃ ሆኖ የቀረበው የስልክ ንግግር የተባለ ሪፖርት ግን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሕግ ውጭ የተገኘ ማስረጃ በመሆኑ የክሱ አካል ሊሆን ስለማይችል ከክሱ እንዲነጠል እንዲታዘዝልን ዳኝነት እንጠይቃለን። በተለይም ፍርድ ቤቶች በነፃነት የተከራካሪ ወገኖችን ማስርጃ የመመዘን ሥልጣን እያላቸው ሌላ የፖለቲካ ተቋም ማስረጃዎችህን እኔ አዘጋጅቸልሀለሁ እንዳለ ተቀበል የሚለውን ለሕገመንግሥቱ ተቃራኒ የሆነ ድንጋጌ መሠረት አደርጎ በማስረጃነት የቀረበው ሪፖርት የዳኝነት ነፃነትን በግልፅ የሚቃረን እና የተከራካሪ ወገን መብትንም ፈፅሞ የሚጥስ በመሆኑ በሕገመንግሥት የተሰጡ መብቶችን የሚጥስ ሕግ ባጋጠመ ጊዜ ደግሞ ፍርድ ቤቶች በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 9(2) መሠረት ተፈፃሚ እንዳይሆን የማድረግ ሕገመንግሥታዊ ሥልጣን ስላላቸው በሕግ አግባብ ያልተገኘው ከስልክ ምልልስ ተገኘ የተባለው ሪፖርት በሕጋዊ መንገድ ያልተገኘ በመሆኑ ብቻ ከክሱ እንዲነጠል፤ ሪፖርቱም የክሱ አካል አይሆንም ተብሎ ውድቅ እንዲደረግልን።

የክሱ አካል ሆኖ እንዲቀጥል የሚደረግበት ሕጋዊ ምክንያት ካለ ደግሞ ሪፖርቱ ከስልክ ምልልስ ላይ የተገኘ ነው ተብሎ የማስረጃ ምንጩ ስለተጠቀሰ የማስረጃው ምንጭ ከታወቀ ማስረጃው እንዲደበቅ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግም ስለማይፈቅድ አብዛኛዎቹ ስልክ ቁጥሮች የእኛ ባለመሆናቸው በማስረጃ ሂደት የሚጣሩ ሆኖ የስልክ ግንኙነት በአንድ ስልክ ብቻ የሚደረግ ስላልሆነ ከእኛ ጋር ተገናኙ የተባሉት ሰዎች ስልክ ቁጥር አለመጠቀሱ ሪፖርቱ ከእኛ የስልክ ምልልስ ያልተገኘ መሆኑን ያረጋግጣል። የክሱ አብዛኛው ክፍል ከስልክ ንግግር በተገኘ ማስረጃ መሠረት ነው ተብሎ ከቀረበ ደግሞ ክሱን ሊያስረዳ የሚችለው የአንድ ተቋም ሪፖርት ሣይሆን ማስረጃ መሆን የሚችለው ቀጥተኛ የሆነው የስልክ ንግግር ወይም ወደፅሑፍ የተቀየረው ድምፅ ራሱ ስለሆነ ክሱን ማስተባበልም ሆነ መከላከል የምንችለው የድምፅ ቅጁ ሲቀርብ ብቻ ስለሆነ የድምፅ ቅጁ እንዲሰጠን እንዲወሠንልን።

