ያለአግባብ ወጪ የተደረገን የኮቪድ 19 ገንዘብ ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ መሰራቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከ…

ያለአግባብ ወጪ የተደረገን የኮቪድ 19 ገንዘብ ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ መሰራቱን የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በኮቪድ 19 ለይቶ ማቆያ ለሰሩ እና ላስተባበሩ ሰዎች ክፍያ እንዲፈፀም በሚል የክልሉ መንግስት በመመሪያ ቁጥር 20/2006 መሰረት በወረዳው በተቋቋመ ግብረሃይል የሰሩና ያስተባበሩ ሰዎች ተለይተዉ ክፍያ እንዲፈፀላቸው የተወሰነ መሆኑ ተጠቅሷል። ይሁን እንጅ ከመመሪያ ውጭ ሳይገመገምና ሳይለይ ክፍያ በመፈፀሙ ለበርካታ አቤቱታና ቅሬታ ምንጭ በመሆኑ የመንግስት ሰራተኛዉና የህብረተሰቡ ጥቆማ ለምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል የደረሰው መሆኑን አውስቷል። የሰነድና የሰዉ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ ምርመራውን ማጣራቱን የገለፀው የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል በዚህም መሰረት፦ 1ኛ)የመንግስት ሰራተኛ ያልሆኑትን የመንግስት ሰራተኛ እንደሆኑ አድርጎ ክፍያ መፈፀም፣ 2ኛ) በከፍተኛ ትምህርት ላይ ላሉ የመንግስት ሰራተኞች ክፍያ መፈፀም፣ 3ኛ)ደመወዝ የሌላቸዉን ደመወዝ እንዳላቸዉ አድርጎ ክፍያ መፈፀምና የተለያዩ የአሰራር ብልሹነትን የታየበትና ያለአግባብ የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዲባክን በመደረጉ ለበርካታ የመንግስት ሰራተኞች የስራ ተነሳሽነትንና እምነትን እንዲያሳጣ አድርጓል ሲሉ የዞን ፖሊስ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና ክፍል ኃላፊ ዋ/ኢ/ር ክንዱ በላይ ገልፀዋል። ኃላፊዉ እንዳስረዱት ምርመራዉን በቡድን በማጣራት አንድ የወረዳዉ ጤና ጣቢያ ኃላፊን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ በመጣራት ላይ ሲሆን ያለአግባብ የተከፈለ ክፍያ የ34 ግለሰቦች 333,612/ ሶስት መቶ ሰላሳ ሶስት ሺ ስድስት መቶ አስራ ሁለት ብር ተመላሽ እንዲደረግ ተደርጓል ሲሉ አክለዉ ገልፀዋል። በመጨረሻም ህብረተሠቡ ለሠጠን ጥቆማ በዞኑ ፖሊስ መምሪያ ስም ከልብ እያመሰገን ቀጣይም እኒህና መሠል የሙስና ድርጊቶች ሲፈፀሙ አስፈላጊውን ጥቆማና መረጃ በመስጠት እንዲተባበር አሳስበዋል። የአሰራር ብልሹነት እና ሌሎችንም ጨምሮ ህዝብና መንግስት የጣለባቸዉን ኃላፊነት ባልተወጡ አመራርና ባለሙያን ለመጠየቅ የዞኑ ፖሊስ ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑን እናሳዉቃለን ብለዋል ሲል የዘገበው የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሚዩንኬሽን ሚዲያ ዋና ክፍል ነው። የአማራ ሚዲያ ማዕከልም ለኮቪድ 19 ተጋላጮች በሚል ከክልል የተላከ ገንዘብ አላግባብ ለአመራሩ እንዲከፋፈል ተደርጓል በሚል የደረሰውን ቅሬታ መሰረት አድርጎ የዘገባ ሽፋን የሰጠ መሆኑ ይታወቃል። በወቅቱም የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ቅሬታውን ካዳመጡ በኋላ ስልክ በመዝጋት፣የዞኑ የማህበራዊ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ደግሞ አሁን አይመቸኝም፣ ደጋግመህ ስትደውል አንገብጋቢ ጉዳይ መስሎኝ ነው ስልኩን ያነሳሁት በማለት ምላሽ ለመስጠት አለመፍቀዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ከቀናት በፊት የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማስታወቁም ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply