የዋልድባ ሁለት መነኮሳት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ – 88 መነኮሳት ደግሞ ከገዳሙ ተፈናቀሉ

ሁለት መነኮሳት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። ሰማኒያ ስምንት መነኮሳት ደግሞ ከገዳም ተፈናቀሉ። ይህ አስነዋሪ ተግባር የተፈጸመው የትህነግን ቅድመ-ምርጫና ድህረ-ምርጫ ተከትሎ ነው።

የአማራ ተወላጅ ከሆንክ ለነብስህ ካደርክበት ገዳም እንኳን መኖር አትችልም። አማራው ከእየ አቅጣጫው እንደቆዳ ተወጥሯል።

ዛሬ መስከረም 6/2013 ዓ.ም ወደ ማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ-ስብከት ጽ/ቤት ጎራ ብዬ ነበር። ወደ ጽ/ቤቱ የማቅናቴ ዋና ጉዳይ ከዋልድባ አብረንታንት መድሃኔ ዓለም ገዳም በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ አባቶች መኖራቸውን ስለሰማሁ ነው። ገዳሙ ከ1984 ዓ.ም በፊት የጎንደር በጌምድር ክፍለ አገር የግዛት አካል እንደነበር ልብ ይለዋል።ወደ ጉዳየ ስመለስ:- ከገዳሙ ተፈናቅለው የመጡ 8 አባቶችን አገኘሁ። ቀሪዎቹ 80 አባቶች አማራ ክልል ወደ ሚገኙ ገዳሞች ነብስ አውጭኝ ብለው ተጠግተዋል።ቦታ መጥቀስ አያስፈልግም።ሰምንቶቹ አባቶች ተለይተው ወደ ጎንደር የመጡበት ምክንያት:-

ለቤተ-ክህነትም፣ለቤተ-መንግስትም ግፍና ሰቆቃውን ለማስረዳት ነው። ሰቆቃወ-ዋልድባን ዘርዝሮ ለሁለቱም ተቋማት አቤት ለማለት ነው።በመሆኑም ለቤተ-ክህነት እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ዘርዝረው አስረድተዋል።ለመንግስት ሰዎችም አቤት ለማለት ቀነ-ቀጠሮ እንደ ያዙ አባቶች አጫውተውኛል።

***

በምን ምክንያት ተፈናቀላችሁ? ማን አፈናቀላችሁ ስል አባቶችን ጠየኩ።አባቶች ተራ…በተራ ምክንያታቸው ፍጹም ትህትና በተሞላበት አንደበት አስረዱኝ። የአባቶችን መልስ ለአንባቢያን እንዲመች አድርጌ እንደ ሚከተለው አቀርበዋል:-

ትህነግ በአባቶች ላይ ብዙ ግፍ ፈጽሟል። ዛሬ ተፈናቅለው ወደ ጎንደር ከመጡ 8 አባቶች መካከል ሶስቱ በትህነግ ታስረው ከፍተኛ ፍዳና መከራ እንደ ተቀበሉ ነግረውኛል።አባቶች እንዲህ ይላሉ “ከዱላው በላይ፣አፈሙዝ ካፋችን አስገብተው ልበልህ ከሚሉት በላይ፣ እስክብሪቶ በአፍንጫችን ከመክተታቸው በላይ…ዛሬም ድረስ የሚያመን #አማራ በመሆናችን የተሰደብነው ስድብ ነው” ይላሉ። ስድቡ አጥንት ይሰብራል።ልብ ያደማል።አጥንት የሚሰብረውን፣ልብ የሚያደማውን ስድብ ከመነኮሳቱ አንደበት ብሰማም ከዚህ ላይ ለመጻፍ ግን ሞራሌ አይፈቅድልኝም። አልፈዋለሁ። እናተንም አላቃጥልም። እኔ ብቻም ልቃጠል። ልንደድ። ልጭስ።

ትህነግ በአባቶች ግፍና ሰቆቃ መፈጸም ከጀመረ ቆይቷል። በተለይ ሐምሌ 5/በ2008 ዓ.ም ጎንደር ላይ አብዮቱ ሲፈነዳ በዋልድባ አብረንታንት መድሃኔ ዓለም ገዳም ለነብሳቸው ያደሩ አባቶች #እርመት ቤት ሳይቀር በማስወጣት ተገድለዋል። ታስረዋል። ተደብድበዋል። ደብዛቸው ጠፍተው የቀሩ አባቶችም አሉ።

ትህነግ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ተነቅላ መቀሌ ጠቅልላ ከከተመች በኋላ፣በዋልድባ አብረንታንት ገዳም በሚኖሩ አባቶች ላይ የሚፈጸመው በደል እጅግ አይሏል ይላሉ።

ለዚህ ሁሉ ግፍ መፈጸም

1ኛ የገዳሙን አብምኔት አባ ገብረጊዮርጊስ ጨምሮ፣

2ኛ አባ ገብረህይወት መስፍን

3ኛ አባ ሰላማ ገብሩ

4ኛ አባ ወልደ ሰማያት

5ኛ አባ ገብረመስቀል ገብረ ስላሴ (ቀጭኔ)