በማስረጃነት የተጠቀሰ ነገር ሁሉ ፍርድ ቤት መቅረብ እና ለተከራካሪ ወገንም መድረስ ያለበት ስለመሆኑ፡- በእኩልነት ያልተዘጋጀ ክስና ማስረጃ በሕግ ፊት እኩል ሆኖ መዳኘት (Equality Before the Law) የሚለውን ሕገመንግሥታዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ማስረጃዎቹን በቁጥጥር ሥር ካሉ ተከሣሾች ደብቆ ማስረዳት ሚዛናዊ ያልሆነ ዳኝነት ለማሰጠት ሲባል በሕገመንግሥት የተሰጡ መብቶቻችንን የሚያጣብብ በመሆኑ በዚህ ረገድ የቀረበው የክስ አቀራረብ የተከሣሾችን የመከራከር መብት ሙሉ በሙሉ የሚገድብ ነው። በዚህም መሠረት የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 14 እና 32፣ አዋጅ ቁጥር 669/2003 ሙሉ በሙሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) ላይ የተደነገገውን ተከሣሽ የቀረበበትን ማንኛውንም ማስረጃ የመመልከት መብት በግልፅ ስለሚቃረን ‹‹ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም የባለሥልጣን ውሣኔ ከዚህ ሕገመንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም›› ተብሎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) ላይ ከመደንገጉ በተጨማሪ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ ቁጥር 2 ላይ ሕገመንግሥቱን የማስከበር ሀላፊነቱም የፍርድ ቤቶች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የየአንዳንዱ ዜጋ ግዴታ በመሆኑ ዐቃቤ ሕግም ሕገመንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ሀላፊነት ስላለበት ለሕገመንግሥቱ ተቃራኒ የሆነውን ማስረጃን ለተከራካሪ ወገን አለማሣወቅ ሕገመንግሥቱን የሚቃረን ድንጋጌ እንዲፈፀም በማድረግ ክሱን ባልተሟላ ሁኔታ ማቅረቡን ከክሱ ላይ ለመገንዘብ ችለናል። በዚህ ክስ የማስረጃ ዝርዝሩ በፊደላት ተራ የተመደበ ሲሆን በ‹‹ሐ›› እና በ‹‹መ›› ሥር የተዘረዘሩትን ማስረጃዎች ስናይ በፊደል ተራ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› የተዘረዘረ ማስረጃ መኖሩን ስለሚያመላክት እና ይህ የማስረጃ ዝርዝርም ለተከሣሾች ያልደረሰን ስለሆነ ግልፅነት በሌለው አቀረራብ ከተከሣሾች የተደበቀ ማስረጃ ካላ ማለትም ዐቃቤ ሕግ ማስረጃውን ለተከሣሾች አይሰጥም የሚልበት ምክንያት ካለም ምንም እንኳን ለሕገመንግሥቱ ተቃራኒ ቢሆንም በፀረሽብርተኝነት አዋጁ መሠረት ፍርድ ቤቱን ሣያስፈቅድ ማስረጃውን ከተከሣሾች መደበቅ ስለማይቻል በፊደል ተራ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ሥር የተዘረዘረ ማስረጃ ካለ ተከሣሾችን በሕግ በግልፅ በመከራከር ሣይሆን በተደበቀ ማስረጃ ጥፋተኛ ለማሰኘት እንደተሞከረ የሚያስመስል የክስ አቀራረብ ነው። በዚህም መሠረት ከፊደል ተራ ‹‹ሐ›› በፊት የተዘረዘረ ማስረጃ ካለ ማስረጃው የሰው ይሁን የሰነድ ማስረጃ ሣናውቀው ማስረጃ በሚታይበት ጊዜ በማስረጃነት ሊቀርብ ስለማይችል የተከበረው ፍርድ ቤት ማስረጃው (የምስክሮች ዝርዝር) እንዲሰጠን እንዲታዘዝልን። የማይሰጠን ከሆነ ግን ለተከሣሾች ከደረሰው የማስረጃ ዝርዝር ውጭ የቀረበው ማንኛውም የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ በማስረጃነት አይያዝም ወይም የክሱ አካል አይደለም ተብሎ ብይን እንዲሰጥልን።

በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነሥርዓት ቁጥር 27 መሠረት ተገኙ የተባሉትን ማስረጃዎች በተመለከተ፡- በተጠቀሰው ድንጋጌ መሠረት ተከሣሹ የሚሰጠው ቃል በቅድሚያ የሕግ አማካሪውን አግኝቶ፣ መብቶቹ ተነግረውት፣ ሣይገደድ እና በነፃ ፈቃዱ የሰጠው ከሆነ እና በሌላ ማስረጃ ከተደገፈ ብቻ እንደማስረጃነት ሊቆጠር ይችላል። ይሁን እንጅ በየአንዳንዳችን ላይ የቀረበው ይህ ማስረጃ እኛ ያልሰጠነው በመርማሪ ፖሊስ ተዘጋጅቶ በማሠቃያ ክፍል ውስጥ ሆነን ሣናውቀው እና ሣይነበብልን በግዴታ ውስጥ ሆነን የፈረምነው በመሆኑ ከመፈረማችን በፊትም የሕግ ምክር አገልግሎት እንዳናገኝ ተገድበን እና ተገድደን የፈርምነበት እንጅ ወደን እና ፈቀደን ያልሰጠነው ቃል ስለሆነ አሁን ከክሱ ጋር ደርሶን ስንመለከተው ደግሞ አንዱም ቃል እኛ ያልተናገርነው መሆኑን ስላረጋገጥን በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 19(5) መሠረት በማስረጃነት እንደማያገልግል የተረጋገጠ በመሆኑ በግዳጅ የተገኘ ማስረጃ ከክሱ ጋር ሊያያዝ አይገባም ተብሎ ብይን እንዲሰጥልን።

