ያላባራው የኢትዮጵያውያን መከራና የተናቀው የወንጌል እውነት – ግልጽ ደብዳቤ ለወንጌላዊ አማኞች በመላው ዓለም ለምትኖሩና በደሙ ለተዋጃችሁ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ፦

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/42435

ዳላስ/ቴክሳስ ውስጥ ከምንገኝ በጌታ ከሆንን ወገኖቻችሁ

በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም ሠላምታችን ይድረሳችሁ:: ይህ ደብዳቤ የተጻፈላችሁ ብዙዎቻችን ተወልደን ባደግንባት አገራችን ውስጥ ህዝባችን እየደረሰበት ያለው እጅግ ሰቅጣጭ ሰቆቃና መጠነ-ሰፊ ግፍ በብርቱ ካሳሰበን፤ በአሜሪካ ሃገር፥ በቴክሳስ ግዛት፥ ዳላስና ፎርት ዎርዝ አካባቢ ከምንኖር ጥቂት ወገኖቻችሁ ነው። ይህ ‘ጉዳይ’ እኛን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑትን በሙሉ በብርቱ ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ ስለሆነ ትብብራችሁን በመፈለግና [የእስካሁኑም በኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞች ዘንድ ያረበበው ዝምታ እንቆቅልሽ ስለሆነብን፥ ቅሬታችንን ሳንደብቅ] ጌታችን ኢየሱስ “… በህጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን … ንቃችኋልና …”ብሎ በግሳጼ ያስተማረው በእርግጥም ችላ መባሉን እየጠቆምን የፍትህን ነገር በተመለከተ የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞች አቋም መገለጫ ሆኖ የቆየው ዝምታ አክትሞ ክርስቶስን ወደመምሰል ልንቀረጽባቸው ወዳሉት የእምነታችን ተግባራዊ መገለጫዎች በመመለስ ለታፈነው ህዝባችን ድምጽ እንድንሆነው የግፉ ሰለባ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጠበቃቸው ሆነን እንድንቆም ጥሪ በማቅረብ የሚከተለውን እንድንጽፍላችሁ የግድ ሆኖ አግኝተነዋል::     

ባለፉት ብዙ ዓመታት ተዓማኒነት ባላቸው ታላላቅ የሚዲያ ተቋም ዜና ማሰራጫዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሚያወጧቸው ዘገባዎችና የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርትም እንኳን ሳይቀር በትውልድ አገራችን ውስጥ ስለሚፈጸመው መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በስፋት ተጽፏል:: በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ሰቆቃ ጭራሽ እየከፋ መጥቶ ባለፈው ጥር 15/2010 ዓ.ም. (Jan. 23, 2018) ጥምቀትን ለማክበር በወጣው ህዝብ ላይ “ፀረ-መንግሥት መዝሙሮች ዘመሩ” በሚል ሰበብ ‘የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር’ ብሎ ራሱን በሚጠራው ድርጅት የሚመራው የመከላከያ ኃይል በከፈተው የእሩምታ ተኩስ ሰዎች እንደተገደሉና ቁጥራቸው የበዛ ደግሞ እንደቆሰሉ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ራቪና ሻምደሰኒ (Ms. Ravina Shamdasani) ገልጸዋል:: የተለያዩ የዜና ምንጮች እንደዘገቡት ደግሞ የሟቾች ቁጥር ቢያንስ አስራ ሁለት መሆኑንና ከተገደሉትም ውስጥ አንዱ የአስር ዓመት ታዳጊ ልጅ እንደሆነ ተጠቅሷል::

የዚህ ዓይነቱ እብሪት የተሞላበት ጭካኔና ኢ-ሰብዓዊነት ሊቀሰቅሰው የሚችለውን የህዝብ ቁጣና ተያይዞም ሊመጣ የሚችለውን መዘዝና ጠንቅ መገመት ብዙም አያዳግትም:: ስለሆነም ነው ታዲያ በዚህ ወቅት በህዝባችንና በትውልድ አገራችን ላይ የተጋረጠውን እጅግ አሳሳቢና አደገኛ ሁኔታ በመገንዘብ ያ የምንፈራው የእርስ-በእርስ ጦርነት እንዳይከሰት ዛሬ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ እውነትን ተመርኩዘን ትዝብታችንን፣ ሃሳባችንን እንዲሁም አቋማችንን በግልጽ ልናሳውቃችሁ የወደድነው።

