የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ በየአካባቢው የተደራጁ የጎበዝ አለቆችን እንዳይከተል አዲሱ የክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር አሳሰቡ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/145764

DW : የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ በየአካባቢው የተደራጁ «የጎበዝ አለቆችን» እንዳይከተል አዲሱ የክልሉ ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ርስቱ ይርዳዉ አሳሰቡ።
አቶ ርስቱ ከተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለተወከሉ ተሰብሳቢዎች ትናንት እንደተናገሩት «በለዉጡ የተገኙ ድሎች» ያሏቸዉን ጥቅሞች ሕዝቡ በየአካባቢዉ ለተደራጁ ኃይላትና «የጎበዝ አለቃ» ላሏቸዉ ወገኖች አሳልፎ መስጠት የለበትም።
በደቡብ ኢትዮጵያ በተለያየ ስም የተደራጁ ኃይላት በተለይም ወጣቶች ባገባደድነዉ ዓመት በቀሰቀሱት የጎሳ ግጭት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟልም።
በተለይ የሲዳማ ዞን የክልል መስተዳድርነት ሥልጣን ይኑረዉ በሚል ጥያቄ ሰበብ ባለፈዉ ኃምሌ አጋማሽ በተቀሰቀሰዉ ግጭትና ሁከት በትንሽ ግምት ከ50 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል፣ ግምቱ በዉል ያልታወቀ ሐብትና ንብረት ወድሟል ወይም ተዘርፏል።
ሁከት፣ግጭት ረብሻዉ የበረደዉ መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ከገባ በኋላ ነዉ።ምክትል ርዕሠ መስተዳድር ርስቱ እንደሚሉት «የህዝብ ተቆርቆሪ» መስለው በየቦታው የሚንቀሳቀሱ አካላት ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ ችግር ውስጥ እያስገቡት ፣ መልካም ስሙንም እያጠለሹት ነዉ።»
አቶ ርስቱ «ሌብነታቸው» እንዳይታወቅባቸዉ በጎሳና በብሄር ስም የተሸሽጉ ወንጀለኞች» ያሏቸዉን ኃይላት ሕዝቡ ለመንግስት አሳልፎ እንዲሰጥም አደራ ብለዋል።DW እንደጠቀሰዉ በክልሉ ሰላም ካልሰፈነ የክልልና የዞን አደረጃጀት መጠየቅ ቀርቶ በሕይወት መኖርም አይቻልም-እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.