የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያው (ማእከላዊ እስር ቤት) ከማሰቃየነት ወደ ሙዚየምነት እንደሚቀየር ተዘገበ

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/41035

አባይ ሚዲያ ዜና 

የኢትዮጵያ መንግስት በፖለቲካ አመለካከታቸው ለእስር የዳረጋቸውን ተቃዎሚዎች እና የፖለቲካ እስረኞችን እንደሚፈታ ባወጣው መግለጫ አሳወቀ።

በደረግ ስርአት እስረኞች ሲሰቃዩባቸው የነበረውና የደርግን መንግስት በመገርሰስ ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ አገዛዝ ለ 26 አመታት ተቃዋሚዎችን እንዲሁም ፖለቲከኞችን በማሰር እያሰቃየበት ያለውንም የማእከላዊ እስር ቤትን ለመዝጋትም ውሳኔ እንደተደረሰ በዚሁ መግለጫ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸው እንዲህ አይነት ውሳኔ ላይ መድረሱ በአገሪቷ ለሚደረገው ፖለቲካዊ ውይይት በር ከፋች ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ በመንግስት የተደረሰው ይህ ውሳኔ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እና የሚፈቱት እስረኞች በትክክል እነማንን እንደሚያካትት በግልጽ አላስቀመጡም።

አገዛዙን በፖለቲካ ሲገዳደሩት የነበሩ ተቃዋሚዎች ለ 26 አመታት ከሚታሰሩበትና ከሚሰቃዩበት እስር ቤቶች መካከል ውስጥ በተለምዶ ማእከላዊ እስር ቤት ተብሎ የሚጠራው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያ ሲሆን ወደ ፊት ዘመናዊ እስር ቤት ተገንብቶ  በእስር ለማቀቁት እስረኞች መታሰቢያ እንዲሆን ሙዚየም እንደሚሆን  ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም መግለጻቸው ተዘግቧል።  

የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያውን ወይም የማእከላዊ እስር ቤቱን ለመዝጋት ከመንግስት በኩል የተደረሰው ውሳኔ  በኢትዮጵያ ያለውን የመብት ረገጣ ለማስቆም አበረታታች ምልክት ሆኖ መቆጠር እንደሚችል አምንስቲ ኢንተርናሽናል ጠቁሟል። ነገር ግን ውሳኔው በዚሁ የማሰቃያ እስር ቤት ውስጥ  የተፈጸሙትን ወይም እየተፈጸሙ ያሉትን በደል እና ግፍ ወደ ፍርድ አደባባይ ሳይወጡ እንዲያው ለማድበስበስ የሚደረግ ጥረት መሆን እንደሌለበት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በተጨማሪ አሳውቋል።

የብርታኒያው ቢቢሲ በእንግሊዘኛው አምዱ ላይ አገዛዙ የምእራብያኑ ወዳጅ እንደሆነ ጠቅሶ በፓለቲካ አመለካከታቸው የሚቃወሙትን ሰዎች ልሳን ለማዘጋት የጅምላ እስራት እንደሚፈጽም በመብት ተከራካሪዎች የሚቀርብበትን ክስንም በመጥቀስ ሪፖርቱን አቅርቧል።  በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የሽብርተኛ ህጉን የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን አሊያም ተቃዎሚዎችን ወደ እስር ቤት ለማስገባት እየተጠቀመበት እንደሆነ  የተለያዩ የመብት ተከራካሪ ድርጅቶች ክሳቸውን እያሰሙ እንደሚገኙም በተጨማሪ ቢቢሲ በእንግሊዘኛው ሪፖርት አስነብቧል።

የፌዴራል የወንጀል ምርመራ መምሪያ ወይም በተለምዶ ማእከላዊ እስር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ እስረኞችን የማሰቃያ ወህኒ ቤቶች ውስጥ አገዛዙን በመቃወም የአማራና የኦሮሞ ማህበረሰብ ተወላጆች ታስረው እንደሚገኙ ቢቢሲ በዚሁ በእንግሊዘኛው ዘገባው አትቷል። ከ2015 እኤአ ጀምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ እንዲሁም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልሎች እየታየ ባለው የህዝብ ተቃውሞ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ተቃዋሚዎች እንዲሁም  ሙያቸው በሚፈቅድላቸው መንገድ አገዛዙን በብእራቸው ሲተቹ የነበሩ ጋዜጠኞች በየእስር ቤቱ ታጉረው እንደሚገኙ የቢቢሲው ባልደረባ ኢማኑኤል ለአንባቢያን አስፍሯል።

በተለያዩ የማሰቃያ እስር ቤቶች የግፍ ጽዋን እየተጎነጩ የሚገኙ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥራቸውን ለማወቅ ከባድ እንደሆነ የጠቀሰው የቢቢሲ ባልደረባ ኢማኑኤል የሽብር ህጉን በመታከክ ወደ 1000 የሚደርሱ ሰዎች በየእስር ቤቶች ሳይወረወሩ አይቀርም በማለት ዘግቧል። በአገሪቱ በተነሳው የህዝብ ተቃውሞ ምክንያት ባሳለፍነው ጥቅምት 2016 እኤአ ተደንግጎ የነበረውን የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅን በመጠቀም አገዛዙ በተለያዩ እስር ቤቶች ያሰራቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር በግምት ወደ 5000 እንደሚደርስ ይህ የቢቢሲ እንግሊዘኛ አምድ ባልደረባ ለአንባቢያን ገልጿል።