በህዝባችን ዘንድ የቆየው የረጅም ዘመናት በክፉም በደጉም አብሮ ተቻችሎ የመኖር ዘይቤው በብሔርተኞች የፖለቲካ አባዜ ጠንካራ ፈተና ሲደርስበትና በተለያዩ ቦታዎች የህዝቡ ሰላም ሲደፈርስ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ መኩሪያና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ልዩ አርአያ ሆኖ የቆየው አንድነታችንና የነጻነት ታሪካችን ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ወገኖቻችን ከአገራችን ተሰደው በሔዱበት ሲታረዱና ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው ህዝቡ በአገሩም ውስጥ ሆኖ “እኔ ነኝ የምመራህ!” ብሎ አስተዳደሩን በኃይል ጨምድዶ በያዘው አምባገነናዊ መንግሥት መጠነ-ሰፊ በደል ሲደርስበት፦ ግድያ ሲፈጸምበት፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከቀዬው ሲፈናቀል በ’ዘር ማጽዳት’ ወንጀል ቤቱን አቃጥለው በአገሩ ውስጥ ስደተኛ ሲያደርጉት ዘርን ማዕከል ባደረገ የአድልዎ አሠራር ክፉኛ ሲቀጡት [የተባበሩት መንግስታት ተቋሞች እንኳን (UNDP) በይፋ ዘግበው ጉድ! እስኪሉ ድረስ] የህዝብ ንብረት ሲመዘበር፣ . . . ወዘተ)  ብዙዎች የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ክፍሎች ተቃውሟቸውን በማሰማት የዜግነት ግዴታ ድርሻቸውን ሲወጡ፥ ጥቂት የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞች  በግል እና እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ተቋማት ደግሞ በተናጠል ከሚያደርጉት ተሳትፎ በቀር አብዛኛው የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞች ኅብረት በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ (እንደ ቤተ ክርስቲያን) ዝምታን መርጦ እስከዛሬ ድረስ መቆየቱ የማይካድ ሐቅ ነው:: ይሄ ነገር በብዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ዘንድ ጥያቄና ቅሬታን ማስነሳቱ አልቀረም:: በተለምዶ ’ ኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞችን’ “ጴንጤ” በሚል ሥያሜ የሚጠራው ሰፊው የኅብረተሰባችን ክፍል፦ “ለምንድን ነው ጴንጤዎች ስለአገራቸውና ስለህዝባቸው ግድ የማይላቸው? ህዝባችን በግፍ ሲገደል እያዩ እንዴት ነው ዝም የሚሉት? ” ብሎ ደጋግሞ ሲጠይቅ ይደመጣል:: እንዲያውም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ – ሰው ከፈጣሪው የተቸረውን በጉልበተኞች የመነጠቅ ነገር  ከምንም በላይ በተቀዳሚነት ሊታይ የሚገባው የሞራል ጉዳይ ሆኖ ነው ( … is an issue of morality) ብሎ ስለሚያምን፤ ይኸው ኅብረተሰብ “እነሱ (መንፈሳውያን ነን የሚሉቱ) በዚህ ጉዳይ ከፊት ሊቆሙ በተገባቸው ነበር::” ሲልም ይሰማል:: ይህ ታዲያ እውነተኛ አባባል ነው::

እውነቱ እንግዲህ ይህ ከሆነ ለኢትዮጵያ ወንጌላዊ አማኞች ዝምታ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? ካንዳንድ ወገኖቻችን ጋር ካደረግናቸው ውይይቶችና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲባሉ ከሰማናቸው ውስጥ የሚከተሉት እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ናቸው፦

 • “አገራችን በሰማይ ነው:: እኛ በዚህ ምድር መጻተኞች ነን::” ሲሉ የሚደመጡ አሉ::
 • “የዜጋ መብት የሰብዓዊ መብት የኅብረተሰብ ፍትሕና የመሳሰሉት ነገሮች የፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው:: እኔ ደግሞ ፖለቲካ አልወድም:: ፖለቲካ ለክርስቲያኖች አይበጅም:: እንዳውም ከመንፈሳዊ ውጪ የሆነ ነገር ሁሉ ኃጢዓት ነው::” የሚሉ ደግሞ አሉ::
 • “እኛ የማምለክ ነጻነት እስካገኘን ጊዜ ድረስ ስለ ሌላው ነገር ግድ አይለንም::” ብለው የሚናገሩም አልጠፉም::
 • “በፊት ያልነበረ የከተማ ውስጥ የባቡር . . . አገልግሎት ዛሬ አለ የቀለበት መንገድ አለ ፣ ብዙ ህንፃ እየተሰራ ነው . . . ወዘተ.        እና ምን ይሁን ብዬ ነው የተቃውሞ ድምጽ የማሰማው?” ብለው ክቡር የሆነውን ነፃነት በህንጻና በሸቀጦች ዋጋ የተመኑም አሉ::

