ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቻይና ነፃ የትምህርት እድል ላገኙ 228 ኢትዮጵያውያን ሽኝት አደረጉ

Source: https://fanabc.com/2019/09/%E1%89%BB%E1%8B%AD%E1%8A%93-%E1%88%88228-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8B%8D%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%89%B0%E1%88%9B%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%8A%90%E1%8D%83-%E1%8B%A8%E1%89%B5/

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 30፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይና ነፃ የትምህርት እድል ላገኙ 228 ኢትዮጵያውያን ሽኝት አደረጉ።

ቻይና ለ228 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ነፃ የማስተርስና የዶክትሬት ትምህርት እድል መስጠቷ ተገልጿል።

ለነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚዎቹም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በዛሬው እለት በብሄራዊ ቤተ መንግስት የሽኝት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ መንግስት ቃል በገባው መሰረት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የውጭ የትምህርት እድል ለማመቻቸት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በዛሬው እለት የሚሸኙት 228 ተማሪዎች የትምህርት እድል በቻይና ንግድ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የተሰጠ መሆኑን በመግለጽ፤ በኋላ ላይ የሌሎች ተማሪዎች ተደምሮ የዘንድሮ የነፃ የትምህርት እድል ተጠቃሚዎች ቁጥር 400 እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

የትምህርት እድል ያገኙ ተማሪዎች ለትምህርት ቻይና ሄደው ሲመለሱ ሀገራቸውን የሚጠቅም እውቀት በሌሎች ነገሮች ሳይዘናጉ መገብየት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የሚገበዩትን እውቀትም በብዙ አስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ የምትገኘውን ሀገራቸውን ለመርዳት እንዲያውሉም አስገንዝበዋል።

ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገር ሲጓዙም መጥፎ አስተሳሰቦችን በመተው አዲስ ማንነት ይዘው መጓዝ እንዳለባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተናግረዋል።

ቻይና ዘንድሮ በ90 ሀገራት ለሚገኙ 1 ሺህ 300 ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል መስጠቷን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ከዚህም ውስጥ ከ100 በላይ ተማሪዎችን በመላክ ቀዳሚ ተጠቃሚ ኢትዮጵያ እንደሆነችም አስታውቀዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2018 ድረስም 7 ሺህ 697 ኢትዮጵያውያን በቻይና የነፃ የአጫጭር ስልጠና እና የዲግሪ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በዘንድሮው ዓመትም ከ400 የትምህርት እድል ተጠቃሚዎች በተጨማሪ 800 ኢትዮጵያውያን ለአጫጭር ስልጠና ወደ ቻይና እንደሚያቀኑም ገልፀዋል።

ትምህርትና ስልጠናዎቹም በልማት ስትራቴጂና ፖሊሲ፣ ኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ በባህልና ቱሪዝም፣ በትራንስፖርት፣ በቴሌኮም መሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ አስተዳደር እና ድህነት ቅነሳ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ይህንን ኮታ ቻይና ለኢትዮጵያ መስጠቷ የሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ደረጃ ትልቅነትን እንደሚያመላክትም አስታውቀዋል።

በባሃሩ ይድነቃቸው

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.