ፈተና አልባ ምርጫ ማድረግ ባይቻልም፤ የተሻለ ምርጫ ግን ማካሄድ ይቻላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ

Source: https://fanabc.com/2019/10/%E1%8D%88%E1%89%B0%E1%8A%93-%E1%8A%A0%E1%88%8D%E1%89%A3-%E1%88%9D%E1%88%AD%E1%8C%AB-%E1%88%9B%E1%8B%B5%E1%88%A8%E1%8C%8D-%E1%89%A3%E1%8B%AD%E1%89%BB%E1%88%8D%E1%88%9D%E1%8D%A4-%E1%8B%A8%E1%89%B0/

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፈተና አልባ ምርጫ ማድረግ ባይቻልም፤ የተሻለ ምርጫ ግን ማካሄድ እንደሚቻል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።

በጉባዔው ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ከምርጫው ጋር ተያይዞ በተለይም ከአሁኑ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምርጫውን አሁን ማድረግ አዋጭ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስት አቅርበው ምላሽ ተሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት ምላሽም፥ በዘንድሮውም ሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ችግር አልባ፤ ተግዳሮት የሌለው ምርጫ ማድረግ አይቻልም፤ ምክንያት እየፈለጉ አሁን እንችልም ብንል ብዙ ችግር ነው ያለው ብለዋል።

አሁን ያለው ምክር ቤት ስልጣኑን ማራዘም ይችላል ነገር ግን አሁን ባለው ሞራል ሊቀጥል አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ስለዚህም የህዝብን ይሁንታ አግኝቶ እንዳዲስ መወከል ይሻለል ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም ምርጫ ተደርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ምርጫ አይደረግ የሚለው ጉዳይ ለእኔ አሳማኝ አይደለም ሲሉም አብራርተዋል።

ከምርጫ ቦርድ ጋር በተያያዘም፥ ቦርዱ አሁን ያለው ቁመና ከአምና እና ካቻምና በተሻለ ቁመና ላይ ነው እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን በቂ በጀት መንግስት የመደበለት መሆኑን እና ቦርዱ እስካሁን ከነበሩት አባላት በተሻለ የህዝብ እና የምክር ቤቱን ይሁንታ አግኝተው መመረጣቸውንም አስታውሰዋል።

መንግስት ዴሞክራሲያዊ እና ነፃ ምርጫ እንዲደረግ ፍላጎቱ መሆኑን በመግለጽ፤ መንግስት በምርጫው ከተሸነፈ ስልጣን ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑንም በማሳያነት አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዴሞክራሲያዊ እና ነፃ ምርጫ እንዲደረግ ለማስቻል አዲስ የምርጫ ህግ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ፈተናዎችን ስላሳለፈ የአንድ ቀን ምርጫን መቋቋም አያቅተውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ፥ ምርጫን ተከትለው የሚመጡ ግጭቶች የሚያስከፍለውን ጉዳት ከምርጫ 97 በተግባር ተምሯል፤ ህዝቡ ምርጫን አስታኮ የሚከሰት ግጭትን የሚፈልግ ህዝብ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።

ችግር አለ ተግዳሮት አለ ሆኖም መንግስት እና ህዝብ ተግባብተው ከሰሩ ችፍሩን መፍታት ይችላሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን፣ ሲቪክ ማህበራት ሚናቸውን ከተወጡ እንደዚሁም ፓርቲዎች ህዝብን አሳምነው ከተመረጡ ስልጣን ለመረከብ እንዲሁም ከተሸነፉ ውጤቱን ለመቀበል ዝግጁ ከሆኑ የተሻለ ምርጫ ማድረግ ይችላል።

ሌላው ለምርጫው ወሳኝ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፤ ፓርቲዎች በነፃነት የመወዳደር እድል ስላገኙ ይህንን መጠቀም ይኖርባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የምርጫ ህጉ ለካቢኔ ሳይቀርብ የምርጫ ቦርድ ባለደርሻ አካላትን አወያይቶ ማፅደቁን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ከአንድ አንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ከምርጫ ህጉ ጋር በተያያዘ የሚያነሱት ቅሬታ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

እነዚህ አካላት 30 እና 40 ሆነው ምርጫን እንዴት ማሸነፍ ይችላሉ፤ ምርጫን የማሸነፍ እድል ቢያገኙስ እንዴት ሀገርን መምራት ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ አባል ማብዛት ባይቻል አንኳ ወደ አንድ መሰባሰብ ተገቢ ነው ሲሉም አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አክለውም፥ የዘንድሮ ምርጫን ማድረግ በብዙ መንገድ ተገቢ ነው፤ ፈተና አልባ ምርጫ ማድረግ ባይቻልም የተሻለ ምርጫ ግን ማድረግ ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር አያይዘው ስለ ኢህአዴግ ውህደት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ ባለፉት 10 ዓመታት ውይይት ሲደረግበት እንደነበረ እና በሀዋሳው ጉባኤ የኢህአዴግ ምክር ቤት ተገቢውን ስራ ካከናወነ ከቀጣዩ ጉባኤ በፊት ውህደቱን ይፈፀም ብሎ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን አስታውሰዋል።

ውህደቱ አያስፈልግም የሚል ሀሳብ እስከዛሬ አልሰማሁም ያሉ ሲሆን፥ ውህደቱ ግን አሁን መሆን የለበትም የሚል በግለሰብ እና በፓርቲ ደረጃ ይነሳል፤ ጥናቱን ካየን በኋላ ግን የኢህአዴግ ምክር ቤት የሚያፀድቀው ይሆናል ብለዋል።

ነገር ግን የኢህአዴግ ውህደትን ከሀገር እና ከመንግስት ጋር ማያያዝ ተገቢ አይደለም፤ ኢህአዴግ ከሌለ ሀገር የለም መንግስት የለም ማለት ስህተት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ህዝቡን ከማወያየት ጋር ተያይዞ በተለይም ለምን የወሎን ህዝብ አያወያዩም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፥ የወሎን ህዝብ ብቻ ሳይሆን የድሬዳዋ እና የሐረር ህዝብን የማወያየት ጥያቄ ይቀርባል፤ ፕሮግራም እያመቻቸን እናወያያለን ብለዋል።

ከክልሎች ትጥቅ ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰጡት ማብራሪያ፥ ክልሎች የያዙት ትጥቅ በሌሎች ሀገራት አይን ሲታይ ግለሰብ ከሚታጠቀው ያነሰ ነው፤ ያን ያክል ስጋት የሚያመጣ ትጥቅ የታጠቀ አካል የለም ብለዋል።

ሆኖም ግን ክላሽ የመቁጠር ባህሪ አለ፤ መፍትሄ የሚመጣው በጦርነት ነው ብለው የሚያምኑ አካላት አሁንም አሉ፤ እነዚህ አካላት አሁንም የፓርቲ አመራር ሆነው ነው ያሉት ፤ የሚሞተው ግን የደሃው ልጅ ነው ስለዚህ ህዝቡም በክላሽ ዘላቂ ድል አይመጣም ብሎ በቃ ሊል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ክልሎችን በተመለከተ ትግራይን ለአብነት ያነሱ ሲሆን፥ በትግራይ ያሉ አመራሮች የህዝቡን ችግሮች መፍታት ላይ እንጂ ስለጦርነት አስበው አያውቁም፤ ህዝቡም ልምድ ስላለው ጦርነት አይፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ በሌሎች ክልሎችም እንደዛው ነው፤ ይህንን መረዳት ተገቢ ነው ብለዋል።

ከቅማንት ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄም፤ የቅማንት ጉዳይ በአብዛኛው እልባት ማግኘቱን እና የሶስት በቀሌዎች ጉዳይ ብቻ መቅረቱን በማንሳት፤ ለዚህም አንድም ሰው መሞት የለበትም ብለዋል።

አሁን በአካባቢ ያለውን ግጭት በሶስተኛ ወገን አሊያም በውጭ አካል ማሳበብም ችግሩን ለመፍታት አያስችልም ያሉ ሲሆን፥ መንግስት በአማራና ቅማንት ብቻ ሳይሆን በአፋር እና በሶማሌ ጎሳ መካከል ለተነሳው ግጭት መፍትሄ ለማምጣት እየሰራ ነው ብለዋል።

ሆኖም ግን በሁሉም አካባቢዎች ሀላፊነት ላለመውሰድ ከውጭ የሚመጣ አካል ነው የሚያጠቃን የሚሉ ቅራኔዎች ይስተዋላሉ፤ አሁን መንግስት በስፍራው ልዩ ሀይል ማስገባቱን እና ወንጀለኞችም በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ከመንገድ መዝጋት ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም መንገድ መዝጋት ኋላ ቀርና የብሽሽቅ ፖለቲካ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ መቆም እንዳለበት እና ሰው ሀሳቡን በሰላማዊ መንገድ ወጥቶ እንዲገልፅ ማለማመድ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በሙለታ መንገሻ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.