በመጀመሪያ “እኛ አገራችን በሰማይ ነው:: የዚህ አለም ጣጣ (ኢትዮጵያም ውስጥ እንኳን የሚፈፀመው በደል) የኛ ጉዳይ አይደለም” ለሚሉት:

በቅርቡ የወንጌል አገልጋይ የሆነ ወንድማችን (ያሬድ ጥላሁን) በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ደብዳቤው ላይ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር:: “አገሬ በሰማይ እንደሆነ ባውቅም ፣ ያየኋትን ምድራዊ አገሬን ሳልወድ ያላየኋትን ሰማያዊ አገር እወዳለሁ ብል ቃሉ ውሸታም ይለኛል::”    ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል:: እያንዳንዳችን በአፋችን የምንላቸው ሳይሆን የምንተገብራቸው ነገሮች ቢፈተሹ የሚመሰክሩብን ከተወለድንበትና ካደግንበት ምድርና ህዝብ ጋር ትሥሥርና ቁርኝት እንዳለን ነው:: ያንን ሐቅ አንካደው:: እውነቱ ያ ከሆነ ደግሞ ኃላፊነትን ለመሸሽ “ሐረግ” አንጎትት::

2ኛው ሳሙ 10:12 ኢዮአብ ለወንድሙ እንዲህ ሲል ተናገረ ተብሎ ተጽፎ ይገኛል፦ “እንግዲህ በርታ፤ ለህዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ …” ፦ ለህዝብና ለምድሩ ትልቁን መስዋዕትነት ለመክፈል ራስን የመስጠት ምሳሌ ነው::

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፈ እዝራና ነህምያን ስናነብ ለእምነታቸው ካላቸው ቅናት ሌላ ጎልቶ የምናየው ለምድራቸውና ለወገኖቻቸው የነበራቸውን ልዩ የአገር ፍቅር ስሜት ነው:: እነርሱ እንኳን ባይወለዱባትም አባቶቻቸው የተፈናቀሉባትንና፤  ፈራርሰውም የነበሩትን የኢየሩሳሌምን ከተማ ቅጥሮች፣ በሮቿንና ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመገንባት ያደረጉትን ትጋት፣ ከተማውንና ወገኖቻቸውን ከጥቃት ለመከላከል ጦረኞችንና ቀስተኞችን ስለማሰለፋቸው ስናነብ፤ መጀመሪያ በስደት የሄደው ትውልድ (the first generation) ብቻ ሳይሆን ቀጣዩ ትውልድም እንኳን ከእናት አገሩና ወገኑ ጋር ትሥሥርና ቁርኝት የነበረውና ለእምነቱ፣ ለ’እናት’ አገሩና ለህዝቡ ግድ ይለው እንደነበር ነው የምንረዳው:: ከዚህም በመነሳት ስለ አገር-ወገን ማሰብ፣ መቆርቆርና ራስን አሳልፎ መስጠት የእግዚአብሔር ቃል የሚደግፈው እንጂ የሚቃወመው አለመሆኑን ነው የምንገነዘበው::

ሌላም መጨመር ቢያስፈልግ ፦ ብዙ ጊዜ በምንዘምረው በመዝሙር 137: 1-6 ተጽፎ የሚገኘው ወደ ባቢሎን በምርኮ የተወሰዱት የጽዮን ሰዎች ያሉት ተመሳሳይ ትምህርት ሊሰጠን የሚችል ጥቅስ ነው::

“በባቢሎን ወንዞች ማዶ አዝነን ተቀምጠን ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ እጅግ አለቀስን::  . . .  ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ።

ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።

እንዲሁም በሐዲስ ኪዳን : በሉቃስ ወንጌል 19:41-44  ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌምና ልጆቿ እንዳለቀሰላት ተጽፎ እናነባለን:: ከዚህም ጥቅስ የምንረዳው አንድ ነገር ቢኖር ኢየሱስ ለከተማዋና ለ’ልጆቿ’ ልዩ ፍቅር እንደነበረው ነው:: እንግዲህ ይህንን ሁሉ ያልነው “እኛ አገራችን በሰማይ ነው:: የዚህ አለም ጣጣ (ኢትዮጵያም ውስጥ እንኳን የሚፈፀመው በደል) የኛ ጉዳይ አይደለም” ለሚሉ ይህ አተያይ ትክክለኛ ካልሆነ መረዳት የመነጨ ስለሆነ (አገርና ወገን ክፉ በደል ሲደርስበት) ዝምታው ከዛ የተሳሳተ ግንዛቤ ጋር የተዛመደ ከሆነ ሊታረም ይገባዋል ለማለት ነው::

“የዜጋ መብት …” ብሎ ጥያቄ ማቅረብ፣ ያንንም በመመርኮዝ መብትን ለማስከበር መሞከር ለክርስቲያኖች አይገባም ለሚሉት፦  እንግዲህ የክርስትና እምነት ተከታዮች ለሆንን ዳኛችን የእግዚብሔር ቃል ነውና ወደዛው እንመለስ::

በሐዋ. ሥራ 22: 24-28 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እንዲህማ ልታደርጉኝ አትችሉም:: እኔኮ ሮማዊ ዜግነት ያለኝ ሰው ነኝ’ (paraphrased) ብሎ ሲመልስ እናያለን:: በእርግጥም ጳውሎስ የሮማዊ ዜግነት ስለነበረው፤ ሮማዊ ዜግነት ያለው ደግሞ ቢከሰስ እንኳን ያለ ፍትህ-ሂደት ቅጣት/ግፍ ሊፈጸምበት እንደማይገባ/እንደማይችል ያውቅ ስለነበር ነው የዜግነት መብቱን በመጠቀም በዚያን ወቅት ሊደርስበት ከነበረው የአካል ግርፋትና ሰቆቃ ራሱን ያዳነው:: እንግዲህ የሐዲስ ኪዳንን ሲሶ (1/3ኛ) መልዕክት ጽፏል ተብሎ የሚነገርለት የወንጌል ሐዋርያ የዜግነት መብቱን መጠቀም አግባብ ያለው ሆኖ ካገኘው – ማነው ዛሬ ይህንን መብት በፖለቲካዊነት ፈርጆ “ለክርስቲያኖች አይገባም” የሚለው? እኮ በየትኛው ሥልጣን?

ብዙ የወንጌላዊ እምነት ተከታዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣኑን በአምባገነናዊነት የሚመራው መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና አስከፊ በደል በህዝቡ ላይ እየፈጸመ እንደሆነ ቢያምኑም እንኳን የሚሏት አንድ የተለመደች አባባል አለች፦ “እኔ የፖለቲካ ሰው ስላልሆንኩ : ማድረግ የምችለው መጸለይ ነው:: እና በቃ! ያው :  በጸሎቴ አስባቸዋለሁ::” በመሰረቱ ጸሎት መልካም ስለሆነ በእውነትም የሚጸልዩ ከሆነ እሰዬው ነው:: ግን ደግሞ “እኔ የፖለቲካ ሰው ስላልሆንኩ : ማድረግ የምችለው” ሲሉ የሚናገሩት ችግር ያለበት አባባል ነው:: እስቲ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንጻር ይህንን አባባል እንየው ፦

ያዕቆብ 2:14-17

“ወንድሞቼ ሆይ፤ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ሥራ ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ያለው እምነት ሊያድነው ይችላልን?

አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚለብሱት ልብስም ሆነ የሚመገቡት ምግብ አጥተው፣ ከእናንተ መካከል አንዱ፣ “በሰላም ሂዱ፤ አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” ቢላቸው፣ ለሰውነታቸው ግን የሚያስፈልጋቸውን ባይሰጣቸው፣ ምን ይጠቅማቸዋል?  

