የኦነግ አባላትና አመራር ቡድንን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል – አቶ ቶሌራ አደባ

Source: https://fanabc.com/2018/09/%E1%8B%A8%E1%8A%A6%E1%8A%90%E1%8C%8D-%E1%8A%A0%E1%89%A3%E1%88%8B%E1%89%B5%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%98%E1%88%AB%E1%88%AD-%E1%89%A1%E1%8B%B5%E1%8A%95%E1%8A%95-%E1%88%88%E1%88%98%E1%89%80%E1%89%A0/

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በነገው ዕለት ከኤርትራ ወደ ኢትዮዽያ የሚገባውን የኦሮሞ ነጻነት ግምባር ኦነግ አባላትና አመራር ቡድንን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተነግሯል።

የግምባሩ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ቡድኑ በቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም ደማቅ አቀባበል የሚደረግለት መሆኑንም ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት።

አቶ ቶሌራ እንደገለጹትም የአቀባበል ስነ ስርዓቱ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ መስቀል አደባባይ ይጠናቀቃል።

ስነ ስርዓቱ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ከፌዴራል መንግስት፣ ከኦሮሚያ ክልልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጋራ በመቀናጀትም ስነ ስርዓቱን ሰላማዊና ስኬታማ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ ቶሌራ ጠቁመዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የተጋበዙ ሲሆን፤ የሚታደሙት ወጣቶችና የህብረተሰብ ክፍሎችም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ድጋፋቸውን እንዲያሳዩም አቶ ቶሌራ አሳስበዋል።

 

 

በትእግስት ስለሺ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.