የክስ አቀራረቡ ከፍርድ በፊት ንፁህ ሆኖ የመገመት መብታችንን የሚጥስ እና ስህተት ያለበት ስለመሆኑ፡- በመጀመሪያ ደረጃ አሸባሪነት የኢትዮጵያውያን ባህሬ እንዳለሆነ ሁሉም የሚያውቀው ሲሆን የተከበረው ፍርድ ቤትም ኢትዮጵያውን መከባበር እና መረዳዳት እንጅ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሽብርተኝነት ተግባር እንደማይፈፅሙ በማንኛውም ደረጃ ቢሆን ለሃይማኖታዊ እና ለባህላዊ መልካም ሥነምግባር ቅድሚያ የሚሰጡ ጨዋ ሕዝቦች መሆናቸውን ስለሚረዳ ኢትዮጵያውያን የአሸባሪነት ተግባር ይፈፅማሉ ብሎ እንደማይገምት እንረዳለን። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ‹‹አሸባሪነት›› (ሽብርተኛ) ለሚለው ቃል ትርጉም አልሰጠም። አዋጁ ትርጉም ካልሰጠ ደግሞ ‹‹አሸባሪነት›› የሚለው ቃል መተርጎም የሚገባው ዓለምአቀፍ ይዘት ያላቸውን የመዝገበ ቃላት ትርጉም እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን የአሸባሪነት ትርጉም መሠረት አድርጎ ነው። ከመብት ጥያቄ ጋር የሚያያዝ ግጭት ደግሞ የአሸባሪነት ባህሬ ስለሌለው አዋጁ ራሱ ትርጉም ባይሰጥም ዓለምአቀፋዊ ትርጉም እንዲከተል ግርድ ቤቶች ሕግን የመተርጎም ያልተገደበ ሥልጣን አላቸው። በተለይም ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ቃልኪዳን ሰነዶችን ስምምነቶችን ተቀብላ ያፀደቀች ሲሆን በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 13(2) ላይም ሕገመንግሥቱ ሣይቀር ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ጋር ተጣጥሞ መተርጎም እንደሚገባው ለዓለም አቀፍ ሕጎቹ ከፍተኛ ዋጋ ሰጥታለች። በዚህም መሠረት በአሁን ተከሣሾች ላይ የቀረበው ክስ ሰፊ እና የተደጋገመ ዝርዝር ቢኖረውም የግጭት ምክንያት የሆነው ዋናው ነጥብ በክሱ በበርካታ ገፆች ላይ ‹‹… የዋልቃይት ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ምላሽ ስለማይሰጥ፣ መንግሥት የአማራን ሕዝብ እየጨፈጨፈ ስለሆነ…›› በሚል መነሻ የሽብር ወንጀል ለመፈፅም ተደራጅተዋል የሚል ነው። ነገር ግን አንድ የወንጀል ድርጊት ተፈፀመ ተብሎ ክስ ሊያስቀርብ የሚችለው ተፈፀመ በተባለው የወንጀል ድርጊት የሀሣብ ክፍል የድርጊት ክፍል እና የወንጀል ውጤት በአንድነት ተጣምረው ሲገኙ ብቻ ነው። አሁን በቀረበው ክስ ላይ በዝርዝር እንደተመለከትነው ከመብት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ግጭት የነበረ መሆኑን እንጅ የአሸባሪነት ዓላማ ይዘን ለአሸባሪነት ድርጊት መደራጀታችንን አያሣይም። በሌላ በኩልም ከተከሣሾች ጋር ተገናኙ የተባሉት ሰዎች አሸባሪ ይሁኑ አይሁኑ፣ በሕይወት ያሉ ይሁኑ አይሁኑ ወይም ተጠቃሾቹ ሰዎች የአሸባሪ ቡድን አባላት መሆናቸውን የሚሣይ ምንም ዓይነት ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ከአሸባሪ ጋር ተገናኝታችኋል የሚያሰኝ ምክንያት የለም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ከኢትዮጵያ ውጭ መኖራቸው