እንዲሁ ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው።”

ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት እንደሚያስተምሩን ዐቅም ለሌላቸው፣ ለተበደሉ፣ ለተቸገሩና ለተገፉ ጥብቅና እንድንቆም፣ እንድንታደግ፣ ከግፈኞች እንድናስጥላቸውና መብታቸውን እንድናስከብርላቸው የሚያዝዘን ራሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው:: ይህንን ባናደርግ ፍትሕን እናጓድላለን:: ማጓደል ብቻ አይደለም፤ በዝምታችን (“ግፉና በደሉ አልቆረቆረንም” እያልን ነው:: ለበዳዮቹ ደግሞ “ይመቻችሁ” የሚል መልዕክት እያስተላለፍን ነው::) ለክፉዎቹና/ለግፈኞቹ እያደላን ነው ማለት ነው::

ሌላው፦ በጣም ግልጽ በሆነ መልኩ የተቀመጠው የያዕቆብ መለዕክት – በሥራ የማይገለጥ “እምነት”/ቃላት/ጸሎት “የሞተ” ነው ሲለን      “እኔ ማድረግ የምችለው መጸለይ ብቻ ነው” የሚለውን አባባል ደግሞ በሥራ የማይገለጥ ከሆነ (ከንቱ ፡ ትርጉም የለሽ / ለለበጣ የሚባል / ራስን ማታለያ / ፍሬ-ቢስ ነው) ብለን ልንወስደው እንችላለን ማለት ነው በሌላ አነጋገር::

የሰብዓዊ መብትና የዜጋ መብት ጉዳይን ሞራላዊነት ገፍፈው የፖለቲካ ነገር ነው ብለው ምክንያት የሚሰጡ ሰዎች ላንዳፍታ ቆም ብለው ያለፉበትን የህይወት ጉዞ መንገድና ከዛም ጋር ተዛማጅ የሆኑ የታሪክ ክስተቶችን አጣምረው ለማየት ቢሞክሩ ዛሬ እነሱ እንደዋዛ (for granted) ወሰደው ለሚኖሩት ኑሮ (the American dream) ለሚያጣጥሙት ለማንኛውም ትልቅና ትንሽ ነገር ሁሉ መሰረቱ እና ዋነኛ ምክንያት የሆነው ከአምስትና ስድስት አስርት ዓመታት በፊት ቀደም ብለው የተነሱ፤ ማስተዋልና ጽኑ እምነት ያላቸው የእግዚአብሔር ሰዎች የእነዚህን መብቶች ጉዳይ በሞራላዊነት እንጂ በፖለቲካ ጉዳይነቱ ብቻ ባለመፈረጃቸው እንደሆነ ወይ የማያውቁ አሊያም የዘነጉ መሆኑን ነው::

ታዲያ “የሰብአዊ መብት ጉዳይ የፖለቲካ ነገር ስለሆነ …” ብለው ተልካሻ ምክንያት ለሚሰጡ ሰዎች “እኛ – የዜጋዊ መብት እኩልነት እንዲከበር በተደረገው ትግልና ከዛም በተገኘው ድል ምክንያት ወደ ምድረ አሜሪካ ለመምጣት እድል አግኝተን የመጣን ሰዎች [ሌላው እንኳን ቢቀር በድሉ ተጠቃሚነታችን ምክንያት] ወገኖቻችን ከፈጣሪ የተቸሩትን ሰብአዊ መብት ‘ጠብ-መንጃ’ በያዙ ጉልበተኞች ሲነጠቅ እያየን ዝም እንዳንል የሞራል ኃላፊነት አለብን” ስንላቸው ከሚሰጡን መልሶች ውስጥ “እኔን እዚህ አገር ያመጣኝ እግዚአብሔር እንጂ …” (ስብዕናን ዝቅ የሚያደርግ ዓይነት ቃልም በመጠቀም) “… ሰው አይደለም::” የሚሉት ዋነኛ ተጠቃሽ ነው:: ታዲያ ይህ አባባል ለተናጋሪው መንፈሳዊ ካባን ያከናነበና የእምነት ሰው አስመስሎ ያቀረበ ቢሆንም የአባባሉን አውድ/context [የሰውን ስብዕና የሚያዋርድና፣ ጌታችን የፍትሕን ነገር ችላ አትበሉ ብሎ ያዘዘውን እምቢ የሚል ሰው – ራሱን የእምነት ሰው አድርጎ ሲያቀርብ] ከአባባሉ የምንገነዘበው ወይ አላዋቂነቱን አሊያም ቅጥ ያጣ ድፍረቱን ነው::

