የጅማ ኢንደስትሪ ፓርክ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም የቡና ማቀነባበሪያ ማዕከል ሊደረግ ነው

Source: https://fanabc.com/2019/04/%E1%8B%A8%E1%8C%85%E1%88%9B-%E1%8A%A2%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%88%B5%E1%89%B5%E1%88%AA-%E1%8D%93%E1%88%AD%E1%8A%AD-%E1%89%B4%E1%8A%AD%E1%8A%96%E1%88%8E%E1%8C%82-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8C%A0%E1%89%80/

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጅማ ኢንደስትሪ ፓርክን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም የቡና ማቀነባበሪያ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ታጥቦ፣ ተቆልቶ፣ ተፈጭቶ እና ታሽጎ ያለቀለት ቡና በኤሌክትሮኒክ ግብይት ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፥ የቻይና ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ መቅረቡንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ “ያለቀለት” ቡና ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት በቻይና ቤይጂንግ መካሄዱንም ገልጿል።

በአለም አቀፍ ደረጃ በቡና ሽያጭ ዘረፍ የተሰማሩ ድርጅቶች በተሳተፉበት በዚህ ውይይት የኢትዮጵያ መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያርግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ አበበ አበባየሁ ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቡናን በኤሌክትሪኒክስ ግብይት ወደ ውጭ ከመላክ በዘለለ ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለመፈፀም የብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂን ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ ሁኔታ ጥያቄዎችን አቅርበው ማብራሪያ መሰጠቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.