ጠቅላይ ሚንስትር የሚሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ መከላከያውና ደህንነቱ ይታዘዙላቸዋል ተብሎ እንደማይጠበቅ እየተነገረ ይገኛል

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/43418

አባይ ሚዲያ ዜና
አቤነዘር አህመድ

የአራት ድርጅቶች ጥምር የሆነውን የኢህአዴግን ግንባር በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት ዶክተር አብይ በግንባሩ የስራ አካሄድ መሰረት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትርም ሆነው እንደሚያገለግሉ ተገልጿል።

የቀድሞውን ሟች ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊን ተክተው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከ 2015 እኤአ ጀምሮ እየተቀጣጠለ የመጣውን የህዝብ እምቢተኝነት መቋቋም አቅቷቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ በተደረገው የሊቀመንበርነት ፉክክር የኦህዴዱ ዶክተር አብይ አህመድ ከ180 ድምጽ 108 ድጋፍ በማግኘት ተተኪ መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ባሳለፍነው ሶስት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ እና በአማራ ህዝብ መሪዎች መካከል እየተስተዋለ ያለው መናበብ እና መደጋገፍ በኢህአዴግ የሊቀመንበርነት ምርጫ ሂደት ላይ በከፍተኛ ደረጃ ተንፀባርቆ ዶክተር አብይ ስልጣኑን እንዲይዙ እንደረዳቸው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

ዶክተር አብይ አህመድ የአገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ማገልገል ሲጀምሩ ከፊታቸው እጅግ ከባድ ፈተና ተደቅኖ እንደሚጠብቃቸው እየተነገረም ይገኛል።

ሹመቱ መባከን የሌለበት እድልን ያቀፈ እንደሆነ በመግለጽ ዶክተር አብይ ይህን እድል በርግጥ ለመጠቀም ከወሰኑ ኢትዮጵያን በሰላማዊ መንገድ ወደ ዲሞክራሲ የማሸጋገር ታሪክ መስራት ይችላሉ በማለት አክትቪስት ጃዋር መሃመድ አስተያየቱን ሰጥቷል።

የሰማያዊ ፓርቲ መሪ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ዶክተር አብይ ህዝቡ እየጠየቀ ያለውን የለውጥ ጥያቄ መረዳት ይችላሉ ብለው እንደሚያምኑ በመግለጽ ዋናው ቁም ነገር መሆን ያለበት ህዝቡ እያነሳ ያለውን ጥያቄዎች መረዳት መቻል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ከእስር የተለቀቁት የኦሮሞ ፌዴራል ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በሰጡት አስተያየት በአገሪቷ ለውጥ የማምጣት ሃይል በዶክተር አብይ አህመድ ስር ሊሆን እንደማይችል ስጋታቸውን ጠቁመዋል። ዋናው የሃይል ሚዛን የሆኑት መከላከያው እና ደህንነቱ  በታማኝነት ይታዘዙላቸዋል ብለው እንደማይገምቱም አቶ በቀለ ገርባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። እነዚህ ሁለት ክፍሎች (መከላከያው እና ደህንነቱ)  ለህገ መንግስቱ ተገዢ ሆነው ይሰራሉ የሚሉት ጥያቄዎች  የአገሪቱን የወደፊት እጣ ፋንታ መወሰን የሚያስችሉ ነጥቦች እንደሆኑ አቶ በቀለ ገርባ አክለው ገልጸዋል።

በአገሪቱ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ በየእስር ቤቱ እየተሰቃዩ የሚገኙ ጋዜጠኞች እንዲሁም ፖለቲከኞችን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት እንዲሁም ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር እውነተኛ ውይይት ማድረግ  የዶክተር አብይ አህመድ ቆራጥነት የሚለካበት መስፈርቶች እንደሆኑም አስተያየት ሰጪዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ጠቁመዋል።

በንፁሃን ኢትዮጵያውያኖች ላይ የግድያ እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የፈፀሙ የመንግስት ባለስልጣናትን እንዲሁም ወታደሮችን ለፍርድ ማቅረብ ከቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር የሚጠበቁ ነገር ግን ፈታኝ የቤት ስራዎች እንደሆኑም ተንታኞች ገልጸዋል።

ዶክተር አብይ አህመድ ውስብስብ እና ፈታኝ ችግሮች ከፊታቸው ቢደቀንባቸውም በስልጣናቻው በጎ ታሪክን የመስራት እድልም በእጃቸው እንዳለ በመጠቆም ይህን እድል እንደ አቶ መለስ ዜናዊ አሊያም እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳያባክኑት የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች በማህበራዊ ሚዲያ እየገለጹ ይገኛሉ።

 

 

 

 

 

 

Share this post

One thought on “ጠቅላይ ሚንስትር የሚሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ መከላከያውና ደህንነቱ ይታዘዙላቸዋል ተብሎ እንደማይጠበቅ እየተነገረ ይገኛል

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.