ብዙዎቻችን በተለይም ወደ ምድረ አሜሪካ የመጣነው ስላመጣጣችን (ለትምህርትም ይሁን ወይ በስደት፣ በ D.V. ሎተሪ ወይም ደግሞ በጋብቻ … ወዘተ) የራሳችን የሆነ ትርክት (personal narrative) አለን::  ታዲያ የብዙዎቻችን ትርክት ለመምጣታችን ስኬት ምክንያት የሆነውን ሁሉንም እውነት አይተርክም:: እንዲያውም በአላዋቂነትም ቢሆን የድፍረት ቃሎቻችን የሚያሳዩት ግንዛቤያችን የተዛባ መሆኑን ነው:: በአለም ላይ የሚሆነው ማንኛውም ክስተት ሉአላዊ በሆነ አምላክ ይሁንታ (orchestration) እንደሚሆን ያለን እምነት እንደተጠበቀ ሆኖ ክርስቶስን መምሰል በተግባር መገለጫው ምን እንደሆነ የገባቸው ባለ ራዕዮች የከፈሉት ዋጋና ያደረጉት ትግል እኛ እዚህ መጥተን በነጻነት መኖር እንድንችል የቁልፍ ያህል በር ከፋች ምክንያት መሆኑን የተገነዘብን አይመስልም::  ይህ እውነት እንደሆነ ታሪካዊ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል:: እንደው ለማገናዘብ እንዲረዳ – ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዛሬ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም (እ.ኤ.አ.) ከ1960ዎቹ ዓ/ም በፊት ለትምህርትም ሆነ … ወዘተ ይመጡ/ይኖሩ የነበሩ የኢትዮጵያውያን ቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት ነበር:: ቢገመት እንኳን በጣም ትንሽ ከመሆኑ የተነሳ ምናልባት ከመላኩ በያን እና ከሌሎች ጥቂት በጣት ከሚቆጠሩ በቀር ብዙ ልንጠቅስ አንችልም:: ያ ታዲያ አለምክንያት አይደለም:: እስቲ ለነዚህ ነገሮች ዋነኛ ምክንያት የነበሩትን ላንዳፍታ እንመልከት::

TIMOTHYPNIXON በሚል ሥም WordPress.com ተብሎ በሚታወቀው blog site ላይ Sept. 6, 2015 ጦማሪው ጽፈው ባስነበቡን መጣጥፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ነገር እናገኛለን፦

Oct. 3, 1965 በፕሬዘደንት ሊንደን ጆንሰን የተፈረመው “Hart-Celler Immigration bill” እየተባለ የሚታወቀው የስደተኞች ህግ ‘አዲሱ’ የአሜሪካ መርህ (ፖሊሲ) ከመሆኑ በፊት ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ከሚፈቀድላቸው ሰዎች ውስጥ 70%(ኡ) የተመደበው ከሶስት አገሮች ለሚመጡ ብቻ ነበር:: እነዚህም አገሮች አየርላንድ ፣ ታላቋ ብሪታንያና ጀርመን ናቸው::” አያይዘውም የቀረው 30% መደብ ተጠቃሚዎች የነበሩትም ባብዛኛው የደቡብ አውሮፓ (የኢጣልያ፣ የግሪክ፣ የፖርቱጋል … ወዘተ) አገር ዜጎች እንደነበሩ ይጠቅሳሉ::

ይህ “Hart-Celler Immigration bill” እየተባለ የሚታወቀው የኢሚግሬሽን ህግ ቀደም ብሎ የነበረውን ለጥቂት አገሮች ብቻ አድልዎ ያደርግ የነበረውን አሰራር የቀየረ ህግ ነበር:: ታዲያ ይህ ህግ እንዲሁ በድንገት የተከሰተ አልነበረም:: እ.ኤ.አ. ከ1957 ጀምሮ በአሜሪካ ይደረግ ከነበረው የዜጋ መብት-እኩልነት ትግል (ከCivil Rights Struggle) ጋርና በኋላም በብዙ ትግልና መስዋዕትነት በድል አድራጊነት የጥቁር አሜሪካዊያኖችን የእኩል-ዜግነት መብትን ለማስከበር ካለፉትና ጸድቀው ከተፈረሙት ህጎች ጋር የተሳሰረ እንደነበር የዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ ያትታሉ::

እንግዲህ ለኛ መጤዎቹ፤ በተለይም ከምድረ አፍሪካ ለመጣነው – በዚህ ምድር ለመብታችን ህጋዊ ሥረ – መሰረት የሆነውን ታሪክ ጠቅሰን ይህን ካልን፤ ያ የተደረገው ትግል ለምንወያይበት ጉዳይ እጅግ በጣም ጠቃሚ ትምህርት ስለሚሰጠን ስለሱ ደግሞ እስቲ አንድ፣ ሁለት ነገሮች እንበል::

