የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን እንዲለቁ እስከ ሰኞ እኩለቀን ቀነ ገደብ ተቀመጠ

Source: http://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%8B%9A%E1%88%9D%E1%89%A3%E1%89%A1%E1%8B%8C%E1%8B%8D-%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%8B%9D%E1%8B%B3%E1%8A%95%E1%89%B5-%E1%88%B5%E1%88%8D%E1%8C%A3%E1%8A%93%E1%89%B8%E1%8B%8D%E1%8A%95/

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 11/2010)የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን እንዲለቁ እስከ ሰኞ እኩለቀን ቀነ ገደብ መጣሉ ታወቀ።

ፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ እሁድ ባደረገው ስብሰባ ሙጋቤን ከፓርቲው መሪነት ሲያስወግድ ባለቤታቸውን ደግሞ ማባረሩ ታውቋል።

እስከ ዛሬ ሰኞ ድረስ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በፓርቲያቸው የጊዜ ገደብ የተሰጣቸው የዚምባቡዌው ፕሬዝዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ ትላንት እሁድ በቴሌቪዥን ቀርበው በያዙት ስልጣን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ በሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ወር የሚያደርገውን ጉባኤ እንደሚመሩም ተናግረዋል።

ዛኑ ፒ ኤፍ እሁድ እለት ባደረገው ስብሰባ ሙጋቤን ከፓርቲው መሪነት ያስወገደ ሲሆን ባለቤታቸውንም አባሯል።

እስከ ሰኞ እኩለቀን የፕሬዝዳንትነቱን ወንበር እንዲለቁ ቀነ ገደብ ጥሏል።

በመዲናይቱ ሃራሬ ቅዳሜ ዕለት በተደረገ ትዕይንተ ህዝብ ሙጋቤ ከስልጣን እንዲለቁ ሲጠየቅ የተወሰኑ ሰልፈኞች ወደ ፕሬዝዳንቱ መመሪያ ለተቃውሞ ሲያመሩ በወታደሮች ተመልሰዋል።

ሙጋቤ እሁድ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ባደረጉት ንግግር ከሕዝቡም ሆነ ከወታደራዊው ሃይል የቀረበላቸውን ጥያቄ ቸል በማለት ሌሎች ሀገራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በማውራት አጠናቀዋል።

ወታደሩ እያደረገ ያለውንም በሳቸው ስልጣን ላይ የተቃጣ ሴራ ሳይሆን ሀገሪቱን የመጠበቅ ህገ መንግስታዊ ድርጊት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ በዝግታና ዙሪያውን ሲሽከረከር በዋለው የ20 ደቂቃ ንግግራቸው አንድ ወይም ከዚያ በላይ ገጾችን ዘለው ማንበባቸውን የቀጠሉ ሲሆን በመጨረሻም ይቅርታ እንደሚሆን አድርጉት ሲሉ ተደምጠዋል።

ዛሬ ዛኑ ፒ ኤፍ የፓርላማ አባል የሆኑ አባላቱን ለስብሰባ የጠራ ሲሆን የሙጋቤን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመወሰን እንደሚመክር ታውቋል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የጉባኤው ውጤት ያልታወቀ ሲሆን በዚምባቡዌ ነገሮች በፍጥነት ሊለዋወጡ እንደሚችሉ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

ሮይተርስ የደረሰው የፓርቲው ረቂቅ ጽሁፍ በሀገሪቱ ለደረሰው የኢኮኖሞ ድቀት ሙጋቤን ተጠያቂ አድርጓል።

የዚምባቡዌ ቀውስ የጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት ሙጋቤ ምክትላቸውን ኤምርሰን ናንጋግዋን ከስልጣን ማባረራቸውን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል።

የሙጋቤ አላማ ለባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ስልጣኑን ለማስተላለፍ ነው በሚል ባለፈው ሳምንት የጦር አዛዦች የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙሃን ማሰራጭእዎች ተቆጣጥረው ፕሬዝዳንቱን በቁም እስር አውለዋል።

የቢቢሲው አንድሪው ሀርዲንግ ከሀራሬ እንደዘገበው በሙጋቤ የእሁድ ንግግር የተበሳጩት የመዲናዋ ነዋሪዎች ፕሬዝዳንቱ ተመልሰው በቴሌቪዥን ቀርበው ከስልጣን መልቀቃቸውን ያሳውቃሉ በሚል በተስፋ እየጠበቁ ሲሆን ወሬውም በሰፊው በከተማው እየተወራ ነው ብሏል።

የእሁዱ ንግግርም ፕሬዝዳንቱ የጦር አዛዦቹ ያደረጉት ድርጊት ጥፋት እንዳልሆነና የፈቀዳቸውን ማድረግ የሚችሉ እንደሆነ ለማወቅ ነው ሲሉ አብዛኞቹ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው ሲል የቢቢሲው ዘገባ አመልክቷል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.