ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተወያዩ

Source: https://fanabc.com/2019/04/%E1%8C%A0-%E1%88%9A-%E1%8B%B6%E1%8A%AD%E1%89%B0%E1%88%AD-%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%8B%AD-%E1%8A%A0%E1%88%85%E1%88%98%E1%8B%B5-%E1%8A%A8%E1%89%BB%E1%8B%AD%E1%8A%93%E1%8B%8D-%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%8B%9A/

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ፡፡

ሺ ጂንፒንግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አመራርና ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት እንደሚያደንቁ የገለፁ ሲሆን፥ ቻይና ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ ቦታ ትሰጣለች ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በውይይቱ ወቅትም እስከ ፈረንጆች 2018 መጨረሻድረስ የተጠራቀመው የብድር ወለድ ሙሉ በሙሉ እንደተሠረዘ አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም የቻይና መንግስት የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትን ጠቀሜታ ይረዳል ያሉት ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥታቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁለንተናዊ የስትራቴጂ አጋርነት እንደምታጠናክር ገልፀዋል፡፡
 
እንዲሁም እንደ አዲስ ጅቡቲ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት ያሉ ዕዳዎችን ለመከለስ የሚረዱ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን ለመተግበር ኢትዮጵያ ቁርጠና መሆኗን ነው የገለፁት፡፡
 
የባቡር ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ተሳታፊ የሆነችበት የቤልት ኤንድ ሮድ ማዕቀፍ ቀዳሚ ውጤት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
 
ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቻይና በአደገኛ እፅ ዝውውር ተጠርጥራ በእስር ላይ የምትገኘው ኢንጂነር ናዝራዊት አበራ ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ለፕሬዚዳንቱ አንስተዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈ መሪዎቹ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር በተለያዩ ዘርፎች አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል።

 

Photo:-office of the prime minister

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.