እኛ ዛሬ ተጠቃሚ የሆንንበትን የ ሙሉ ዜጋ መብትን ያስገኘልን የአሜሪካው የዜጋ መብት-እኩልነት ትግል (Civil Rights Struggle) ቀደም ላሉ ዓመታት ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም ትግሉ ተፋፍሞ የተቀጣጠለው እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ ማብቂያና በ1960ዎቹ ዓ/ም ውስጥ ነው:: በነዚህ ዘመናት ታዲያ ይህ የእኩል-ዜግነት መብት ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሞራል ጉዳይም ነው ብለው አግላይነትን (Segregationን) ለመዋጋት ትግሉን ከፊት ሆነው ይመሩትና ያቀናጁት የነበሩት እንደነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያሉ በ Southern Christian Leadership Conference ሥር የተሰባሰቡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ነበሩ:: ለእነዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሮሜ 13 መልዕክት ጠፍቷቸው አልነበረም ባለሥልጣናትን የተጋፈጡት::

በእርግጥም የዓላማ ጥራት ነበራቸው:: በወቅቱ በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የጥቁር አሜሪካዊያንን የእኩል-ዜግነት መብት ይነፍግ የነበረውን የአግላይ መርህ (segregationist policy) በኢ-ፍትሐዊነት (በጡር/immorality) ለመፈረጅ ብዠታ አልነበራቸውም:: ስለሆነም እነዚህን ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ህግ-ተብዬዎችን ማውገዝ፣ መቃወምና በዐመጽ-ዓልባ ትግል የእኩልነት መብታቸውን ማስከበር መለኮታዊ ጥሪያቸውና ግዴታቸው እንደሆነ እንጂ የፖለቲከኞች ጉዳይ ብቻ አድርገው አልተዉትም:: ምዕመናቸውን ስለ ትግሉ ፍትሐዊነት በማስተማርና ዐመጽ-ዓልባ ለሆነው ትግሉም በማስተባበር፤ እነዛን ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ህጎችን እያወቁ በመጣስ፤ ከዛም ጋር ተያይዞ የመጣውን ግፍና መከራ ፈቅደው በመቀበል ነው ዛሬ እኛ የምንኖርበትን የእኩል ዜጋ መብትና ነጻነትን ያስገኙልን:: ያ ትግል ወንድምና እህቶቻችን የሆኑት አፍሪካ-አሜሪካዊያኖች በዋነኛነት እጅግ በጣም ትልቅ ዋጋ የከፈሉበት ትግል ነው::    በትግሉ ይሳተፉ የነበሩ ሰዎች ለአመጽ በተደራጁ ሰዎች ተቀጥቅጠውና ተሰቅለው ተገድለዋል፤ ቤተ ክርስቲያናት በቦምብ ጋይተዋል፤ በዚያም የነበሩ ህጻናት ተገድለዋል፤ ለሠላማዊ ሰልፍ የወጡ ወንድና ሴቶች በተናካሽ ውሾች ተዘንጥለዋል፤ በፖሊሶች ያለ-ርህራሄ በዱላ ተደብድበዋል፣ ተፈንክተው ደማቸው ፈስሷል፤ ወደ እስር ቤቶች ተግዘዋል . . . ወዘተ.   

ታዲያ ይሄ ሁሉ ዋጋ የተከፈለበትንና በዚያም ምክንያት የተገኘውን ድል አጣጥመን እየበላን-እየጠጣንበት፥ እየወጣን-እየገባንበት፥ [መብታችን ተከብሮ] እየሠራን-እየበለፀግንበት፥ ወግ ማዕረግ አይተን ወልደን እየከበድንበት . . . ፥  “የ. . .  መብት ጉዳይ  የፖለቲካ ጉዳይ ስለሆነ እኔን አይመለከተኝም” ማለት በጣም የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ነገር አይደለም? ኅሊና ያለው ሰው ራሱ ይፍረድ:: ‘ይህ’ ከኛ የሚጠበቅ ነው? መተኪያ የማይገኝለትን ውድ የሰው ህይወት መስዋእትነት ያህል የተከፈለበትን ክቡር ነገር አቅልሎ ማየትና በተዛቡ የመንፈሳዊ ትርጓሜዎች ሽፋን በቸልተኝነት ኃላፊነትን መሸሽ ከምን የመነጨ ነው? ለዛ መልስ ሆነው ሊባሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም በጥቅሉ ግን ፦

