“የዶሃዉ የሙቀት ኃይለኛነት” የማራቶን ሯጮችን እስከሞት ሊያደርሥ ይችል ነበር – አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/153607

የኦሎምፒክ እና የዓለም ሩጫ ባለድሉ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ-ሥላሴ በካታር ዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር የተጀመረበት ከፍተኛ የሙቀት ወቅት ትክክለኛ ጊዜ አይደለም አለ። አሶሽየትድ ፕሬስ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን ጠቅሶ እንደዘገበዉ «የዶሃዉ የሙቀት ኃይለኛነት» የማራቶን ሯጮችን እስከሞት ሊያደርሥ ይችል ነበር።
ባለፈው ዐርብ ካታር ዶሃ ውስጥ የተጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር በሀገሪቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እና ወበቅ የተነሳ ተወዳዳሪ አትሌቶች ላይ ከፍተኛ ችግር መፍጠሩ ተገልጧል። ኢትዮጵያውያን ሴት የማራቶን ሯጮች በሙቀቱ የተነሳ ውድድራቸውን መጨረስ ባልቻሉበት ፉክክር 68 አትሌቶች ውድድሩን ለማቋረጥ ተገደዋል። ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረ-ሥላሴ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገረው ከኾነ ውድድሩ በሌላ ጊዜ ቢከናወን ይመረጣል።
«ኳታር ውድድር መኾን ካለበት በዚህ ወቅት ሳይሆን፤ መኾን የነበረበት ለኢትዮጵያም አትሌቲክስ አየሩ ጥሩ የሚኾነው በታኅሣስ ወይንም ደግሞ ቢያንስ ታኅሣስ እንኳን ባይሆን ድንገት ጥቅምት ወር ላይ ምናምን፤ በእርግጥ [የውድድሩ ወቅት] ደግሞ በጣም ይዘገያል ለዚያም ተብሎ መሰለኝ እንደዚህ የኾነው። አየሩ ያው ተፈታትኗቸዋል ልጆቻችንን። ለእዚህ ነው እኔ እንደዚህ ባይኾን ኖሮ ይመረጥ ነበር ያልኹት።»አሶሺየትድ የዜና ምንጭ ትናንት እንደዘገበው የዓለም የአትሌቲክስ ውድድር የሚካሄድባት ዶሃ የአየር ሙቀት የማራቶን ሯጭ አትሌቶችን ሕይወት ሊያሳጣ ይችል ነበር ብሏል ሲል ዘግቧል።
በትናንትናው የዶሃ የ5000 ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌት ሙክታር እድሪስ እና ሰለሞን ባረጋ የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።DW

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.