ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን ነገ መርቀው ይከፍታሉ

Source: https://fanabc.com/2018/10/%E1%8C%A0-%E1%88%9A-%E1%8B%B6-%E1%88%AD-%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%8B%AD-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8B%B3%E1%88%9B-%E1%8A%A2%E1%8A%95%E1%8B%B1%E1%88%B5%E1%89%B5%E1%88%AA-%E1%8D%93%E1%88%AD%E1%8A%AD%E1%8A%95-2/

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክን በነገው ዕለት መርቀው ይከፍታሉ፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የኢፌዴሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማምረቻ ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

የአዳማው ኢንዱስትሪ ፓርክም የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን ለፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡

ግንባታው በ2009 ዓመተ ምህረት ጥቅምት ወር ላይ የተጀመረው ይህ ፓርክ፤ በ102 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ከ147 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ነው ግንባታው የተካሄደው፡፡

ፓርኩ በተለያየ ዘርፍ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች የሚያገለግሉ 19 የመስሪያ ሼዶች ወይም የመስሪያ ቦታዎችን የያዘ ነው።

ከእነዚሀ ሼዶች ውስጥም ስድስቱ 11 ሺህ ካሬ ሜትር፣ ዘጠኙ 5 ሺህ 500 ካሬ ሜትር፣ አራቱ ደግሞ በ3 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ናቸው።

ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገባም ከ60 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.