ዶ/ር ኤርጎጌ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

Source: https://fanabc.com/2019/04/%E1%8B%B6-%E1%88%AD-%E1%8A%A4%E1%88%AD%E1%8C%8E%E1%8C%8C-%E1%8A%A8%E1%8A%B3%E1%89%B3%E1%88%AD-%E1%8C%A0%E1%89%85%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%88%9A%E1%8A%92%E1%88%B5%E1%89%B5%E1%88%AD-%E1%8C%8B%E1%88%AD/

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትርና የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ናስር ቢን ካሊፋ አል ታሃኒ ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም ሀገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።

በዚህ መሰረትም የሰራተኛ ስምሪት ስምምነቱን በአፋጣኝ ወደ ስራ ለማስገባት፣ የዜጎቻችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እና ለኢትዮጵያ የሰራተኛና አሰሪ ኤጀንሲዎች የብዙ ጊዜ መመላለሻ ቪዛ ለመስጠት ተስማምተዋል።

በተጨማሪም በሰራተኛ ስምሪት ስራ የተማሩ ዜጎቻችንን ለማካተት እና በሰራተኛ ጉዳይ ዙሪያ እንደተደረገው ሁሉ በሌሎች የማህበራዊ ጉዳይ መስኮችም የትብብር ስምምነት ለመፈራረም መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትርና የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ናስር ቢን ካሊፋ አል ታሃኒ ኳታር የቪዛ መስጫ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ ለመስራት በአንድ ሳምንት ውስጥ የልዑክ ቡድን እንደምትልክ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሯ የኳታር መንግስት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች እያደረገ ላለው ድጋፍና ትብብር ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን በኳታር ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ ዶክተር ኤርጎጌ ከኳታር አቻቸው ዮሱፍ ሞሃመድ አል ኦስማን ፋክሩህ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሀገራቱ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ኢትዮጵያና ኳታር ከስምምነት ላይ የደረሱበትን የሰራተኛ ስምሪት ስምምነት በአፋጣኝ ወደ ሥራ ለማስገባትም በሁለቱም ወገኖች በኩል ዝግጅቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም ሚኒስትሯ በኳታር ከሚገኙ የኢትዮጵያዊያን የሰራተኛና አሰሪ ኤጀንሲ ባለቤቶች ጋር ምክክር አድርገዋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.