ዶ/ር አክሊሉ ከቻይና የቢዝነስ ልዑካን ጋር ተወያዩ

Source: https://fanabc.com/2019/05/%E1%8B%B6-%E1%88%AD-%E1%8A%A0%E1%8A%AD%E1%88%8A%E1%88%89-%E1%8A%A8%E1%89%BB%E1%8B%AD%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%89%A2%E1%8B%9D%E1%8A%90%E1%88%B5-%E1%88%8D%E1%8B%91%E1%8A%AB%E1%8A%95-%E1%8C%8B%E1%88%AD/

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2011 (ኤፍቢሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በጋዎ ሶንግ የተመራ በህክምና ቴክኖሎጂ ከተሰማራ የቻይና የቢዝነስ ልዑካን ጋር ተወያዩ።

ዶክተር አክሊሉ የቻይና የቢዝነስ ልዑካን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ስለሀገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በማደግ ላይ የሚገኝ ኢኮኖሚ፣ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖርባት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ከ130 በላይ ኤምባሲዎች፣ የበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗን አብራርተዋል።

እንዲሁም መንግስት ለህክምና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአብነትም በ26 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህክምና ትምህር እንደሚሰጥ፣ በርካታ ሆስፒታሎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

ዶክተር አክሊሉ ልዑኩ ኢትዮጵያን መምረጡ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ሲሉም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ለሚያደርጓቸው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም ተናግረዋል።

የልዑካን ቡድኑም በኢትዮጵያ በህክምና ዘርፍ በተለይም ከካንሰርና መሰል በሽታዎችን ለማከም የሚደረጉ ጥረቶችን በዳበረ ቴክኖሎጂ መፍታት የሚያስችል ሰፊ ልምድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ለኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎችና የዘርፉ ተማሪዎችም የስልጠናና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ እንዳቀዱም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.