ፌስታልህን ስጠኝ /ሜሮን ጌትነት/

Source: https://mereja.com/amharic/v2/137504

Imageፌስታልህን ስጠኝ /ሜሮን ጌትነት/
ከጠቆረው ገፅህ ከቆዳህ ላይ ውይብ
ከከሳው ሰውነት ከግንባርህ ሽብሽብ
በፅናት ውሃልክ ይታያል ተሰምሮ
ለቃል የመታመን፣ ላመኑት
የመኖር የአላማ ቋጠሮ።
እኔማ… ከአንተ ጨለማ ውስጥ
በወሰድኩት መብራት
ከአንተ ሰንሰለት ስር ካገኘሁት ፍ’ታት
በአንተ አለመበገር ባገኘሁት ብርታት
ወግ ደርሶኝ ጀግኜ ጬኸቴን ብለቀው
ደርሶ የፈሪ ዱላ
እንደ እያሪኮ ግንብ ተናደ ጭቆና።
እናም ታዲያ ዛሬ…
ወልዶ ላሳደገ ምጥ እንደመካሪ
ቀን የሰጠኝ ቅል ሆንኩ ዞሮ
አንተን ሰባሪ
እርግጥ ገብቶኝ ቢሆን የአላማህ ውጤቱ
መች ያስፈራኝ ነበር
ያንተ ብዕር በልጦ ብረት ካነገቱ
ፍርሃት ባይሆን ኖሮ ስጋት
የሆነብኝ ‘ካፍረቴ እያላጋ
መቼ እዘነጋለሁ የከፈልክልኝን
መራር ትግልና የነፃነት ዋጋ።
አንተ ማለት… ፅናት!
መንገድህ አላማ!
ለሌሎች ደህንነት ራስን የመስጠት-
የድምፅ የለሽ አርማ።
ያልከው ዲሞክራሲ …ያለምከው ነፃነት
እስኪመጣ ድረስ…የታገልክለት ቀን
የታሰርክለት ዕለት
በከፍታህ መጠን የሞራል
ልዕልናን እንዳስታውስበት
ፌስታልህን ስጠኝ ሙዚየም
ሰቅዬ ራሴን ልውቀስበት!
ታሪክ ልንገርበት!
ፅናት ልስበክበት!
 /ሜሮን ጌትነት/
Image

Share this post

One thought on “ፌስታልህን ስጠኝ /ሜሮን ጌትነት/

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.