የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ መሆኑን የትግራይ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮዎች ገለጹ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%8B%A8%E1%8B%B0%E1%88%A8%E1%88%B1-%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%88%8E%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%89%A0%E1%88%B0%E1%89%A1-%E1%88%98%E1%88%86%E1%8A%91%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%89%B5/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ተግባር ተጠናከሮ መቀጠሉን የትግራይ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮዎች ገለጹ።

የሁለቱ ክልሎች የግብርና ቢሮዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የአንበጣ መንጋ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብና የአንበጣ መንጋውን የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን በስፍራው ቅኝት ያደረገው ባልደረባችን መታዘብ ችሏል።

በመኸር እርሻ ከተዘራው ሰብል ውስጥም ከ80 በመቶ የተሰበሰበ ሲሆን፥ ሰብሎችን ለመሰብሰብና የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልም ትምህርት ቤቶችን ለተወሰነ ጊዜ በመዝጋት ተማሪዎችን ማሳተፍ መቻሉም ተገልጿል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞን የደረሱ ሰብሎችን አርሶ አደሮቹና የአካባቢው ማህበረሰብ እየሰበሰቡ ይገኛል።

በክልሉ በመኸር እርሻ ከ4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን፥ እስካሁን ባለው ሂደት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የሚገኘው ሰብል ብቻ መሰብሰቡን ቢሮው ገልጿል።

በክልሉ አንዳንድ ቦታዎችም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት አድርሷል ነው የተባለው።

ክልሎቹ በቀጣይ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ እና አሁንም ድረስ የሚታየው የአንበጣ መንጋ በምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርሰ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የአንበጣ መንጋ በሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ ሊሳተፍ እንደሚገባው የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ግርማሜ ጋሩማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት፥ 382 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ወደ 6 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የደረሰ ሰብል ተሰብስቧል ነው ያሉት።

ይሁን እንጅ ካለፉት አራት ቀናት ወዲህ እየጣለ ያለው ዝናብ በጤፍ፣ ስንዴ እና የጥራጥሬ ሰብሎች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንደሚያደርስም አውስተዋል።

ሚኒስቴሩም ለክልሎች የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ የሚቻልበትን አግባብ የተመለከተ ምክረ ሃሳብ የያዘ ሰነድ መላኩን ገልጸዋል።

የሚደርሰው ጉዳትም የሁሉም በመሆኑ መላው ህብረተሰብ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።

ከአንበጣ መንጋ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ አራት አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት በማድረግ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ከውጭ ሃገር ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን መንጋም በሚገባባቸው አካባቢዎች ሳይዛመት የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

 

 

በአወል አበራ

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.