 • ፍትሕን በተመለከተ ያለን ግንዛቤና ከዛም ጋር በተያያዘ የኛ ኃላፊነት ምን ሊሆን እንደሚገባው በትክክለኛ አለመረዳት፤
 • ኃላፊነቱን መቀበል ጥቅማችንን (በተለይም የተቋማትን ጥቅም) ሊጋፋ እንደሚችል በመስጋት እና
 • ዋጋ እንደሚያስከፍለን በመፍራት ሊሆን ይችላል::

ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ህጎችን መቃወምና ማውገዝ – ክርስቶስን በጌታና አዳኝነቱ ተቀብለን ፤ ልንከተለው የገባነው ቃልኪዳን አካል ፤ እምነታችን በተግባር የሚግለጽበት ነገር ነው መሆን ያለበት:: ኢ-ፍትሐዊ ህጎችን መቃወም ትክክለኛ ስለመሆኑ ቀደም ያሉ የክርስትና እምነት ትምህርት አባቶች የነበሩት እነ St. Augustine እና St. Thomas Aquinas ከማስተማራቸውም ሌላ ክርስቶስም በማቴዎስ 23:23 ላይ “በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና . . . “ በማለት የሃይማኖት መሪዎችን ገሰጾ የፍትሕን ነገር ችላ እንዳንል ሁላችንንም ያዝዘናል::

ጌታ ኢየሱስ ከአብ የተላከው የሰው ዘር ሁሉ በእርሱ እንዲድን ነው:: ሆኖም በዚህ ምድር በተመላለሰበት ዘመን ለተገፉ፣ ለተገለሉ፣ ዐቅም ለሌላቸው፣ ለተበደሉና ለተናቁ ልዩ የሆነ ፍቅር እንደነበረውና ለነሱም ጠበቃ ሆኖ ባለሥልጣናትን ሲገስጽና ሲያወግዝ በመጨረሻም ታላቅ ዋጋን ከፍሎ፣ መከራን ተቀብሎ፣ ክቡር ህይወቱን መስዋዕት አድርጎ እንደሰጠ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን::

የሚያስከፍለንን ዋጋ በማሰብም ሆነ ስለጥቅማችን መጓደል በመስጋት የፍትሕን ነገር ችላ ብንል በማቴ. 25: 31-46 ላይ የተጻፈውን የክርስቶስ ኢየሱስን ቃል እናስብ፦ “ . . . ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ አለማድረጋችሁ፣ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ነው’ ይላቸዋል። . . .”

እንግዲህ ስለፍትሕና ስለኃላፊነታችን ይህን ካልን ዘንዳ ባሁኑ ወቅት አስከፊ ግፍና በደል እየተፈጸመባቸው ላሉት ወገኖቻችን በክርስቶስ ተምሳሌት ስለበደላቸው ድምጻችሁን እንድታሰሙ፣ ግፈኞቹን እንድታወግዙና ስለፍትሕም በትጋት በመሥራት ጌታችን በሚገለጥበት ጊዜ በፊቱ ሳናፍር፤ በተግባራችን ታማኝነታችንን የሚያስመሰክር ግፉአንን የመታደግ ስራ እንድንሰራ በጌታ ፍቅር ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን::

ተጻፈ ረቡዕ የካቲት 7/2010 ዓ/ም

Share this post

One thought on “ያላባራው የኢትዮጵያውያን መከራና የተናቀው የወንጌል እውነት – ግልጽ ደብዳቤ ለወንጌላዊ አማኞች በመላው ዓለም ለምትኖሩና በደሙ ለተዋጃችሁ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ፦

 1. ኢትዮፕያንቸርች ዶት ኦርግ ላይ ብዙ መጣጥፎችን ቅርብ ጊዜ ሰው ጠቁሞኝ ሳነብ ነበር። ሁለቱን ከታች ለጥፌአለሁ። የቀረውን ድረገጹ ጋ ሄዶ ማየት ይቻላል።
  http://ethiopianchurch.org/en/editorial2/277-%E1%8C%AD%E1%88%AB%E1%89%86%E1%89%BB%E1%89%BD%E1%8A%95.html
  http://ethiopianchurch.org/en/editorial2/275-%E1%89%A2%E1%8B%88%E1%88%B3%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%88%9D-%E1%88%98%E1%8D%8D%E1%89%B5%E1%88%94%E1%8B%8D-%E1%89%80%E1%88%8B%E1%88%8D-%E1%8A%90%E1%8B%8D.html

  Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.