በአገዛዙ ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ ድርጅቶች መካከል ውስጥ የግንቦት ሰባት የቀድሞው ዋና ጸሃፊ  የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም አገዛዙን በመቃወም ሲያደርጉ በነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ምክንያት ከ 2014 እኤአ ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙና በሌሉበት የተበየነባቸውን የሞት ቅጣት እየተጠባበቁ መሆኑን በመግለጽ በያዝነው ሳምንት ብቻ የግንቦት ሰባት አባል በመሆን ሲሰሩ ነበሩ የተባሉ 19 ግለሰቦችም የፍርድ ቅጣት እንደተበየነባቸው ኢማኑኤል አስነብቧል። ለሮይተርስ በዜና ሪፖርተርነት የሚያገለግለው አሮን ማሾ በበኩሉ አገዛዙ ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጀው የኦነግ ድርጅት ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው በሽብር ክስ በርካታ ዜጎች በየእስር ቤቱ እንደሚገኙ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከእህት ድርጅቶች ጋር በመሆን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ በዘገበበት የዜና አምዱ ጠቅሷል።

የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የቀድሞው የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም ሌሎች የኦፌኮ አባላትን ከእስር እንዲፈቱ በመጠየቅና ኢፍትሃዊ የከተማ ማስተርፕላን ማስፋፋቱን ጨምሮ የፖለቲካ አፈናውን በመቃወም ሰልፎች ሲደረጉ እንደነበረ ሮይተርስ ዘግቧል። ከ 2015 እስከ 2016 እኤአ አገዛዙን በመቃወም በተቀጣጠለው የህዝብ ቁጣ ወደ 700 የሚደርሱ ኢትዮጵያኖች መገደላቸውን ሮይተርስ ጠቅላይ ሚንስር ሃይለማርያም ደሳለኝ ማእከላዊ እስር ቤት ተዘግቶ እስረኞችን የመልቀቅ ውሳኔ ላይ መንግስታቸው እንደደረሰ  ያሳወቁበትን ጋዜጣዊ መግለጫ በዘገበበት ዜና ላይ  አስነብቧል።

የፌዴራል የወንጀል ምርመራ መምሪያ ወይም በተለምዶ ማእከላዊ የሚባለው እስር ቤት ከመዘጋቱ በፊት በሰዎች ላይ ሲፈጸም የነበረው ስቃይ ተጣርቶ፤ ይህን ስቃይ የፈጸሙ የአገዛዙ ባለስልጣናት ለፍርድ መቅረብ እንዳለባቸው አምንስቲ ኢንተርናሽናል መጠየቁን  ሮይተርስ እና ቢቢሲ የአምንስቲን የምርምር ባለሙያ ዋቢ በማድረግ በዜናቸው አስነብበዋል። በማእከላዊ እስር ቤት በፖለቲካ እስረኞችም ሆነ በጋዜጠኞች ላይ የስቃይ ወይም የቶርቸር ድርጊትን አልፈጸምኩም በማለት አገዛዙ እንደካደ በመዘገብ ሌላ እስር ቤት ተገንብቶ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያው (ማእከላዊ እስር ቤት)  ሙዚየም እንደሚሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጻቸውን ቢቢሲና ሮይተርስ በዜና ዳሰሳቸው አስፍረዋል።

የኦህዴድና የብአዴን ድርጅቶች አገዛዙን በመቃወም በአገሪቷ የተደረጉትን ግዙፍ ሰላማዊ ሰልፎችን መሰረት በማድረግ አገዛዙ በአፈና የያዘውን ፖለቲካ እንዲለውጥ እንዲሁም የአማራና የኦሮሞ ህዝቦችን መብት እንዲያከብር ጫና እንዳሳደሩበት ቢቢሲ በመጥቀስ እነዚህ ድርጅቶች ባሳደሩት ጫና ምክንያት በጠቅላይ ሚንስትር ሃይለ ማርያም የሚመራውን አገዛዝ ለውጥ ማድረግ አማራጭ የሌለው ግዴታ እንደሆነ እንዲያውቅ ማስቻላቸውን  አትቷል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ ያሉትን የህሊና እስረኞችን ለማሰብ በፈረንጆቹ ዲሴምበር 2017እኤአ ወር ከፍተኛ አለም አቀፍ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሲካሄድም እንደነበረ የቢቢሲው እንግሊዘኛ ዜና ክፍል ባልደረባ  ለአንባቢያን አሳውቋል።

 

 

Share this post

One thought on “የፌዴራል ወንጀል ምርመራ መምሪያው (ማእከላዊ እስር ቤት) ከማሰቃየነት ወደ ሙዚየምነት እንደሚቀየር ተዘገበ

  1. ማእከላዊን ዘግቶ ሌላ እስር ቤት መገንባት ለምን አስፈለግ? ዞሮ ዞሮ የፖለቲካ እስረኛ ለማጨቅ አይደል? ሌላ ወንጀለኛ ለማሰርማ ያሉት ከበቂ በላይ ናቸው፡፡ እንዲ ነው በጥልቀት መለወጥ!!

    Reply

Post Comment