እየታወቀ በየአህጉሩ ካለ ከቤተሰቡ ጋር የተገናኘውን እና በገንዘብ የተረዳዳውን ሰው ሁሉ ‹‹አሸባሪ›› በማለት ክስ ለማቅረብ በቂ የክስ ምክንያት ሊሆን አይችልም። በሌላ በኩል ማንም ሰው ሣይፈረድበት ንፁህ ሆኖ የመገመት የማይጣስ ሕገመንግሥታዊ መብት እያለው በተለይም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20(3) እና በዓለም አቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 14(2) ላይ ማንም ሰው ሣይፈረድበት የወንጀለኛ ስም እንደማይሰጠው በግልፅ ተደንግጎ እያለ በዚህ ክስ ከፍርድ በፊት አሻባሪ እየተባልን በክሱ ላይ መገለፁ የክስ አቀራረቡ ስህተት ያለበት በመሆኑ ክሱ ሊሠረዝ ይገባዋል።

ስለዚህ ከላይ በዝርዝር የቀረቡት ሁሉም የክስ መቃወሚዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነሥርዓት ቁጥር 130(1)ን እና 146ን እንዲሁም ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለምአቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የቀረበ ስለሆነ እና የክስ አቀራረብ ጉድለቶችን ሙሉ በሙሉ መቃወም እንደሚቻል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 73514 አስገዳጅ ትርጉም የሰጠበት በመሆኑ ክሱ ከወገን ከዘመድ መገናኘትን ሁሉ ወንጀል የሚያስመስል እና ከፍርድ በፊት ተከሣሾችን አሸባሪ ብሎ በመግለፅ መቅረቡ ስነልቡናዊ እና ሞራላዊ ተፅዕኖ ያሣደረብን ስለሆነ እንዲሁም ከሕግ ውጭ በማስገደድ እና ያለፍርድ ቤት ፈቃድ የሰዎችን ግንኙነት በመጥለፍ የተገኙ ማስረጃዎችን መሠረት አድርጎ የቀረበው ክስ ከጅምሩ ለሕግ ተቃራኒ በመሆኑ ግልፅ የሆነ የክስ አቀራረብ ስህተት ስላለበት ክሱ እንዲሠረዝልን፤

ይህ የሚታለፍበት ሕጋዊ ምክንያት ካለ ደግሞ እኛ ግንቦት ሰባት የተባለ ቡድን መኖሩን አናውቅም እንጅ ቢኖር እና እኛ አባል ብንሆን ኖሮ ‹‹ … ለአርበኞች ግንቦት ሰባት አሸባሪ ቡድን …›› በማለት ራሣችንን አሸባሪ ብለን እንደማንጠራ እየታወቀ በክሱ ላይ እና የእምነት ቃል በተባለው ላይ ራሣችንን የአሸባሪ ቡድን እያልን እንደምንጠራ አስመስሎ የተፃፈው ክሱ ተቀነባብሮ መቅረቡን ስለሚያሣይ ክሱ በሕግ አግባብ እንዲቀርብ እና በማስረጃ ዝርዝር ላይ ከፊደል ተራ ‹‹ሐ›› የተጀመረበት ምክንያት ግልፅነት ስለሌለው በፊደል ተራ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› የተዘረዘረ ማስረጃ ካለ እንዲሰጠን የማይሰጠን ከሆነ ክሱ ጎደሎ ስለሆነ በተለይም የፍርድ ቤቱ ሬጅስትራር ጽ/ቤት እኩል እና ተመሣሣይነት የሌለው ክስ ሲቀርብ ክስ አቅራቢውን እንዲያስተካክል መንገር ካላስተካከለም መመለስ እያለበት በአንድ ክስ ላይ የተለያየ ማስረጃ ይዘት ያለው ክስ ተቀብሎ መክፈቱ ስህተት ስለሆነ ከፍርድ ቤቱ የቀረበው ክስና ማስረጃ ምንም ሣይቀነስበት ለተከሣሾች መድረስ ስላለበት ለተከሣሾች ያልደረሰ የማስረጃ ዝርዝር እንዲሰጠን ከዚህ በተጨማሪም ከስልክ ምልልስ ተገኘ የተባለው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጽ/ቤት ወደፅሑፍ የቀየረው የስልክ ንግግር የድምፅ ቅጂ እንዲደርሰን እንዲታዘዝልን በትህትና መቃወሚያችንን አቅርበናል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.