ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደሚሰየሙ ተገለጸ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8B%B6%E1%8A%AD%E1%89%B0%E1%88%AD-%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%8B%AD-%E1%8A%A0%E1%88%95%E1%88%98%E1%8B%B5-%E1%8B%A8%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%8C%A0%E1%89%85%E1%88%8B%E1%8B%AD/

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 19/2010) ትላንት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደሚሰየሙ የኢሕአዴግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለፓርቲና ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አቶ ደመቀ መኮንን ራሳቸውን ከምርጫው እንዳገለሉም አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ወገኖች ይፋ በሆኑ ተመሳሳይ መረጃዎች መሰረት ዶክተር አብይ አህመድ ከ170 መራጮች የ108ቱን ድምጽ በማግኘት መመረጣቸውም ታውቋል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ትላንት ባደረገው ስብሰባ ከ180 አባላት በምርጫው የተካፈሉት 170ዎቹ እንደሆኑም ተዘግቧል።

ከእያንዳንዱ ፓርቲ 45 በጥቅል 180 አባላት በሚሳተፉበት የኢሕአዴግ ምክር ቤት በተለያዩ ምክንያት 10 አባላት ያልተገኙ ሲሆን 170ዎቹ በምርጫው ተሳትፈዋል።

የድምጽ አሰጣጡ ሒደት ከመጀመሩ በፊት የብአዴኑ ሊቀመንበር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል።

የአቶ ደመቀ መኮንን ራሳቸውን ከምርጫው ማግለል የዶክተር አብይ አህመድን የማሸነፍ እድል እንዳሰፋው ተመልክቷል።

ዶክተር አብይ አሕመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ብሎም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ብአዴን አቋም ይዞ መንቀሳቀሱም ተመልክቷል።

የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በማህበራዊ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ለዶክተር አብይ መመረጥ ብአዴን የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን አረጋግጠዋል።

“ብአዴን ለኢሕአዴግ ብቁ መሪ ለመምረጥ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል”በማለት ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

የኦሕዴድ ደጋፊ ዶክተር ደረጄ ገረፋ በበኩላቸው ለዶክተር አብይ መመረጥ ብአዴንን እንደ ድርጅት አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን እንደ መሪ የተጫወቱትን ሚና በማመስገን በማህበራዊ ገጻቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ከዶክተር አብይ ጋር የተወዳደሩት የሕወሃቱ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ሁለት ድምጽ ሲያገኙ ሶስተኛው ተወዳዳሪ የደኢሕዴኑ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ 59 ድምጽ ማግኘታቸው ይፋ ሆኗል።

በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ወደ መሪነት የመጣው የአቶ ለማ ቡድን አባል የሆኑት ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደሚሰየሙም የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አስታውቀዋል።

የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለፓርቲና ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ቀኑ ባይገለጽም ዶክተር አብይ አህመድ በፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ይሰየማሉ።

ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን ተከትሎ አዲስ ካቢኔ ያቋቁማሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ፓርላማው በስራ ላይ በመሆኑ ነገ ሀሙስ ወይንም በሚቀጥለው ማክሰኞ ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሰይማል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 

 

 

 

The post ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደሚሰየሙ ተገለጸ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

One thought on “ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንደሚሰየሙ ተገለጸ

  1. What a great achievement!! ESAT people, did you learn from your stupid political analysis for days and months? Why do not you guys do what you are good at – investigative journalism. You were even writing to OPDO and ANDM to leave EPRDF. You think it is easy like walking in the streets? What shameful and childish political analysis!! You must be careful. You guys have many listeners everywhere including in Ethiopia
    Your messages must not be confusing and erroneous.

    Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.