6ኛ አባ ገብረ መስቀል የሚባሉ የትግራይ ተወላጆች ስመ-መነኩሴዎች ዋና ተባባሪ፣ ብቻ ሳይሆን የግፉ አስፈጻሚ መሆናቸውን ተፈናቃይ አባቶች ይናገራሉ።

በተለይ በተራ ቁጥር 6 የጠቀስኩት መነኩሴ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም በገዳሙ የሚገኙ አጠቃላይ መነኮሳትን መረጃ ሰበሰበ። የመረጃ ስብሰባው ዋና ትኩረቱ ብሄር ላይ ነው።የህወሃቱ ሰው አባ ገብረመስቀል መነኮሳቱን ለመረጃ ስለተፈለገ በሚል ብሄራቸውን ለይቶ መዘገበ።መዝግቦም ለትህነግ ባለስልጣናቶች አስተለለፈ። በለይ ግፉን እንዲያስፈጽሙና ለሞት መልዕክተኞቹ:-

1ኛ ለማይጸምሪ ወረዳ አስተዳደርና ጸጥታ ኃላፊ ለአቶ ሸዊት፣

2ኛ ለማይጋባ ፖሊስ ሃላፊ ለፍሰሃ፣

3ኛ ለማይ ጫአ ፖሊስ ለአታላይ ተልኮው ተሰጠ።

በዚህ መሰረት ከላይ የዘረዘርኳቸው የትህነግ ሰዎች በዋልድባ አብረንታንት መድሃኔ ዓለም ገዳም በምንኩስና ስም፣ወይባ ለብሰው፣ ቆብ ደፍተው፣ዕጸ-መስቀል ጨብጠው ግን ሰይጣናዊውን ተልዕኮ አስፈጻሚ ከሆኑት ጋር በመቀናጀት በአማራ ተወላጅ መነኮሳት ላይ መከራ ጫኑ።

ትህነግ ህገወጥ ምርጫዋን ለማድረግ ቀነቀጠሮ እንደ ቆረጠች ሁለት መነኮሳትን በአሰቃቂ ሁኔታ ገደለች። የግድያዋ ምክንያትም ምርጫ እንዳይመርጥ ያሳድሙብኛል ያለቻቸውን መነኮሳት ነው።መነኮሳቶቹ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ይገናኛሉ፣ፋኖን መንገድ እየመሩ ትግራይን ለማስወረር አቅደዋል የሚል ታርጋም ተለጠፈባቸው።በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም የተገደሉት መነኮሳት ስም:-

1ኛ አባ ገብረ ስላሴ

2ኛ አባ ሀብተወልድ ናቸው።በተለይ የአባ ሀብተወልድ አገዳደል ዘግናኝ መሆኑን ተፈናቃይ መነኮሳቱ ዐይናቸው እንባ እየሞላ፣እያቀረረ፣ፊታቸው ቅጭም እያለ፣ በሀዘን ጦር በተወጋ ልብ ነግረውኛል።አባ ሀብተወልድ የተገደሉት በገጀራ ተቆራርጠው ነው።”ከግድያው በላይ የሚያሳዝ ነው ደግሞ” ይላሉ ተፈናቃይ መነኮሳቱ “የተቆራረጠ አካላቸውን ለቅመን በስርዓተ-ፍታት መቅበር እንዳንችል መከልከላችን ነው።” ይላሉ። የመነኮሳቱ ግድያ ተጨማሪ መልእክት ለው።መነኮሳቱን በፍራት ቆፈን ለማንቀጥቀጥ ነው።ብናስራችሁ፣ብንገድላችሁ፣ብንደበድባችሁ፣ብናፈናቅላችሁ…ማንም አይደርስላችሁም የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው።

***

ከግድያው በኋላ በማይ ጸምሪው የአስተዳደር ጸጥታ ሃላፊ የሚመራው የሞት መልዕክተኛ ቡድን ለመነኮሳቱ የምርጫ ካርድ ይዞ መጣ። በሰኔ ወር በ2012 ዓ.ም በአድዋ ተወላጁ መነኩሴ መሳይ አባ ገብረ መስቀል አማራነታቸው ተለይቶ ለታወቀው መነኮሳት የምርጫ ካርዱን በግድ ለማደል ተሞከረ። ካርድ አንቀበልም ያሉና የሚፈጸምባቸውን ግፍ የሰጉ መነኮሳት እግሬ አውጭኝ ብለው ተሰደዱ።በጊዜው ለማምለጥ ያልቻሉት ካርዱን ተቀበሉ። ግን ምርጫ ሳይደርስ ከሚፈጸምባቸው ግፍና ግድያ ለመሸሽ ቀስ ብለው ተሰደዱ።በአጠቃለይ 88 መነኮሳት ከሞት አምልጠው ወደ አማራ ክልል ገብተዋል።የቀሩት ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ነው።የመንግስት ያለህ እያሉም እየተጣሩ ነው!! ሰሚ ካለ ይስማ!

ዘገባው የዓምደማሪያም እዝራ ነው

Source: Link to the Post

Leave a Reply