ግሎባል አሊያንስ ከቤንሻንጉል ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ8 መቶ ሺህ ብር በላይ እረዳ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8C%8D%E1%88%8E%E1%89%A3%E1%88%8D-%E1%8A%A0%E1%88%8A%E1%8B%AB%E1%8A%95%E1%88%B5-%E1%8A%A8%E1%89%A4%E1%8A%95%E1%88%BB%E1%8A%95%E1%8C%89%E1%88%8D-%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%88%88%E1%89%B0/

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2010) አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን/ግሎባል አሊያንስ/ ከቤንሻንጉል ክልል ለተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ከ8 መቶ ሺህ ብር በላይ እርዳታ ሰጠ።

በአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አሊያንስ ለተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች የላከውን ገንዘብ ለብርድልብስና አልባሳት እንዲሁም ለእለት ምግባቸው እንደሚያውሉት ተረጂዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች በግሎባል አሊያንስ ወገናዊነት ልባቸው እንደተነካ በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

በባህር ዳር ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የተጠለሉት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉት የአማራ ክልል ተወላጆች ተወካይ አቶ አበባው ጌትነት ለኢሳት እንደገለጹት አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ግሎባል አሊያንስ የላከው ገንዘብ 8 መቶ አንድ ሺ ብር ነው።

በዚሁም አልባሳትና የእለት ችግራቸውን ለመፍታት እንደሚረዳቸው ነው የገለጹት።

ግሎባል አሊያንስ ለወገን በመቆርቆር ከውጭ ገንዘቡን በመላኩም የተፈናቃዮቹ ተወካይ አቶ አበባው ጌትነት አመስግነዋል።

በአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አሊያንስ በተለያዩ የአለም አካባቢዎችም ለሚገኙ ስደተኞችና በሃገር ውስጥ ለሚደርሱ መፈናቀሎች ልዩ ልዩ እርዳታዎችን ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።

ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ከክልሉ መንግስትም ይሁን ከፌደራሉ ምንም አይነት ዘላቂ እርዳታ እንዳልተደረገላቸው ይናገራሉ።

ከዚህም በፊት ከሚኖሩበት የቤንሻንጉል ቀዬ ከተፈናቀሉት ከ5 መቶ በላይ ሰዎች አሁን በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተጠልለው የቀሩት 160 ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ በኮማንድ ፖስቱ ታፍነው የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ ነው የተናገሩት።

ተፈናቃዮቹ የክልሉ መንግስት በዘላቂነት በአማራ ክልል ውስጥ እንዲያቋቁማቸው ይጠይቃሉ።

ወደ ቤንሻንጉል ክልል ተመለሱ የሚለውን የመንግስት ውሳኔ ግን በምንም አይነት እንደማይቀበሉት ተፈናቃዮቹ የአማራ ተወላጆች አረጋግጠዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

The post ግሎባል አሊያንስ ከቤንሻንጉል ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ8 መቶ ሺህ ብር በላይ እረዳ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.